የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለባቡር አደጋው ምክንያት የሆኑ ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በተቃራኒ አቅጣጫ ሲጓዙ የነበሩ ባቡሮች ተላትመው የ288 ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ለአደጋው ጥፋተኛ ሆኖ የሚገኝ ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አደጋው የደረሰበትን ስፍራ ከጎበኙ በኋላ የተመለከቱትን ነገር “እጅግ በጣም የሚያሳምም ነው” ብለዋል።
ሞዲ በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ ተጎጂዎችን የጎበኙ ሲሆን፣ መንግሥታቸው ለተጎጂዎችን አስፈላጊውን ሕክምና ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ከትናንት በስቲያ ዓርብ በተከሰተው አደጋ ቢያንስ 288 ሰዎች ሲሞቱ ከ800 በላይ ቆስለዋል።
ይህ አደጋ በሕንድ በዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ከደረሱ የባቡር አደጋዎች የከፋው ነው ተብሏል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው እና ከአደጋው መውጣት አቅጧቸውን የነበሩ ሰዎችን ከስፍራው የማውጣት ሥራ መጠናቀቁን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
አደጋው የደረሰው አንድ የመንገደኞች ባቡር መስመሩን ስቶ ከወጣ በኋላ በሌላ ከተቃራኒ አቅጣጫ እየመጣ ይመጣ በነበረ ባቡር መገጨቱን ተከትሎ ነው በርካታ ሰዎች ሊጎዱ የቻሉት።
አደጋው ሲከሰት በሁለቱ ባቡሮች ላይ ወደ 2000 የሚጠጉ ሰዎች ተሳፍረው ነበር።
በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ ከ200 የማያንሱ አምቡላንሶች በአደጋው ስፍራ ተገኝተው ነበር። የግል አውቶብሶችም ተጎጂዎችን ወደ ጤና ማዕከላት ሲያመላልሱ ታይተዋል።
የሕንድ የባቡር አስተዳደር እንዳለው በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ኮሮማንዴል ኤክስፕረስ እና ሆውራሽ ሱፐርፋስት ኤክስፕረስ ባቡሮች ናቸው።
ሕንድ በዓለም ላይ ሰፊ፣ ረዥም እና ጥልፍልፍ የባቡር መስመሮች ያሏት አገር ስትሆን የባቡር መስመሮች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶ በተደጋጋሚ ዕድሳት ቢደረግላቸውም እንዲህ ዓይነት አደጋዎች የተለመዱ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በሕንድ የከፋ የተባለው የባቡር አደጋ ደርሶ የነበረው በእአአ 1980ዎቹ ማብቂያ ላይ ሲሆን በወቅቱ አንድ ባቡር በአውሎ ንፋስ ከሃዲዱ ተገፍትሮ ፉርጎዎቹም ወደ ወንዝ መወርወራቸውን ተከትሎ 800 ተሳፋሪዎች አልቀው ነበር።












