ዝነኛ የሆኑት ኡጋንዳውያን፡ ብሪቴይንስ ጎት ታለንት ማሸነፍ ‘በኡጋንዳ የትልቅ ቤት ባለቤት መሆን ነው’

Gheto kids

የፎቶው ባለመብት, Britain's Got Talent

ብሪቴይነስ ጎት ታላንት በተባለው ስመ ጥር የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለፍጻሜ በመድረስ የበርካታዎችን ቀልብ መግዛት የቻሉት ኡጋንዳውያን ታዳጊዎች፤ ውድድሩን ማሸነፍ በኡጋንዳ የትልቅ ቤት ባለቤት መሆን ማለት ነው አሉ።

ታዳጊዎች በውድድሩ ዳንሳቸውን እንኳ አሳይተው ሳይጨርሱ ‘ጎልደን ባዘር’ በማግኘት ታሪክ ሰርተዋል።

ከዚህ ቀደም በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊዎች ሥራቸውን አሳይተው ሳይጨርሱ ‘ወርቃማ የአሸናፊነት ደውል’ ተሰጥቶ የሚያውቅ ተወዳዳሪ የለም።

ከ5-13 ዓመት መካከል የሚገኙት ኡጋንዳውያን ዛሬ በሚከናወነው የፍጻሜ ውድድር ተሳታፊ ከሚሆኑ 10 ተወዳዳሪዎች መካከል መካተት ችለዋል።

እነዚህ ታዳጊዎች ለውድድሩ ዩናይትድ ኪንግደም ድረስ የተጓዙት ካምፓላ ከሚገኘው የድሆች መኖሪያ መንደራቸው ነው።

የልጆቹ አሳዳጊ እና ማናጀር የሆነው ዳውድ ካቩማ የታዳጊዎቹ ስኬት በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሌሎች ልጆችን ያበረታታል የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል።

“ይህን ማድረግ በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን፤ በመላው ዓለም በደኅነት ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ተስፋ እንዳላቸው እንዲያስቡ ማድረግ ችለናል ብለን እናስባለን ብሏል።

እነዚህ ታዳጊዎች በዩናይትድ ኪንግደም እና በመላው ዓለም ባሉ ብሪቴይንስ ጎት ታለንት ተመልካቾች ዘንድ አዲስ አድናቂዎችን ማግኘት ቢችሉም፤ ዝናቸው መናኘት የጀመረው በ2022 ኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ የዳንስ ዝግጅት ካቀረቡ በኋላ ነው።

ከቡድን አባላቱ መካከል የ13 ዓመት ታዳጊዋ ፕሪሲላ ዛዌዴ የቲቪ ፕሮግራሙ አሸናፊ ሆነው 250ሺህ ፓዎንድ የገንዘብ ሽልማት ቢቀበሉ ድላቸው፤ ‘ለሁላችንም የሚበቃ የትልቅ ቤት ባለቤት መሆን ማለት ነው’ ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ካቩማ የሚንከባከባቸው ወደ 30 የሚጠጉ ታዳጊዎች በአሁኑ ወቅት 5 መኝታ ቤት ባለው ቤት የካምፓላ የድሆች መንደር ውስጥ ይኖራሉ።

ካቩማ እአአ 2007 ላይ ጎዳና ላይ የወደቁ ታዳጊዎችን ለመንከባከብ ነበር ‘ጌቶ ኪድስ ፋውንዴሽን’ የተሰኘ ተቋም የመሰረተው።

በአሁኑ ወቅት ታዳጊዎቹ መተዳደሪያ ገንዘብ የሚያገኙት ከእርዳታ ሰጪዎች፣ ከማሕብራዊ ሚዲያ ከሚገኙ ገቢዎች እና በዳንስ ዝግጅቶቻቸው ላይ ለመታደም ከሚሸጠው የቲኬት ገቢ ነው።

ወላጅ አባቱን በሞት ካጣ በኋላ ጎዳና ላይ መውደቁን የሚናገረው ሌላኛው የዳንስ ቡድኑ አባል አክራም ሙያና፤ ሙዚቃ የአስቸጋሪ ሕይወት እውነታ ማምለጫዬ ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የ13 ዓመቱ ታዳጊ አክራም፤ “ስደንስ በጣም ደስተኛ እሆናለሁ፤ ጨንቀቴ ሁሉ ይለቀኛል። እናቴ ልብስ እና ምግብ እንድትገዛለኝ ገንዘብ ለማግኘት ስል ወደ ቤተክርስቲያን እየሄድኩ እደንስ ነበር” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።