የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም በቀረበ ረቂቅ ሕግ የተቆጡ ኬንያውያን የምክር ቤቱን ኢሜል አጨናነቁ

የኬንያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በቀጣይ በረቂቅ ሕጉ ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኬንያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አወዛጋቢ የሆነ ረቂቅ ሕግ ላይ የሕዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ ያስቀመጠው ኢሜል በተናደዱ እና በተቆጡ ዜጎች አስተያየት ብዛት ተጥለቀለቀ።

ረቂቅ ሕጉ የፕሬዝዳንቱን፣ የግዛቶች አስተዳዳሪዎችን እንዲሁም ሕዝብ እንደራሴዎችን የሥልጣን ቆይታ ዘመን ከአምስት ዓመት ወደ ሰባት ከፍ ለማድረግ ያለመ እንዲሁም ሌሎች የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን የያዘ ነበር ተብሏል።

ይህ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዕቅድ ኬንያውያንን ያስቆጣ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል።

የአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢሜይል አድራሻ “ከ200 ሺህ በላይ አስተያየቶችን ከሚችለው በላይ ተቀብሏል” ይላል የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ በኤክስ ገጽ ላይ ያሰፈረው መልዕክት።

ይህ የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ምንም እንኳን በአንድ የምክር ቤቱ አባል የቀረበ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ራሳቸውን ከጉዳዩ ማራቃቸው ተሰምቷል።

ዩናይትድ ዲሞክራቲክ አልያንስ (ዩዲኤ) ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የሆኑት ሐሳን ኦማር ረቂቅ ሕጉን “ኋላ ቀር እና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ በአገሪቱ በየዕለቱ በሚታተመው ዘ ኔሽን ጋዜጣ ላይ ተችተውታል።

ረቂቅ ሕጉን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ግለሰብ በበኩላቸው ሰባት ዓመት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እና የምክር ቤት አባላት ለመራጭ ሕዝባቸው ለመሥራት የገቡትን ቃል ለመፈጸመው በቂ ጊዜ ይሰጣቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ኬንያውያን በረቂቅ ሕጉ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት እስከ ዛሬ አርብ ድረስ ብቻ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፓርላማው ምንጮች ለስታር ጋዜጣ በሰጡት አስተያት በየሰከንዱ ኢሜሎች ይደርሷቸው እንደነበር እና እስካሁን የትኛውም ረቂቅ ሕግ የዚህን ያህል መጠን ያለው ምላሽ ከሕዝቡ አግኝቶ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

መልዕክቶቹ እንዲላኩለት ጥሪ ያቀረበው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ምላሽ የሰጡትን ዜጎች አመስግኖ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢሜሎች በመላካቸው ምክንያት እክል አጋጥሞናል” ብሎ ሌላ አማራጭ የኢሜል አድራሻ ሰጥቷል።

ረቂቅ ሕጉ የሥልጣን ዘመንን ከማራዘም ባሻገር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ቦታ እንዲኖር እና ለግዛት አስተዳደሮች የሚሰጠው ገንዘብ ከፍ እንዲል ሃሳብ አቅርቧል።

የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ኮሚቴ በቀረበው ረቂቅ ዙሪያ የሕዝቡን ምላሽ መገምገም ይጀምራል ተብሏል።

ይህ ረቂቅ የቀረበው ኬንያውያን በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት በመንግሥት ላይ ጫና እያሳደሩ ባሉበት ጊዜ ነው።

ባለፈው ዓመት ሰኔ መንግሥት ተግባራዊ ሊያደርገው የነበረን የታክስ ጭማሪ በመቃወም ኬንያውያን ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች አድርገው ቢያንስ 40 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ተቃውሞዎቹን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሕጉን ውድቅ አድርገው የተቀሰቀሰባቸውን ቁጣ ለማብረድም ለተቃዋሚዎች በመንግሥታቸው ውስጥ ሥልጣን ሰጥተዋል።

ይህ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሥልጣን ዘመን የማራዘም ዕቅድ በሕዝቡ ዘንድ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ በኢሜይል ከጎረፉት መልዕክቶች እንደሚንጸባረቅ ይታመናል።

ዊሊያም ሩቶ ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ሥልጣን በመጡባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የሥልጣን ዘመንን ለማራዘም በምክር ቤት አባላት ሙከራ ሲደረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ነገር ግን አንድ ፕሬዝዳንት ለሁለት ዙር ብቻ በሥልጣን ላይ ይቆያል የሚለውን ሕግ ለማስወገድ የተደረገውን ጥረት ፕሬዝዳንት ሩቶ “አላስፈላጊ እና ውጤት የሌለው ሙከራ” በማለት ተቃውመውት ነበር።