በበይነ መረብ አማካይነት ወጣቶችን ለባርነት እየዳረጉ ያሉ አጭበርባሪዎች

ወጣቶች በደቡብ ምሥራቅ እስያ እንግልት እየደረሰበቸው ይገኛል

የፎቶው ባለመብት, MIRROR WEEKLY

የምስሉ መግለጫ, ያንግ ዊቢን ካምቦዲያ ውስጥ ያሳለፈውን እንግልት የሚገልጽ ጽሑፍ ይዞ በመዞር ንቅናቄ ያደርጋል።

ያንግ ዊቢን የ35 ዓመት ታይዋናዊ ነው።

በበይነ መረብ ካምቦዲያ ውስጥ የአሻሻጭነት ሥራ ማስታወቂያ ሲመለከት ተደስቶ ነበር።

ሥራው ጥሩ ደመወዝ እንዳለውና ሠራተኞች በውብ ሆቴል እንደሚያርፉ ማስታወቂያው ያትታል።

አባቱ ስትሮክ ከታመሙ በኋላ ያንግ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ተቸግሯል።

በማሳጅ ሥራ የሚያገኘው ገንዘብ እምብዛም አጥጋቢ አልነበረም።

ያንግ አላቅማማም። ለመቀጠር ወሰነ።

ወደ ካምቦዲያ የአውሮፕላን ትኬት ቆረጠ።

የካምቢዲያ መዲና ሲደርስ የተወሰኑ ወንዶች ተቀበሉት።

የሥራ ማስታወቂያው ላይ ከተመለከተው ውብ ሆቴል በተቃራኒ፣ ወዳልታወቀ ቦታ በመኪና ወሰዱት።

“የምናስፈጽምልህ ጉዳይ አለ” ብለው ፓስፖርቱን ወሰዱ።

አንድ ትንሽ ቤት ውስጥ አስገቡትና “ከዚህ ጊቢ ፈጽሞ ለመውጣት እንዳታስብ” ሲሉ አስጠነቀቁት።

“አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደገባሁ ያወቅኩት ያኔ ነው” ይላል ያንግ።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ወንጀለኞች ሰለባ ከሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች አንዱ ያንግ ነው።

በሥራ ማስታወቂያ ታዳጊዎችን ማጥመድ

እነዚህ አጭበርባሪዎች በበይነ መረብ የሥራ ማስታወቂያ እያወጡ ነው ሰዎችን መረባቸው ውስጥ የሚከቱት።

የኢንዶኔዥያ፣ የቬትናም፣ የማሌዢያ፣ የሆንግ ኮንግ እና የታይዋን ባለሥልጣናት ይህንን የወንጀል መረብ ለመበጣጠስ እየጣሩ ይገኛሉ።

የበይነ መረብ ማስታወቂያዎቹ ለቀላል ሥራዎች ከፍተኛ ደመወዝ ያስቀምጣሉ።

ማስታወቂያዎቹን አምነው ወደ ካምቦዲያ፣ ሚያንማር እና ታይላንድ የሚበሩ ጥቂሮች አይደሉም።

ወደእነዚህ አገራት ከደረሱ በኋላ ይታገቱና በበይነ መረብ ወንጀል እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንግዳ ነገር አይደለም።

የወንጀል ቡድኖች ከሰዎች ዝውውር ባሻገር ሌሎችም ሕገ ወጥ ድርጊቶች መፈጸም ጀምረዋል።

ዒላማ የሚያደርጉት ታዳጊዎችን ነው።

የሚመለምሏቸው ታዳጊዎች የኮምፒውተር ዕውቀት ያላቸውና ከአንድ በላይ ቋንቋ የሚችሉ ናቸው።

ታዳጊዎቹን በሐሰተኛ የበይነ መረብ የፍቅር አጋር አፈላላጊ ገጾች ያሠሯቸዋል።

‘pig butchering’ የተባለው ድረ ገጽ ይጠቀሳል።

በሕገ ወጥ ቁማር፣ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በክሪፕቶከረንሲ ማጭበርበር ታዳጊዎቹ ተገደው ይሰማራሉ።

“. . . እንዳጠምድ አስገደዱኝ”

ቪየትናማዊው ቺ ቲን ራሱን ሴት አስመስሎ በበይነ መረብ ሰዎችን እንዲያጠምድ መገደዱን ይናገራል።

“በየቀኑ በበይነ መረብ 15 ጓደኞች አፍርቼ በሕገ ወጥ ቁማርና ሐሰተኛ ሎተሪ እንዲሳተፉ እንዳሳምን እገደድ ነበር” ይላል።

ከ15 ሰዎች መካከል አምስቱ በቁማር የሒሳብ ቁጥራቸው ገንዘብ እንዲያስገቡ የማሳመን ግዴታም ተጥሎበታል።

“ኃላፊው ምንም ተቃውሞ ሳላሰማ እንድሠራ ያስገድደኝ ነበር። ለማምለጥ ብሞክር ወይም አልሠራም ብል እንግልት ወደሚፈጸምበት ክፍል እንደሚወስደኝም ያስፈራራኛል። ሌሎች ደግሞ የሚጠበቅባቸውን ካላደረጉ እንደሚደበደቡና ምግብ እንደሚከለከሉም ነግረውኛል።”

ወጣቶቹ የሚደርስባቸው እንግልት እስከ ወዲያኛው የአእምሮ ጠባሳ የሚተው ነው።

ለደኅንነታቸው ሲባል ሁለት ስማቸውን የማይጠቀስ ቬትናማውያን እንደተናገሩት፣ ተደብድበዋል፣ በኤሌክትሪክ ገመድ ተጠብሰዋል፣ ለሌሎች አጭበርባሪዎችን ተሸጠዋል።

አንደኛዋ 15 ዓመቷ ነው።

ፊቷ በደረሰባት ድብደባ በጠባሳ ተሸፍኗል።

ሌላኛው የ25 ዓመት ሰው በአሠሪዎቹ አካላዊ ጥቃት ደርሶበታል።

አሠሪዎቹ ያደረሱበትን ጥቃት ፎቶ አንስተው፣ ቤተሰቦቹ ገንዘብ እንዲከፍሉ ለመጠየቅ አውለውታል።

ከብረት ጋር እጁ ታስሮ፣ ጉልበቱ ላይ በኤሌክትሪክ ገመድ የተጠበሰበት ምልክት በፎቶው ይታያል።

እነዚህ ወጣቶች ከአጭበርባሪዎቹ እጅ መውጣት ከፈለጉ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ። አልያም ለሌሎች አጭበርባሪዎች ይሸጣሉ።

የቺ ቲን ቤተሰቦች 2,600 ዶላር ከፍለው ነው ያስለቀቁት።

ገንዘቡን የመክፈል አቅም የሌላቸው ለማምለጥ ከመሞከር ውጪ አማራጭ የላቸውም።

ወጣቶቹ ከፍተኛ አካላዊ እንግልት ይደርስባቸዋል
የምስሉ መግለጫ, ወጣቶቹ ከፍተኛ አካላዊ እንግልት ይደርስባቸዋል

ራሳቸውን ለማዳን ወንዝ የገቡት ወጣቶች

ባለፈው ወር ካምቦዲያ ውስጥ ታግተው የነበሩ 40 ቬትናማውያን ለማምለጥ ሲሉ ወንዝ ውስጥ መግባታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ወንዙን ዋኝተው ለመሻገር ሲሞክሩ ከመካከላቸው የ16 ዓመት ታዳጊ ሞቷል።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት፣ በካምቦዲያ፣ በታይላንድ እና በሚያንማር በዚህ የማጭበርበር ወንጀል የሚሳተፉት በቻይናውያን የተያዙ ተቋሞች ናቸው።

ዓለም አቀፉ የፀረ ማጭበርበር ድርጅት እንደሚለው እነዚህ ተቋሞች የቻይና የወንጀል ቡድኖች ተቀጥላ ናቸው።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጃን ሳንቲያጎ “እነዚህ ተቋሞች የአይቲ፣ የፋይናንስ እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር የማስገባት ቅርንጫፎች አሏቸው። እንዴት ማጭበርበር እንደሚቻል ሥልጠና የሚሰጡና ዓመታዊ የሽያጭ ግብ ያላቸው ተቋሞችም አሉ” ብለዋል።

ተቋሞቹ ከሚገኙባቸው አገራት ተሻግረው ዓለም አቀፍ የትስስር መስመርም መዘርጋታቸው ተገልጿል።

ምን እርምጃ ተወሰደ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ወር የታይዋን መንግሥት 40 የወንጀል ቡድኖችን እንደደረሰባቸው አስታውቋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት ሰዎች የገጠማቸውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ በመጠቀም ወንጀሉ ተስፋፍቷል።

በተባበሩት መንግሥታት የእስያ ስደተኞች ባለሙያ ፔፒ ኪቪኔሚ ሲዳቅ እንደሚሉት፣ አብዛኞቹ የወንጀሉ ሰለባዎች ታዳጊዎች ናቸው።

“የዩኒቨርስቲ ምሩቅ የሆኑ ታዳጊዎች ሥራ በቀላሉ አያገኙም። በበይነ መረብ የሥራ አማራጭ እንዳገኙ ሲሰማቸው ከመስማማት ወደኋላ አይሉም። የወንጀል ቡድኖችን ለመደምሰስ አቅም በሌላቸው አገራት የበለጠ ተስፋፍተው ይሠራሉ።”

ባለፈው ወር የታይላንድ ባለሥልጣናት ሺ ዢጃንግ የተባለ ነጋዴ በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ የሚያስገኝ መቆመሪያ እና አስጎብኚ ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ንግዶች ነበሩት።

ይህ በኢንተርፖል ይፈለግ የነበረው ግለሰብ፣ በቀጠናው ሕገ ወጥ ቁማር በማከናወን ተከሷል።

‘KK Park’ በሚባለው የዚህ ግለሰብ ግቢ በርካታ ሰዎች እንግልት እንደደረሰባቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በዚህ ጊቢ ታግተዋል፣ ተደብድበዋልም።

የካምቦዲያ መንግሥት “አዲስና በጭካኔ የተሞላ” ያለውን ወንጀል ለመከላከል ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።

የወንጀሉ ሰለባ የሆኑ ወጣቶች ግን የካምቦዲያ ፖሊስ፣ ዳኞችና ሌሎችም የመንግሥት ኃላፊዎች ወንጀሉን ለመግታት ተገቢውን እርምጃ እንዳልወሰዱ እንዲያውም ጉቦ በመቀበል ኃላፊነታቸውን ከመወጣት እንደተቆጠቡ ይከሳሉ።

በተባበሩት መንግሥታት የእስያ ስደተኞች ባለሙያ ፔፒ ኪቪኔሚ ሲዳቅ እንደሚሉት፣ የሰዎች ዝውውር ሕግጋት ሊሻሻሉ ይገባል። የወንጀሉ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለመታደግም የሕግ አካላት መትጋት አለባቸው።

አንዳንድ አገራት ሕዝቡን ከማስተማር አልፈው ወደ ደቡብ እስያ አገራት የሚጓዙ ዜጎቻቸው ላይ ፍተሻ እስከማድረግ ደርሰዋል።

ያንግ በካምቦዲያ ለ58 ቀናት ከታገተ በኋላ በስተመጨረሻ ማምለጥ ችሏል።

የበይነ መረብ ማጭበርበር ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መብት የሚታገሉ አክቲቪስቶች ረድተውት ወደ ቤቱ መመለስም ችሏል።

ልክ እንደሱው የማጭበርበር ሰለባ የሆኑ ወጣቶችን ለማዳን ንቅናቄም ጀምሯል።

ካምቦዲያ ውስጥ ያሳለፈውን እንግልት የሚገልጽ ጽሑፍ ይዞ በመዞር ንቅናቄ ያደርጋል።

“ብዙዎች ቅንጡ ሥራ ይዘው ሕይወታቸውን ለመለወጥ ያልማሉ። አንዳንዴ ይህ ቅዠት ነው። ሰዎች እውነታን የተመረኮዘ ሕልም እንዲኖራቸው ነው የምክረው። ገንዘብ የትም ይገኛል። ሕይወትን አደጋ ላይ ጥሎ ሌላ አገር መሰደድ አያስፈልግም። የሚደርስባችሁን ስቃይ መገመት እንኳን አትችሉምና ተጠንቀቁ” ይላል።