ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ለተወሰኑ እቃዎች እና ሸቀጦች የውጭ ምንዛሪ እንዳይሰጥ ተወሰነ

የተለያዩ ሸቀጦች

የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ አገራት ለሚገቡ በተወሰኑ እቃዎች እና ሸቀጦች ላይ ላልተወሰነ ጊዜ የውጭ ምንዛሬ እንደማይፈቅድ አስታወቀ።

ከእነዚህም መካከል ከረሜላዎች፣ ብስኩቶች፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ዊስኪ፣ ወይን፣ ቢራ፣ የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢሎች እና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ ሰው ሰራሽ ፀጉር፣ የውበት ወይም መኳኳያ እቃዎች ተካትተውበታል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በቁጥር 38 የሚሆኑ ሸቀጦች እና እቃዎችን ዝርዝር በማውጣት የውጭ ምንዛሬ እንዳይፈቅድላቸው ያሳለፈውን ውሳኔ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እንዲያደርግ በደብዳቤ አዟል።

በገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታው ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያትተው የዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብት ቀውስ በአገሪቱ ላይ እየፈጠረ ያለው ጫና እንዲሁም የዋጋ ግሽበት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውንም ችግር ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱንም አስታውሷል።

እነዚህንም እርምጃዎች ውጤታማ ለማድረግም የውጭ ምንዛሬ ለመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች፣ ለመድኃኒቶች እና የህክምና መሳሪያዎች እንዲውል ተወስኗል።

በተጨማሪም ከውጭ ገብተው በአገር ውስጥ እሴት ለሚጨመርባቸው ምርቶች የሚውሉ ግብዓቶችና የካፒታል ዕቃዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ጥቅም ላይ እንዲውል ውሳኔ መተላለፉም ተገልጿል።

ክልከላው የሚመለከታቸው

ከሰኞ ጥቅምት 07/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ እንዳይሰጡ ክልከላ የተጣለባቸው ከውጭ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሸቀጦች እና ምርቶች የሚከተሉት ናቸው።

ከረሜላዎች፣ ማስቲካዎችና ሌሎች ጣፋጭ ምርቶች፣ ቼኮሌት፣ ብስኩቶች እና ዋፈሮች፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎች እና የታሸጉ ፍራፍሬዎች፣ ከፍራፍሬ የተዘጋጁ ጃሞች፣ የድንች ጥብሶች፣ የአሳማ ሥጋ፣ የዶሮ ሥጋ፣ የተለያዩ የአሳ ምርቶች፣ የገበታ ጨው፣ የታሸጉ ውሃዎች፣ ለስላሳ መጠጦች እና አልኮል የሌላቸው መጠጦች ለምግብነት ከሚውሉ ውስጥ ይጠቀሳሉ።

እንዲሁም ዊሰኪ፣ ወይን፣ ቢራ እና ለሎች አልኮል መጠጦች በሙሉ፣ ሲጋራ፣ ከብርጭቆ የተዘጋጁ የመጠጥ መጠጫዎች፣ የሲጋራ መተርኮሻዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ሽቶዎች፣ የውበት ወይም የመኳኳያ ምርቶች፣ የሰው እና አርቴፊሻል ፀጉሮች፣ አርቴፊሻል ጌጣጌጦች፣ የተለያዩ የፀጉር ጌጣጌጦች፣ ባርኔጣዎች እና ኮፍያዎች፣ ሳሙናዎች፣ ርችቶች፣ ቦርሳ እና ዋሌቶች፣ አንዳንድ የቤት እና የቢሮ ዕቃዎች ተካተዋል።

ብስክሌቶች፣የተለያዩ መጫወቻ እቃዎች፣ የእጅ፣ የጠረጴዛ እና የግድግዳ ሰዓቶች፣ ዣንጥላዎች፣ ምንጣፎች፣ ከሴራሚክስ እና ፖርስሊን የተዘጋጁ የቤት እቃዎች፣ ጋዝ ላይተር፣ ልብስ ማሳያ አሻንጉሊቶች፣ የአበባ መያዣና ተመሳሳይ እቃዎች፣ የታተመ ስዕላዊ መግለጫ ያላቸው ካርዶች፣ የቀን መቁጠሪያ ካሌንደሮች፣ ሥዕሎች፣ አርቲፊሻል አበባዎች።

በተጨማሪም በኤሌክትሪክ ከሚሰሩት ውጪ የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢል እና ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች እና ሞተር ሳይክሎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ተከልክሏል። ነገር ግን ይህ ክልከላ በአገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ መኪኖች እና ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በኤሌክትሪክ የሚሰሩትን አይመለከትም።

ቀደም ያሉ እርምጃዎች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ባለፈው ሳምንት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የውጭ ምንዛሪ ግብይትን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አሳውቆ ነበር።

በዚህም በአገሪቱ እየተባባሰ ያለውን የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሕገወጥ መንገድ የሚካሄዱ የተለያዩ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ያላቸውን እርምጃዎችን አሳውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ የሚካሄዱ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር በጥቆማ ለሚተባበሩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው ወሮታ እንደሚከፍል አስታወቆ ነበር።

በዚህም በባንክ ከተፈቀደው በላይ የገንዘብ መጠን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን ለጠቆሙ ከተያዘው ገንዘብ 15 በመቶ፣ የውጭ አገር ገንዘብ ዝውውር ለሚጠቁሙ 15 በመቶ፣ ሕገወጥ ሐዋላን ለሚጠቁሙ 25 ሺህ ብር ወሮታ ብሔራዊ ባንክ እንደሚከፍል ገዢው አሳውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የወርቅ ኮንትሮባንድ ለሚጠቁሙ 15 በመቶ የወርቁን ዋጋ፣ የሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ህትመትን ለሚጠቁሙ ከ20 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ ወሮታ እንደሚከፈልም ተገልጿል።

በተጨማሪም ከአገር ውስጥ ጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪን በመግዛት ከውጭ እቃ እያስገቡ ያሉትን ለመቆጣጠር፣ በፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ እቃ የሚያስመጡ ግለሰቦችና ተቋማት በውጭ አገር ያላቸውን የዶላር መጠን የሚያሳውቅ የባንክ ስቴትመንት ለብሔራዊ ባንክ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ እየጨመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የምንዛሪ ዋጋ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሁሉ ከፍተኛው ነው።

በዚህም በይፋዊው የባንኮች ግብይት የዶላር የምንዛሪ ዋጋ የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ 52 ብር አካባቢ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ በእጥፍ እንደሚመነዘር ይነገራል።