ቬኔዙዌላዊቷ ፖለቲከኛ ማሪያ ኩሪና ማቻዶ የትራምፕን ተስፋ በማጨናገፍ የኖቤል ተሸላሚ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቬኔዙዌላዊቷ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ የ2025 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።
የቬንዝዌላ ተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ የሆኑት ማሪያ ኮሪና ማቻዶ በአገራቸው ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማቀንቀናቸው እና አገራቸው ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር እንድታደረግ በመታገላቸው የዚህ ዓመት የኖቤል ሽልማትን ማሸነፋቸውን ኮሚቴው አስታውቋል።
የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዋ ማቻዶ፣ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ሽልማቱ እንደሚገባቸው ቢናገሩም፣ በአገራቸው ያለውን አምባገነን መንግሥት በመታገላቸው ለሽልማት መብቃታቸው ተገልጿል።
የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢው ፖለቲከኛዋ ማሸነፋቸውን ሲገልጹ፣ በ2025 የኖቤል የሰላም ሽልማት "እየጨመረ በመጣው ጨለማ ውስጥ የዴሞክራሲን ነበልባል ለምታስቀጥል ሴት" መሰጠቱን ተናግረዋል።
"አምባገነኖች ሥልጣን ሲይዙ ተነስተው የሚገዳደሩ ልበ ሙሉ የነጻነት ጠበቃዎችን ዕውቅና መስጠት ይገባል" ሲሉም አክለዋል።
ኮሚቴው ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በላቲን አሜሪካ ካሉት እጅግ "የተለዩ ተምሳሌቶች" አንዷ በመሆን የኖቤል የሰላም ሽልማትን መሸለናቸውን ገልጿል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ በንግግራቸው ላይ ማቻዶ "ዋና የአንድነት ምሳሌ ሆና ቆይታለች" ብለዋል።
"በዲሞክራሲ ማዕከላዊነት ላይ የተቀመጠው ይህ ነው። ባንስማማም እንኳን በሕዝብ የበላይነት መመራት አለበት የሚለውን መርሆዎ ለመከላከል ያለን ፍላጎት ነው።ዴሞክራሲ አደጋ ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት ይህንን የጋራ አቋም መከላከል ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ነው።"
የ58 ዓመቷ ኢንጂነር፣ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ በፍርድ ቤት ታግደዋል።
ምርጫው በዓለም አቀፍ ደረጃ ነፃም ሆነ ፍትሃዊም አይደለም በሚል ውድቅ ተደርጓል።
ምንም እንኳ በምርጫው እንደሚያሸንፉ ትንበያዎች ቢያሳዩም እንዳይሳተፉ በመደረጉ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆነው በሥልጣን ላይ ቀጥለዋል።
ከምርጫ ውጤት በኋላ በመላ አገሪቱ የተቃውሞ ሠልፎች የተካሄዱ ቢሆንም መንግሥት ግን ሙሉ በሙሉ መቆጣጣር እና ዝም ማሰኘት ችሏል።
በማዱሮ በዓለ ሲመት ዕለት በተዘጋጀ ሰልፍ ላይ ለጥቂት ጊዜ የታዩት ማቻዶ፣ ከዚያ በኋላ ግን እስከዛሬ ድረስ ተደብቀው ይገኛሉ።
ለአጭር ጊዜ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዋ ወዲያው ተለቅቀዋል።
ማቻዶ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፋቸውን በተደበቁበት ሆነው ሲሰሙ " በጣም ደንግጫለሁ. . . በደስታ ብዛት ደንግጫለሁ" ብለዋል።
የዋይት ሐውስ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ስቴቨን ቼኡንግ ትራምፕ "የሰላም ስምምነቶችን ማድረግ፣ ጦርነቶችን ማስቆም እና ሕይወቶችን ማዳናቸውን ይቀጥላሉ" ብለዋል።
ቼኡንግ "ለሰብዓዊነት ልብ አላቸው፣ እንዲሁም እንደርሱ ያለ በፈቃዱ ተራራን ማንቀሳቀስ የሚችል ማንም የለም፥ የኖቤል ኮሚቴ ከሰለም ይልቅ ፖለቲካን እንደሚያስቀድም አረጋግጧል" ሲሉ ጽፈዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ሥልጣናቸውን ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ ለኖቤል የሰላም ሽልማት በበርካታ አገራት መሪዎች ዕጩ ተደርገው ተመርጠዋል።
ይሁን እንጂ ተሸላሚ ዕጩዎችን ማቅረቢያ ጊዜው የሚያበቃው ጥር 31 በመሆኑ በዚህ ዓመት ምርጫ ላይ ሊካተቱ አይችሉም ማለት ነው።
የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ማቻዶ ለነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ፣ ከጠብ መንጃ ይልቅ በምርጫ ሳጥን ሥልጣን እንዲገኝ ከ20 ዓመት በፊት መታገል መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አክለውም ለነጻነት ስትሰራ ዓመታትን አሳልፋለች ብለዋል።
ኮሚቴው "ለቬንዙዌላ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማስፈን እና ፍትሃዊ እና ሰላማዊ፤ ከአምባገነንነት ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ባደረገችው ትግል" ማሪያ ኮሪና ማቻዶ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንደሰጣት በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የኖቤል ኮሚቴ በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ ሽልማቱ ይገባኛል ሲሉ የነበሩትን የአሜሪካው ፕሬዚዳንትን በመተው ቬንዚዌላ ላይ ማተኮር መርጧል።
የኖቤል ሰላም ሽልማት አሸነፊ ከሜዳሊያ እና ምስክር ወረቀት ባሻገር 11 ሚሊዮን የሲውዲን ክሮነር (1.2 ሚሊዮን ገደማ) ተሸላሚ ይሆናል።
የኖቤል ሽልማት በሲውዲናዊው የፈጠራ ባለሙያ፣ ሳይንቲስት፣ የንግድ ሰው አልፍሬድ ኖቤል ነው የተመሰረተው።
የኖቤል አሸናፊዎች ሽልማት ሥነ ስርዓት የሚካሄደው አልፍሬድ ኖቤል በ1896 በሞተበት ቀን ታሕሳስ 10 (ዴሴምበር 10) ይሆናል።















