የኖቤል ሽልማት ምንድን ነው? እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, SOREN ANDERSSON/AFP/GETTY IMAGES
በተለያዩ መስኮች ፈር ቀዳጅ ተግባራትን ያከናወኑ ግለሰቦችንን እና ተቋማትን በየዓመቱ የሚሸለሙበት የኖቤል ሽልማት በዓለማችን ከሚሰጡ ዕውቅናዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
የኖቤል ሽልማት በስድስት የተለያዩ ዘርፎች ተከፋፍሎ የሚሰጥ ሲሆን አሸናፊዎቹ በየዓመቱ በመስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት ላይ ስዊዲን፣ ስቶክሆልም በሚገኘው የኖቤል ፋውንዴሽን ይገለጻሉ።
አልፍሬድ ኖቤል ኅዳር 18/1888 ዓ.ም በፈረመው ኑዛዜ ያለውን አብዛኛውን ሃብቱን የኖቤል ሽልማት ተብለው ለሚሰጡ ሽልማቶች እንዲውል ተናዟል።
በኑዛዜው ላይ እንደተገለጸው ከዚህም መካከል አንዱ የሠላም ሽልማት ሲሆን፤ ሽልማቱም "በመንግሥታት መካከል ወንድማማችነት እንዲሰፍን አብዝተው ወይም የተሻለ ሥራን ላከናወኑ፣ የጦር ሠራዊቶች ቅነሳና ለሠላም መስፋፋት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ይሰጥ" ይላል።
እአአ በ1901 ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 1,000 ሰዎች እና ድርጅቶች የኖቤል ሽልማትን አሸንፈዋል።
ከእነዚህም መካከል ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አይንስታይን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ማላላ ዮሳፍዛይ ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለዚህ ሽልማት የበቁት ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መውሰድ በጀመሯቸው እርምጃዎችና በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, EMIL OSTERMAN/GETTY
ኖቤል ሽልማት ምንድን ነው?
የኖቤል ሽልማት በሲውዲናዊው የፈጠራ ባለሙያ፣ ሳይንቲስት፣ የንግድ ሰው አልፍሬድ ኖቤል ነው የተመሰረተው።
አልፍሬድ እአአ በ1833 የተወለደ ሲሆን የበለጠ የሚታወቀው የድማሚት ፈንጂ በመስራቱ ነው።
ስድስት ቋንቋዎችን ይናገር የነበረው አልፍሬድ ግጥም መጻፍ ያስደስተው ነበር።
355 የፈጠራ ባለቤትነት ምስክር ወረቀት ያገኘባቸው የፈጠራ ስራዎች አሉት።
አልፍሬድ ኖቤል ሰዎች ዓለምን በእውቀት፣ በሳይንስ እና በርህራሄ የተሻለ የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ አቅም አላቸው ብሎ ያምናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አልፍሬድ በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቹ የተነሳ የናጠጠ ሃብታም የነበረ ሲሆን እአአ በ1895 ሲሞት አብዛኛው ገንዘቡ "በባለፈው ዓመት ለሰው ልጅ ከፍተኛ ጥቅም ላበረከቱ ሽልማት" እንዲሰጥ ሲል ተናዝዟል።
እአአ በ1901 የመጀመርያው የኖቤል ሽልማት ተሰጥቷል።
ሽልማቱ የተጀመረው በአምስት ዘርፎች፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ሕክምና/ሥነ ልቡና፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሰላም በሚል ተከፋፍሎ ነበር።
እአአ በ1968 የኢኮኖሚክ ሳይንስ የመታሰቢያ ሽልማት ተጨምሯል።
የኖቤል ሽልማትን የሚያሸንፍ ምን ያገኛል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች የአልፍሬድ ኖቤል ምስል የተቀረጸበት የወርቅ ሜዳሊያ፣ ስኬታቸው የተዘረዘረበት የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ሽልማት ያገኛሉ።
የገንዘቡ መጠን 11ሚሊዮን የስዊዲን ክሮን (1,156,395 ሚሊዮን ዶላር) ሲሆን ሽልማቱን ከአንድ በላይ ሰው የሚያሸንፍ ከሆነ ገንዘቡ እኩል የሚካፈሉት ይሆናል።
የኖቤል አሸናፊዎች ሽልማት ሥነ ስርዓት የሚካሄደው አልፍሬድ ኖቤል በ1896 በሞተበት ቀን ታሕሳስ 10 (ዴሴምበር 10) ይሆናል።
የኖቤል ሽልማትን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎች፣ ከዚህ ቀደም ያሸነፉ ግለሰቦች ወይንም ድርጅቶች እና ምሁራን ለቀጣዩ ዓመት የኖቤል ሽልማት መሸለም አለበት ብለው የሚያስቡትን እንዲመርጡ ይጠየቃሉ።
የሚመርጡትን ሰው ስም በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥር 31 ድረስ ማስገባት አለባቸው።
እነዚህ ባለሙያዎች ከተለያዩ አገራት እና ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ በመሆናቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኝን ሰፊ ዕይታን ለመወከል ይረዳሉ።
ለተለያዩ ዘርፎች ኃላፊነት የተሰጣቸው የኖቤል ኮሚቴዎች ሁሉንም እጩዎች ከተቀበሉ በኋላ አሸናፊዎቹን ከመምረጣቸው በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዕጩዎችን ለወራት አንዳንዴም ለዓመታት በመገምገም ያሳልፋሉ።
እጩዎቹ በግል የሚቀርቡ ሲሆን ለ50 ዓመታት የቀረቡ እጩዎች እና ማን እንደጠቆማቸው በይፋ እንዳይገለፁ ተከልክሏል።
ነገር ግን ያጨው ግለሰብ ወይም ተቋም ከፈለገ የመረጠውን ሰው ወይም ድርጅት መግለጽ ይችላል።
አንድ ሰው ራሱን ለኖቤል ሽልማት ማጨት አይችልም።
የኖቤል ሽልማትን እነማን አሸንፈው ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የምትጥረው ፓኪስታናዊቷ ማላላ ዩሳፍዛይ እንደ አውሮፓዊያኑ በ2014 የተሰጠውን የኖቤል የሠላም ሽልማትን በ17 ዓመቷ በማግኘት በዕድሜ ትንሿ የሽልማቱ አሸናፊ ሆናለች።
እአአ በ2019 በ97 ዓመታቸው የኖቤል ሽልማት የተቀበሉት አዛውንቱ ጆን ቢ ጎዴንኦህ ናቸው።
እኚህ አዛውንት የኬሚስትሪ ምሁር የነበሩ ሲሆን "ሊቲየም-አየን ባትሪዎችን በማበልጸጋቸው" መሸለማቸው ተገልጿል።
በትውልድ ፖላንዳዊ በዜግነት እንግሊዛዊ የሆኑት ጆሴፍ ሮትብላት የኑክሌር ጦር መሳሪያ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ተጽእኖ ለመቀነስ ባበረከቱት አስተዋጽኦ እንደ አውሮፓዊያኑ በ1995 የኖቤል የሠላም ሽልማትን ሲያገኙ እድሜያቸው 87 ነበረ።
የኖቤል የሰላም ሽልማትን ካሸነፉ ታዋቂ ሰዎች መካከል ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ይገኝበታል።
ማርቲን ሉተር እአአ በ1964 ያሸነፈ ሲሆን "ለአፍሪካዊያን አሜሪካውያን ሕዝቦች የሲቪል መብቶች እንዲከበር ባደረገው ሰላማዊ ትግል" ሽልማቱን ማግኘቱ በወቅቱ ተገልጿል።
አልበርት አይንስታይን እአአ በ1921 በፊዚክስ ዘርፍ "በቲዮሬቲካል ፊዚክስ መስክ ላበረከተው አስተዋጽኦ እና በተለይ የፎቶኤሌትሪክ ሕግ በማግኘቱ " መሸለሙ ተገልጿል።
ጥቂት ሰዎች የኖቤል ሽልማትን ከአንድ ጊዜ በላይ አሸንፈዋል።
ታዋቂዋ ሳይንቲስት ማሪያ ኩሪ እአአ በ1903 በፊዚክስ ዘርፍ ከባለቤቷ ፔር ኩሪ እና ሄንሪ ቤክኳዋረል "ራዲዮአክቲቪቲ" ላይ ቲዎሪ በማዳበር ፈር ቀዳጅ ስራ ስለሰሩ ተሸልመዋል።
እአአ በ1911 ለሁለተኛ ጊዜ በኬሚስትሪ ዘርፍ ፖሎኒየም እና ራዲየም የተሰኙ ኤለመንቶችን በማግኘቷ ተሸላሚ ሆናለች።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በዓለም ዙሪያ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ከየትኛው ተቋም በላይ በኖቤል ሠላም ሽልማት ዘርፍ እውቅናን አግኝቷል።
ቀይ መስቀል ሦስት ጊዜ ሽልማቱን በመውሰድ ቀዳሚ ሲሆን መስራቹ ሄንሪ ዱና ደግሞ የመጀመሪያውን የኖቤል የሠላም ሽልማትን በመውሰድ ይታወቃል።
የሠላም ሽልማቱን አልቀበልም ያለው ግለሰብ
ቬትናማዊው ፖለቲከኛ ሊ ዱች ቶ በአውሮፓዊያኑ 1973 ከአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በጋራ የኖቤል የሠላም ሽልማትን ቢያሸንፉም ሽልማቱን አልቀበልም በማለት የመጀመሪያው ለመሆን በቅተዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች ለሽልማቱ የተመረጡት የቬትናም የሠላም ስምምነት እንዲደረስ ጉልህ ሚና በመጫወታቸው ነው። ሊ ዱች ቶ የኖቤል የሠላም ሽልማቱን አልቀበልም ያሉት በወቅቱ ቬትናም ውስጥ የነበረውን ሁኔታ እንደምክንያት ጠቅሰው ነው።















