የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ትራምፕ ስለ ሰላም እያደረጉት ላለው ጥረት እናመሰግናለን ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ

ማሪያ ኮሪና ማቻዶ
የምስሉ መግለጫ, ማሪያ ኮሪና ማቻዶ

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት የቬንዚዌላ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በዓለም ዙሪያ ለሰላም" እያደረጉ ላለው ተግባር አመስጋኝ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

የቬንዙዌላ ተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ የሆኑት ማቻዶ በአብዛኞች ዘንድ የ12 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው እንደ ሕገወጥ የሚቆጠረውን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ሞሮስ ን በመቃወም ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

የ2025 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ፖለቲከኛዋ ከቢቢሲ ሙንዶ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መሸለማቸውን ካወቁ በኋላ ከትራምፕ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ወቅት "የቬንዙዌላ ሕዝብ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ለሰላም፣ለነፃነት እና ለዲሞክራሲ እያደረጉ ላለው ነገር አመስጋኝ ነው" በማለት እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

ትራምፕ ሰባት ጦርነቶችን አስቁሜያለሁ በማለት በተደጋጋሚ ሽልማቱን ይገባኛል ሲሉ በይፋ ይናገሩ ነበር።

ትራምፕ ሁለተኛ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን በጥር ወር እንደጀመሩ ለኖቤል የሰላም ሽልማት የሚደረገው ምርጫ አብቅቷል።

አርብ ዕለት አንድ የዋይት ሐውስ ባለስልጣን "የኖቤል ኮሚቴ ፖለቲካን ከሰላም በላይ እንደሚያስቀምጥ አረጋግጧል" ብለዋል።

ማቻዶ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት በማነጋገራቸው "በጣም ደስ ብሎኛል" ያሉ ሲሆን "አድናቆታችንን ማስተላለፍ ችያለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

የ58 ዓመቷ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ላለፈው አንድ ዓመት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ተደብቀው ለመኖር ተገድደዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኖቤል ኮሚቴ "በቅርብ ጊዜ በላቲን አሜሪካ ከታዩት በግለሰቦች የተፈጸሙ የጀግንነት ምሳሌዎች አንዱ ነው" ሲል የማቻዶን ተግባር አሞካሽቷል።

የኖቤል ሊቀ መንበር ጆርገን ዋትን ፍሬድነስ "ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ሽግግርን ለማምጣት ባደረጉት ትግል" ዐዕውቅና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

አክለውም "በሕይወቷ ላይ ከባድ ዛቻ ቢደርስባትም በአገሯ ውስጥ ቆይታለች፤ ይህም ምርጫዋ ሚሊዮኖችን አነሳስቷል።"

ማቻዶ ባለፈው ዓመት በተካሄደው እና ማዱሮ ለሦስተኛ ጊዜ ባሸነፉበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እንዳይወዳደሩ ተከልክለዋል።

ምርጫው በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ነጻም ፍትሃዊም አልነበረም በሚል በስፋት ውድቅ የተደረገ ሲሆን በመላ አገሪቱ ተቃውሞ አስነስቷል።

በምርጫ እንዳይሳተፉ ከታገዱ በኋላ በከፋ ሁኔታ የተከፋፈለውን የአገሪቱን የተቃዋሚ ቡድን አንድ በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቬንዙዌላውያንን ብዙም ታዋቂ ያልነበሩት ኤድመንዶ ጎንዛሌዝ እንዲደግፍ ማድረግ ችለዋል።

ምንም እንኳን ከምርጫ ጣቢያዎች የተገኘው ውጤት ጎንዛሌዝ በከፍተኛ ድምፅ ማሸነፋቸውን ቢያሳይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ ምክር ቤት ማዱሮን አሸናፊ ብሎ ሲያውጅ፤ ማቻዶ ከተደበቁበት በመሆን የማዱሮ መንግሥትን መቃወማቸውን ቀጥለዋል።

ማቻዶ ለቢቢሲ ሙንዶ ሽልማቷ ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴዋ "እንደ ክትባት" እንደሆናቸው ተናግረዋል።

"በቬንዝዌላ ሕዝብ ላይ ኃይልን ይሰጣል፣ ተስፋን፣ ጥንካሬን ያላብሳል" ሲሉ ገልጸውታል።

"በዓለም ዙሪያ ያሉ ዲሞክራቶች ትግላችንን ይጋራሉ" ሲሉም አክለዋል።

ትራምፕ እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቬንዙዌላ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ እየረዱ ነው ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

"በቬንዙዌላ ያለው አገዛዝ የወንጀል መዋቅር ነው" ያሉት ማቻዶ "እናም በዚሁ የሕገወጥ ተግባራቸው በወንጀል ፍሰቶች ራሳቸውን ማቆየት ችለዋል" ሲሉ የአገሪቱን መንግሥት ወንጅለዋል።

"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሙስና ብቻ ሳይሆን ለጭቆና፣ ለአመፅና ለሽብር ተግባር የሚውሉትን ፍሰቶች እንዲያስቆም እንፈልጋለን። ስለዚህ ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ ከወርቅ ንግድ፣ ከጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ከጥቁር ገበያ የሚገኘውን የነዳጅ ዘይት ግብይት ሲቋረጥ አገዛዙ ይወድቃል።"

"እናም እያየን ያለነው ያ ነው፤ አሁን እየተነጋገርን እንኳ ጥልቅ እየሆነ እና ጥልቀት እየጨመሩ ይሄዳል።"

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ጦር በቬንዙዌላ የባሕር ዳርቻ ላይ አደንዛዥ ዐዕጾችን ታዘዋውራለች በተባለች ጀልባ ላይ ባደረሰው ጥቃት አራት ሰዎች ተገድለዋል።

በቅርቡ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ውሃ ላይ በጀልባዎች ላይ በፈጸመችው ጥቃት "የሕገወጥ አደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን" ዒላማ ማድረጓን ትናገራለች።

ቬንዙዌላ እና ኮሎምቢያ የአሜሪካን እርምጃ የተቃወሙ ሲሆን አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ጥቃቱን የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ሲሉ ገልፀውታል።

ሐሙስ ዕለት የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ከጀልባዎቹ አንዱ "የኮሎምቢያ ዜጎችን አሳፍራ ነበር" ያሉ ሲሆን ዋይት ሐውስ "መሠረተ ቢስ" ሲል አጣጥሎታል።