ዩናይትድን አሸንፎን የኤፍ ኤ ዋንጫ ባለቤት የሆነው ሲቲ 'ሦስተኛውን ለመድገም ቋምጧል'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማንቸስተር ሲቲ በኢካይ ጉንዶዋን ጎሎች ታግዞ ዩናትድን በመርታት የኤፍ ኤ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።
በዌምብሊ ስታድየም ቅዳሜ አመሻሹን በተደረገው ጨዋታ የከተማ ተቃናቃኙን የረታው ሲቲ ሦስቱን አበይት ዋንጫዎች ለማንሳት ግስጋሴውን ቀጥሏል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ያነሳው ሲቲ በሚመጣው ቅዳሜ ምሽት በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ከኢንተር ሚላን ይገናኛል።
ሲቲ፤ በኢስታንቡል የሚደረገውን ፍልሚያ የሚያሸንፍ ከሆነ ዩናይትድ በ1999 ያደረገውን መድገም ይችላል።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እስከዛሬ ከማንቸስተር ዩናይትድ ውጭ የሊጉን፣ የኤፍ ኤ እና ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በአንድ ውድድር ዘመን ያነሳ ቡድን የለም።
በትናንትናው የፍፃሜ ጨዋታ አምበሉ ኢካይ ጉንዶዋን በኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ታሪክ ፈጣኗን ጎል በማስቆጠር ስሙን ፅፏል።
ከዚህ ቀደም በ2009 ፈጣኗን ጎል ያስቆጠረው በወቅቱ የኤቨርተን ተጫዋች የነበረው ሉዊስ ሳሃ ነበር።
ነገር ግን በ33ኛው ደቂቃ በቪኤአር አጋዥነት የፍፁም ቅጣት ምት ያገኘው ዩናይትድ አምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴዝ አማካይነት ጎል በማስቆጠረ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር።
ከእረፍት መልስ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ኢካይ ጉንዶዋን የጨዋታዋን ወሳኝ ጎል አስቆጠረ።
ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ብዙ ቢጥሩም የሲቲ ተከላካይ መስመር ሥፍራውን አስጠብቆ ጨዋታው 2-1 ተጠናቋል።
ወደ ታላቅነት እየገሰገሰ ያለው ሲቲ
ማንቸስተር ሲቲ በታሪካቸው ታላቁን የውድድር ዘመን ለማሳለፍ የሚቀራቸው 90 ደቂቃ ብቻ ነው።
አርሰናል በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ከሊጉ መሪነት አሰናብተው የሊጉን ዋንጫ ያነሱት ሲቲዎች ኤፍ ኤፍ ዋንጫ ጨምረውበታል።
በሚመጣው ቅዳሜ ከኢንተር ሚላን የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ፍፃሜ የሚጠብቃቸው ሲቲዎች ዩናይትድ ከ24 ዓመታት በፊት ያደረገውን ለመድገም ቋምጠዋል።
አምበሉ ኢካይ ጉንዶዋን ምናልባት በሚመጣው የዝውውር መስኮት ሲቲን ሊለቅ ቢችልም ለቡድን ምን ያህል አስፈላጊ ተጫዋች እንደሆነ አሳይቷል።
ሌላው በትላንትናው ጨዋታ ጎልቶ የወጣው ተከላካዩ ጆን ስቶንስ ነው።
ጉዋርዲዮላ፤ ስቶንስ ከባሕላዊ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ወጣ ባለ መልኩ ወደ አማካይ ሥፍራ እያደላ ቡድኑን እንዲያግዝ ማድረግ ችሏል።
ማንንም ከመርታት ወደኋላ የሚሉ የማይመስሉት የጉዋርዲዮላ ልጆች ለኢንተር ሚላን ዝግጅት ማድረግ ይጀምራሉ።
ምንም እንኳ ዩናይትድ የውድድር ዘመኑን በሲቲ ተሸንፎ ቢያገባድድም ኤሪክ ቴን ሃግ በመጀመሪያው የውድድር ዘመናቸው መልካም ለውጥ ያሳዩ ይመስላሉ።
ዩናይትድ ከስድስት ዓመታት በኋላ ዋንጫ አንስቷል፤ አልፎም ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተመልሷል።
ነገር ግን የቴን ሃገር ቡድን መጠናከር እንደሚያስፈልገው ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።












