ኢራን ከእስራኤል ጋር ባላት ግጭት ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ ሌላ ወዳጇን እንዳታጣ ትሰጋለች

ቭላድሚር ፑቲን እና የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም ስትጀምር የሩሲያ ባለሥልጣናት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ "አሳሳቢ" እና "አደገኛ" ሲሉ ነበር የገለፁት።

አሁንም ቢሆን የሩሲያ ሚዲያዎች የሁለቱ አገራት ግጭት ለሞስኮ ያለውን አዎንታዊ ውጤት አጽንኦት ሰጥተው በመናገር ላይ ናቸው።

ከእነዚህም መካከል የሩሲያን ካዝና ያደልባል ተብሎ የተገመተው የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከከፈተችው ጦርነት የዓለም አቀፋዊ ትኩረት መከፋፈል እንዲሁም ክሬምሊን ግጭቱን የማሸማገል እድል ካገኘች በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተች ቢሆንም ራሷን በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ እንደ ቁልፍ ተዋናይ እና እንደ ሰላም ፈጣሪነት ራሷን ማሳየት የሚሉ ናቸው።

ይኹን እንጂ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ በቀጠለ ቁጥር ሩሲያ ከወቅታዊ ክስተቶች የምታጣው ነገር እንዳለ እየተገነዘበች መጥታለች።

ሰኞ ዕለት የሩሲያ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አንድሬ ኮርቱኖቭ "የግጭቱ መባባስ ለሞስኮ ከባድ አደጋዎች እና ወጪዎችን ያስከትላል" ሲሉ ጽፈዋል።

"እውነታው ሩሲያ ከአምስት ወራት በፊት ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በተፈራረመችባት አገር ላይ እስራኤል የምታደርገውን ጥቃት መከላከል አለመቻሏ ነው።

"ሞስኮ እስራኤልን ከመውቀስ እና ፖለቲካዊ መግለጫዎችን ከማውጣት ያለፈ ለኢራንን ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ አይደለችም" ብለዋል ።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቭላድሚር ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን የተፈራረሙት የሩሲያ ኢራን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት ወታደራዊ ጥምረትን አያካትትም።

ስለዚህ ሞስኮ ቴህራን እንድትከላከል አያስገድዳትም። በዚያን ጊዜ ግን ሞስኮ ይህንን ጉዳይ አንስታው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከሪያ ኖቮስቲ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ስምምነቱ "በክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎች ሰላም እና ደህንነትን ለማስጠበቅ እና ሞስኮ እና ቴህራን በፀጥታ እና በመከላከያ ላይ የበለጠ ትብብር ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል" ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ሞስኮ በመካከለኛው ምሥራቅ አንድ ቁልፍ አጋሯን አጥታለች፤ ባሽር አል አሳድን።

ባለፈው ታህሳስ ወር የሶሪያው መሪ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በሩሲያ ጥገኝነት ጠይቀዋል።

በኢራን ውስጥ ያለው የስርዓት ለውጥ ተስፋ ፣ በክልሉ ውስጥ ሌላ ስትራቴጂካዊ አጋር የማጣት ሀሳብ፣ ለሞስኮ ትልቅ ስጋት ይኖረዋል።

ሞስኮቭስኪ ኮምሶሞሌትስ ማክሰኞ ዕለት በመካከለኛው ምስራቅ ስለተከሰቱት ለውጦች አስተያየት ሲሰጡ "በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ የሚታዩት ትልቅ ለውጦች አገራችንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይነካል" ብለዋል።