የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ስለታይዋን ምንም ነገር ሳይሉ ጉብኝታቸውን ጀመሩ

አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት ናንሲ ፔሎሲ የቻይናን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ታይዋን የጉብኝታቸው አካል ትሁን አትሁን ምንም ነገር ሳይገለጽ ወደ እስያ ተጓዙ።

ፔሎሲ በጉዟቸው ሴንጋፖርን፣ ማሌዢያን፣ ደቡብ ኮሪያን እና ጃፓንን እንደሚጎበኙ ጽህፈት ቤታቸው የገለጸ ሲሆን፣ ቻይና የግዛቴ አካል ናት የምትላትን ታይዋንን ግን ሳይጠቅስ አልፏታል።

አፈ ጉባኤዋ ጉብኝት እንደሚያደርጉ በተገለጸበት ጊዜ ወደ እራስ ገዟ ታይዋን ሊጓዙ እንደሚችሉ በስፋት ሲወራ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ታይዋን የግዛቴ አካል ናት የምትለው ቻይና፣ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ “ከባድ መዘዝ” እንደሚከተል አስጠንቅቃለች።

ባለፉት 25 ዓመታት አንድም ከፍተኛ ሥልጣን ያለው በሕዝብ የተመረጠ የአሜሪካ ባለሥልጣን ታይዋንን ጎብኝቶ አያውቅም።

የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተመራጯ ናንሲ ፔሎሲ ጉብኝታቸውን በተመለከተ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ የአገሪቱ ምክር ቤት ልዑካን ቡድን ስድስት አባላት “በአካባቢው ላሉ ወዳጆቻችንና አጋሮቻችን አሜሪካ ያላትን የማይወላውል አቋም የምናጸናበት ነው” ብለዋል።

የአፈ ጉባኤዋ ጽህፈት ቤት ጉዞውን በተመለከተ እንዳለው፣ ጉብኝቱ “ሴንጋፖር፣ ማሌዢያ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓንን ጨምሮ የኢንዶ-ፓሲፊክ አካባቢን” የሚመለከት ነው ብሏል።

ቻይና ታይዋን ወደ እናት አገሯ መመለስ ያለባት አፈንጋጭ ግዛቷ እንደሆነች ትመለከታታለች። ይህንንም ለማሳካት ወደፊት ቤይጂንግ ኃይል መጠቀምን እንደ አንድ አማራጭ ታየዋለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቻይና ባለሥልጣናት አሜሪካ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደረገች ነው በሚል ቁጣቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ባለፈው ሚያዚያ ወርም ስድስት የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በታይዋን ድንገተኛ ጉብኝት አድርገው ነበር።

አሜሪካ ከቻይና ጋር እንጂ ከታይዋን ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት የላትም።

ናንሲ ፔሎሲ በቻይና የሰብአዊ መብት አያያዝ የተነሳ የአገሪቱን መሪዎች ለረጅም ጊዜ ሲተቹ ቆይተዋል። በተጨማሪም ከዲሞክራሲ ደጋፊ ቻይናውያን ጋር የተገናኙ ሲሆን፣ የታይናሚን አደባባይ ጭፍጨፋ ሰለባዎችን ለማስታወስ አደባባዩን ጎብኝተዋል።

አፈ ጉባኤዋ ታይዋንን ለመጎብኘት አቅደው የነበረው ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የነበረ ቢሆንም፣ በኮቪድ በመያዛቸው ጉዟቸውን አዘግይተውት ቆይተዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት “ለታይዋን ያለንን ድጋፍ ማሳየት ለእኛ አስፈላጊ ነገር ነው” ብለው ተናግረውም ነበር።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ጦር ኃይል ፔሎሲ ወደ ታይዋን ሊያደርጉ ያሰቡት ጉብኝት “በአሁኑ ወቅት ጥሩ ሃሳብ አይደለም” ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።

ከአፈ ጉባኤዋ ጽህፈት ቤት ዛሬ እሁድ የወጣው መግለጫ ጉዞው “በኢንዶ-ፓሲፊክ አካባቢ ስላላው የጋራ የደኅንነት፣ ምጣኔ ሀብታዊ አጋርነት እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ላይ የሚያተኩር ይሆናል” ብሏል።

በውይይቱ ላይ ንግድ፣ የአየር ፀባይ ለውጥ እና የሰብአዊ መብት ጉዳዮችም እንደሚነሱ ተነግሯል።

ከፔሎሲ ጋር በጉዞው የሚሳተፉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋነኛ አባላት የሆኑት ግሪጎሪ ሚክስ፣ ማርክ ታካኖ፣ ሱዛን ዴልቤኔ፣ ራጃ ክሪሽናሙርቲ እና ኤንዲ ኪም ናቸው።

ታይዋንን የጎበኙ የመጨረሻው የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሪፐብሊካኑ ኒውት ጊንግሪች ሲሆኑ፣ እሱም በአውሮፓውያኑ 1997 ነበረ።