ትራምፕ የወሰዱት እርምጃ ኢራን እና እስራኤል ወደ ተኩስ አቁም እንዲመጡ በማድረግ ፍሬ አፍርቶ ይሆን?

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ወደ እስራኤል እና ኢራን ግጭት በማስገባት ቆምረዋል።

ነገር ግን ይህ እርምጃቸው ለጊዜውም ቢሆን ፍሬ ሳያፈራ አልቀረም።

ትራምፕ ትናንት ሌሊት እንዳስታወቁት ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የተስማሙ ሲሆን ያም ወደ ዘላቂ ሰላም ያመራል ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት የ"12 ቀን ጦርነት" ሲሉ የጠሩት የኢራን እና የእስራኤል ግጭት እውነት ሆኖ የሚያበቃ ከሆነ ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ ሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን ከደበደበች በኋላ ቀጣናው ወደ ባሰ ግጭት ለመግባት ጫፍ ላይ የደረሰ መስሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ትልቅ እፎይታን የሰጠ ነው።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በሰጡት መግለጫ "የእስራኤል አገዛዝ ቴህራን እስከ ሌሊቱ 10 ሰዓት ድረስ በኢራን ሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ሕገ ወጥ ጥቃት ካቆመ"፤ "ከዚህ በኋላ ጥቃታችንን የመቀጠል ፍላጎት የለንም" ብለዋል።

ከለሊቱ 10 ሰዓት ሲደርስ በቴህራን የእስራኤል ጥቃቶች መቆማቸው ተዘግቧል።

አሁን ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተጋጋለውን ግጭት ለማቀዛቀዝ የተስማሙ ይመስላሉ።

ኢራን ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ ለፈፀመችው ጥቃት አፀፋውን ለመመለስ ስትዝት በአካባቢው የነበረው አለመረጋጋት ሌላ ትኩሳት እየተሰማው መጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትናንት ምሽት በኳታር በሚገኘው ግዙፍ የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ የተተኮሱት የኢራን ሚሳኤሎች በሙሉ የከሸፉ ሲሆን አንድም አሜሪካዊ ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅዳሜ ምሽት ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ኢራን በአሜሪካ ጥቅም ላይ ለምትሰነዝረው ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።

አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በአሜሪካ ኃይሎች ሊመቱ የሚችሉ ተጨማሪ ዒላማዎች መኖራቸውን ቃል ገብተዋል።

ከ24 ሰዓታት በላይ ዓለም ኢራን ምን ታደርጋለች የሚለውን ለማየት በጥፍሩ ቆሞ ጠብቋል።

ኢራን እርምጃ ከወሰደች በኋላ ደግሞ ትኩረቱ ወደ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ተመለሰ።

እናም ትራምፕ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የመጀመሪያ ንግግራቸውን አደረጉ።

ትራምፕ በማኅበራዊ ገፃቸው ላይ "ኢራን የኒክሌር ተቋሞቿን ለመደምሰስ ለወሰድነው እርምጃ እንደጠበቅነው በጣም ደካማ ምላሽ ነው የሰጠችው፤ እና በጣም ውጤታማ በሆነ መልኩ መክተነዋል።"

ኢራን ከ"ስርዓቷ" እንደወጣች ተናግረው "ምናልባት ኢራን አሁን በቀጠናው ሰላምና ስምምነት መቀጠል ትችል ይሆናል" ብለዋል።

ኢራን በኒውክሌር ተቋማቷ ላእ የደረሰው ጉዳት የተወሰነ እንደሆነ ብትገልጽም፤ ትራምፕ ኢራናውያን በቅንነት ለመደራደር ፈቃደኛ ይሆናሉ በሚል ተስፋ መሳሪያቸውን ለመያዝ ያሰቡ ይመስላል።

እና ከመጋረጃው ጀርባ፣ ዋይት ሐውስ የተኩስ አቁምን ዝርዝር ሁኔታ ከኳታር አደራዳሪዎች እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር እየተነጋገሩ ነበር ተብሏል።

ትራምፕ በሳምንቱ መጨረሻ በኢራን ላይ የፈጸሙት ጥቃት ከፍተኛ አደጋ ያለበት አካሄድ ነበር። ቢሆንም ውጤቱ መታየት የጀመረ ይመስላል።

እአአ በጥር 2020 ትራምፕ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ መሪ ቃሲም ሱሌይማኒ በባግዳድ እንዲገደሉ ባዘዙበት ጊዜም የሆነው ተመሳሳይ ነበር።

ኢራን በኢራቅ ወታደራዊ ካምፖች ላይ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋ ከ100 በላይ የአሜሪካ ወታደሮችን አቁስላለች።

ነገርግን ዩናይትድ ስቴትስ ነገሮችን ማረጋጋት መርጣለች።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፣ ኢራን ሰኞ ዕለት ባደረሰችው ጥቃት፣ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች የጣሉትን አጠቃላይ የቦምብ ብዛት ጋር እኩል የሆኑ ሚሳኤሎችን በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ አስወንጭፋለች።

ኢራን ለኳታር መንግሥት ሚሳዔሎቹን ከማስወንጨፏ በፊት ያሳወቀች ሲሆን ይህንንም ትራምፕ ኢራን ነገሮችን ማባባስ ሳይሆን አቻነትን ነው የምትፈልገው ሲሉ እውቅና ሰጥተውታል።

ትራምፕ ቀናቸውን ያሳለፉት የነዳጅ ዋጋን፣ የአሜሪካ የሚዲያ ሽፋን እና የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የውጭ አገር ለኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ይሰጣል ማለታቸውን ሲከታተሉ ነው።

የአሜሪካ ባለስልጣናት እንዳሉት እኚህ ፕሬዝደንት ከአንዳንድ የቀድሞ መሪዎች በተቃራኒ ማስጠንቀቂያዎቻቸውን በሚገባ ይገመግማሉ።

ኢራን ሌላ ዙር ጥቃት ብትፈጽም እና አሜሪካዊ ቢሞት ወይም ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስ ትራምፕ ምላሽ እንዲሰጡ ግፊት ይጨምርባቸዋል።

ለጊዜው ግን የፍልሚያ መንገዱን የተዉ ይመስላል፤ እና ሁለቱም አገራት እሱን መከተል የመረጡ መስለዋል።