የዩክሬን ጸጥታ ኃይሎች ሩስያውያን ለስለላ ይጠቀሙበታል ያሉትን ታሪካዊ የኦርቶዶክስ ገዳም ጥሰው ገቡ

በኪዬቭ የሚገኘው ፔቸርስክ ላቫራ ጥንታዊ የኦርቶዶክስ ገዳም

የፎቶው ባለመብት, SBU

የዩክሬን የጸጥታ አገልግሎት በዋና ከተማዋ የሚገኘውን ታሪካዊ ገዳም ጥሰው በመግባት ብርበራና ፍተሻ ማድረጋቸው ተሰማ።

የሩሲያ ወኪሎች ስፍራውን ለጥፋት፣ መረጃ ወይም ለጦር መሳሪያ ማስቀመጫነት እንዳይገለገሉበት ያለመ ዘመቻም ነው ተብሏል።

በኪዬቭ የሚገኘው ፔቸርስክ ላቫራ ጥንታዊ የኦርቶዶክስ ገዳም የተቆረቆረው በ11ኛው ክፍለ ዘመን ነው።

ገዳሙም የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መቀመጫ ነው።

የሩስያን ወረራ ተከትሎም የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሞስኮው ተለይታለች።

በቤተ ክርስቲያኗ መካከል ሽኩቻው የተፈጠረው የሩሲያው የኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ክሪል ጦርነቱን መደገፋቸውን ተከትሎ ነው።

አንዳንድ የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቀሳውስትም ሞስኮን በድብቅ በመደገፍ በምዕመናኑ ላይ ጫና አሳርፈዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሩሲያ በበኩሏ በኪዬቭ ገዳም ላይ የደረሰው ብርበራና ፍተሻ የሩሲያ ኦርቶዶክስን ለማጥቃት ያለመ ነው ብላለች።

በኪዬቭ የሚገኘው የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የሩሲያ ልዩ አገልግሎቶች በሚያደርጓቸው ተግባራት ላይ ያነጣጠረ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

 የበርካታ ነዋሪዎች ማዕከል በሆኑ ስፍራዎች ላይ የጥቃት፣ የማፈን እና የማገት አደጋ ጨምሯል ብሏል።

የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ የሆነው ገዳም ማክሰኞ እለት በዩክሬን የጸጥታ ኃይሎች ከተወረሩ በርካታ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ አንዱ ነው። የገዳሙ ቀሳውስት ለሞስኮ ድጋፍ እያደረጉ ነው እንዲሁም ከክሬምሊን ጋርም ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል በሚል ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ባለስልጣናቱ የሰጡት ምላሽ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ሩሲያን የሚደግፉና “እናት ሩሲያ” እንድትመለስ የሚያነቃቁ የፕሮፓጋንዳ መዝሙር ሲዘመር የሚያሳይ ቪዲዮ ከሳምንት በፊት መውጣቱን ተከትሎም የወንጀል ምርመራ ተከፍቷል።

ከቀናት በኋላ በማዕከላዊ ዩክሬን የቪኒትሲያ አካባቢ የሀገረ ስብከት ሐላፊ የሩስያን ወረራ የሚደግፉ የፕሮፓጋንዳ በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ተከሰዋል።

የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዩክሬን ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ለረጅም ጊዜ "ጦርነት ላይ ናት” ሲሉ ከሰዋል።

የሩሲያው ፓትርያርክ ክሪል በበኩላቸው “በምዕመናን ላይ የሚፈጸምን የማስፈራራት ተግባር” አውግዘዋል።

የሩሲያው ፓትርያርክ የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አጋር እንደሆኑ የሚነገር ሲሆን በዩክሬን ለሚካሄደው የሩሲያ ጦርነት ሙሉ ድጋፍ ሰጥተዋል።

በዩክሬን በቤተ ክርሰቲያኖች ላይ የተፈጸመው ብርበራና ፍተሻ ከዩክሬናውያን በኩል ድጋፍ አግኝቷል። የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቁጥጥር ስር የነበረ ሲሆን ይህም ሁኔታ ከስድስት ወራት በኋላ ልዩ መልክ ይዟል።

 ሆኖም አሁንም ቤተክርስቲያኗ በዩክሬን ያለውን የህዝብ አስተያየት ጫና ለመፍጠር ክሬምሊን እንደ መሳሪያ ትጠቀምባታለች የሚል ጥርጣሬም እንዳለ ተገልጿል።