ሁሉም ሰው ተጨማሪ ቫይታሚን መውሰድ አለበት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምግብ ውስጥ በቂ ቫይታሚን ሳይኖር ሲቀር ተጨማሪ ቫይታሚን መውሰድ ይመከራል። ሆኖም ሁሉንም ችግር ይቀርፋል ማለት አይደለም።
የተጨማሪ ቫይታሚን እና ሚኒራል ገበያ 32.7 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። 74 በመቶ ተጠቃሚዎች አሜሪካውያን ናቸው።
የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ሁለት ሦስተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
አንዳንድ ጥናቶች እነዚህ ተጨማሪ ቫይታሚኖች እና ሚኒራሎች እምብዛም ጥቅም የላቸውም ሲሉ፣ እንዲያውም ይጎዳሉ ብለው የሚከራከሩም አልታጡም።
ለመሆኑ ሁሉም ሰው ተጨማሪ ቫይታሚን መውሰድ አለበት? ጥቅሙስ ምንድን ነው?
ተጨማሪ ቫይታሚንና ሚኒራል መውሰድ ምን ይጠቅማል?
ተጨማሪ ቫይታሚን እና ሚኒራል ወይም በእንግሊዝኛው 'vitamin and mineral supplements' የሚወስዱ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።
ሁለቱን ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን አያመርትም። ሆኖም ለጤና ጠቃሚ ናቸው።
ሰውነታችን የማያመርታቸውን ንጥረ ነገሮች ከምግቦች እናገኛለን። ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ሲ እና ቫይታሚን ኬ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው።
ቫይታሚን ኤ ለዕይታ እና ለጤናማ ቆዳ ይረዳል። ቫይታሚን ሲ በሽታ የመከላከል አቅምን ያጠነክራል። ቫይታሚን ኬ ደም እንዳይረጋ ያግዛል።
ካልሽየም፣ ማግኒዢየም፣ ፖታሽየም የምናገኘውም ከምግብ ነው።
ቫይታሚን እና ሚኒራል ለሰውነታችን የሚያስፈልገው ከካርቦሃይድሬት፣ ከፕሮቲን እና ከስብ ባነሰ መጠን ነው።
ማንኛውም ተጨማሪ ቫይታሚንም ይሁን ሚኒራል ጤናማ አመጋገብን አይተካም።
ሰውነት የሚያስፈልገውን ለማሟላት አትክልት እና ፍራፍሬ፣ ለውዝ፣ ዓሣ፣ ሥጋ እና ሌሎችም ምግቦች የግድ ያስፈልጋሉ።
ፈጣን ምግቦች እና የተብላሉ ምግቦች መበራከት ጤናማ የቤት ምግብ እንዳይዘወተር ምክንያት ሆነዋል።
ፕሮፌሰር ቤስ ዳወሰን-ሀግስ በአሜሪካ በተፍስ ዩኒቨርስቲ የግብርና እና ሥነ ምግብ ተመራማሪ ናቸው።
አብዛኞቹ አሜሪካውያን በሳይንስ ከሚመከረው አትክልት እና ፍራፍሬ ግማሹን እንደሚመገቡ ይናገራሉ።
ለሰውነት ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ከምግብ ያላገኙ ሰዎች በተጨማሪ ቫይታሚን እና ሚኒራል ለማካካስ ይሞክራሉ።
ምን ያህል ክፍተቱን ይሞላል? ለሚለው ቀጥተኛ መልስ የለውም።
በ1970ዎቹ የኖቤል ተሸላሚው ላይነስ ፓውሊንግ ቫይታሚን ሲ አብዝቶ መውሰድ ጉንፋንን ጨምሮ የመተንፈሻ አካላት ሕመም፣ የልብ ሕመም እና ካንሰርንም ሳይቀር ያድናል ብለው ይከራከሩ ነበር።
ከጉንፋን ውጪ ያሉ ሕመሞች ቫይታሚን ሲን በማብዛት እንደማይድኑ ሳይንስ ቢያረጋግጥም ብዙዎች አሁንም ድረስ በመላ ምቱ ያምናሉ።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከ500 በመቶ እስከ 1,000 በመቶ እጥፍ ተጨማሪ ንጥረ ነገሮች መውሰድን ያስተዋውቃሉ።
ቫይታሚን እና ሚኒራል እጅግ በተጋነነ ሁኔታ መጠቀም አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
ቫይታሚን ዲ በብዛት ወስደው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው።
ውሃ ጥማት እና ቶሎ ቶሎ መሽናት የቫይታሚን ዲ መብዛት ምልክት ሲሆኑ ኮማ ውስጥ እስከመግባት እና እስከ ሞትም ያደርሳል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ጤና ተቋም ቫይታሚን ኤ ማብዛት ራስ ምታት፣ የዕይታ መዛባት፣ ማቅለሽለሽ፣ የጡንቻ ሕመም እንደሚያስከትል ይገልጻል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫይታሚን እና ሚኒራል ላይ የተሠሩ ጥናቶች
ቫይታሚን እና ሚኒራል ላይ የተሠሩ ጥናቶች የሚቃረኑ ውጤቶች አስገኝተዋል።
ይህ ማለት ደግሞ ተጨማሪ ቫይታሚን እና ሚኒራል በመውሰድ የሚገኘው ጥቅም እንደየሰዉ ይለያያል ማለት ነው።
'ፍሪ ራዲካልስ' የሚባሉ ጎጂ ኬሚካሎችን የሚያከስሙ አንቲኦክሲደንትስ ላይ ጥናቶች ተደርገዋል።
ፍሪ ራዲካልስ ሕዋስን የሚበጣጥሱ እና ዘረ መልን የሚጎዱ ናቸው።
ይሄንን ጉዳት ለመቀነስ አንቲኦክሲደንትስ መውሰድ ይጠቅማል ተብሎ ቢታመንም የተሳሳተ ምልከታ መሆኑ በጥናት ተደርሶበታል።
በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሕብረተሰብ ጤና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጆአን ማንሰን የመሩት ጥናት አንቲኦክሲደንት የሆኑት ቫይታሚን ሲ እና ቫይታሚን ካንሰር እና የልብ ሕመምን እንደማይገቱ ያሳያል።
'አንቲኦክሲደንትስ' አብዝቶ መውሰድ ጤና እንደሚጎዳ ያሳዩ ጥናቶችም ይጠቀሳሉ።
በተለይም ሲጋራ አጫሾች ለሳምባ ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው እንዲጨምር ያደርጋሉ።
ቫይታሚን ኢ ማብዛት ስትሮክ ሊያስከትል እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ፕሮፌሰር ጆአን "ቫይታሚን ኢ ደም ያቀጥናል። የደም መርጋትን ስለሚያስቆም ደም ወደ አንጎል እንዲፈስ ሊያደርግ ይችላል። አንቲኦክሲደንት አብዝቶ መውሰድ የኦክስዴሽን መጠንን ሊጨምርም ይችላል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫይታሚን ዲ ምን ይጠቅማል?
አንድ ንጥረ ነገር ብቻ አብዝቶ መውሰድ ሌሎች ንጥረ ነገሮች የመውሰድ አቅምንም ያዳክማል።
በቀን ከሚመከረው በላይ አንቲኦክሲደንት መውሰድ ጤናማ አይደለም።
ጤናማ አጥንት እንዲኖረን የሚያግዘው ቫይታሚን ዲ እንደ ሌሎቹ ቫይታሚኖች አይደለም።
ብዙዎች ቫይታሚን ዲ በብዛት አያገኙም።
በቂ ፀሐይ እስካገኘን ድረስ ሰውነታችን ቫይታሚን ዲ ያመርታል። ከምግብ ሊገኝም ይችላል።
የፀሐይ ብርሃን በብዛት በማይገኝባቸው በምዕራባውያን አገራት ቀዝቃዛ ወቅቶች ተጨማሪ ቫይታሚን ዲ መውሰድ ይመከራል።
25 ሺህ አሜሪካውያን በተሳተፉበት ጥናት እንደታየው፤ ተጨማሪ ቫይታሚን ዲ ወይም ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ መውሰድ የካንሰር፣ የልብ ሕመም እና ስትሮክ ተጋላጭነትን ይቀንሳል።
ተጨማሪ ቫይታሚን ዲ መውሰድ ሕመሞቹን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ማለት አይደለም።
እንዲያውም ቫይታሚኖችን ብቻ ለሁለት ዓመታት የወሰዱ ሰዎች በካንሰር የመሞት ተጋላጭነት ወደ 25 በመቶ እንዲሁም ለተባባሰ የካንሰር ደረጃ የመጋለጥ ዕድል ወደ 17 በመቶ ወርዶ ታይቷል።
ፕሮፌሰር ጆአን "ቫይታሚን ዲ የዕጢ ሕዋስ ብዙም እንዳይጎዳ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ካንሰርን ለመዋጋት አይረዳም" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰውነት ጤናማ ሕዋሳት አደገኛ ናቸው ብሎ ተሳስቶ ሲዋጋቸው የሚፈጠሩ ሕመሞችን (autoimmune disease) ለመከላከል ቫይታሚን ዲ ሚናው ቀላል አይደለም።
ተጨማሪ የቫይታሚን ዲ እንክብል መውሰድ በተለይም ለአዛውንቶች የአጥንት መሰንጠቅን ይከላከላል።
በ2000 በፈረንሳይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው በአዛውንቶች መንከባከቢያ ውስጥ የሚኖሩ አረጋውያን ሴቶች በቫይታሚን ዲ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ከዚህ በተቃራኒው ቫይታሚን ዲ መውሰድ የአጥንት መሰንጠቅን የመከላከል ዕድሉ አነስተኛ ነው የሚሉ የጥናት ውጤቶችም ይፋ ሆነዋል።
ፕሮፌሰር ቤስ "ጥናቶቹ አነስተኛ ቫይታሚን ዲ ያላቸው አዛውንቶች ላይ አልተሠሩም። የተሠሩትም የቫይታሚን ዲ ጠቀሜታ ተጋኖ በሚነገርበት ወቅት ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫይታሚን እና ሚኒራልን ጨምሮ ሌሎችም ንጥረ ነገሮች በማዋሃድ የሚሠራው ተጨማሪ እንክብል (multivitamin) በአዛውንቶች ላይ አወንታዊ ለውጥ አሳይቷል።
ፕሮፌሰር ጆአን ጥናት መሥራት የጀመሩት ከ20 ዓመት በፊት ነው።
በጥናታቸው እንዳገኙት ለ11 ዓመታት እነዚህን እንክብሎች የወሰዱ ሰዎች ላይ እንደታየው ከሆነ በካንሰር የመያዝ ዕድልን 8 በመቶ ይቀንሳሉ።
ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች የካንሰር ተጋላጭነት በ18 በመቶ ቀንሷል።
"አዛውንቶች አመጋገባቸው ውስን ስለሆነ ይሆናል ይሄ ውጤት የተገኘው" ይላሉ ፕሮፌሰር ጆአን።
ፕሮፌሰር ቤስ በ2023 በሠሩት ጥናት በየቀኑ መልቲቫይታሚን የወሰዱ ሰዎች በሦስት ዓመታት ውስጥ የአእምሮ ክህሎት መዳከም ችግርን 60 በመቶ መቀነስ ችለዋል።
ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ እንደ ካንሰር እና መዘንጋት ያሉ ችግሮችን በመቀነስ ረገድም ውጤት አግኘተዋል።
ቫይታሚን መውሰድ ያለበት ማነው?
ፕሮፌሰር ቤስ እና ፕሮፌሰር ጆአን እንደሚሉት፣ በርካቶች ተጨማሪ ቫይታሚን መውሰድ የለባቸውም። ጤናማ እና የተመጣጠነ አመጋገብ የተሻለው አማራጭ ነው።
የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ጤና ተቋማት ነፍሰ ጡሮች መልቲቫይታሚን እና ፎሊክ አሲድ እንዲወስዱ ይመክራሉ።
እነዚህን ንጥረ ነገሮች ማግኘት ለጨቅላ ሕጻናት ጤናማ ዕድገት ይረዳል።
አትክልት ተመጋቢዎች እና ዓሣ የማይበሉ ሰዎች ኦሜጋ-3 ያለው የዓሣ ዘይት መውሰድ አለባቸው።
ሰውነት ቫይታሚንን በአግባቡ እንዳያብላላ የሚያግዱ ሕመሞች (Crohn's disease እና ulcerative colitis) ያሉባቸው ሰዎች ተጨማሪ ቫይታሚን ቢወስዱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንት የካንሰር እና የአእምሮ ክህሎት መዳከም ተጋላጭነትን ለመቀነስ በየቀኑ መልቲቫይታሚን እንዲወስዱ ይመከራል።
ሆኖም ግን ከሚፈለገው በላይ ቫይታሚን መውሰድ (mega-dosing) ተገቢ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።
ፕሮፌሰር ጆአን "መልቲቫይታሚን መውሰድ አይጎዳም። የተመጣጠነ ምግብ ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ክፍተት ያለባቸው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ቫይታሚን እና ሚኒራል ለማግኘት መልቲቫይታሚን እንክብል መውሰድ ይችላሉ" ይላሉ።















