ታይዋንን ነጻ አገር ለማድረግ መሞከር ጦርነት እንደሚቀሰቅስ ቻይና አስጠነቀቀች

የታይዋን ሠራዊት አባል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ ታይዋንን ነጻ አገር ለማድረግ ማንኛውንም አይነት ሙከራ የምታደርግ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ አስጠነቀቀች።

ታይዋንን ከቻይና እንድትለይ መሞከር የቻይና ጦር ሠራዊት “የትኛውንም ዋጋ ከፍሎ ከመዋጋት ውጪ” ምንም ምርጫ አይኖረውም ሲሉ የቻይና መከላከያ ከፍተኛ ባለሥልጣን መናገራቸው ተዘግቧል።

ይህ የተነገረው የቻይናው የመከላከያ ሚኒስትር ዌይ ፌንግ ሴንጋፖር ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው የእስያ ደኅንት ጉባኤ ጎን ለጎን ከአሜሪካው አቻቸው ሎይድ ኦስቲን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ተከትሎ ነው።

ቀደም የአሜሪካው የመከላከያ ኃላፊ ሎይድ ኦስቲን ቻይና እያካሄደች ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ “ጠብ ጫሪ፣ ሰላምን የሚያናጋ” ሲሉ ተችተው ነበር።

ጨምረውም ከደሴቲቱ ታይዋን አቅራቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በየዕለቱ መብረራቸው “የአካባቢውን መረጋጋት የሚሸረሽር ነው” ብለዋል።

ቻይና እራሷን የምታስተዳድረውን ታይዋንን የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ የምትመለከት ሲሆን፣ በዚህ አቋሟ የተነሳም የቻይናው የመከላከያ ሚኒስትር አሜሪካ ለታይዋን የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ አውግዘዋል።

የቻይና መንግሥት ቃል አቀባይ የመከላከያ ሚኒስትሩን ጠቅሶ እንደተናገረው "ታይዋንን ከቻይና ለመነጠል የሚደረግን የትኛውንም ሙከራ የቻይና ሠራዊት በመደምሰስ የአገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድንትን ከማስጠበቅ ውጪ አማራጭ አይኖረውም” ብለዋል።

የአሜሪካው የመከላከያ ኃላፊ ሎይድ ኦስቲንም አገራቸው የቻይናን መንግሥት ተገቢውን እውቅና በመስጠት የታይዋንን ነጻ አገርነት እንደማትቀበል በመግለጽ፣ ያለው ሁኔታ ባለበት እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ያሉ ውጥረቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ምንም አይነት ሙከራ መኖር እንደሌለበትም ተናግረዋል።

የሁለቱ አገራት የመከላከያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በእስያ የደኅንት ጉባኤ ላይ ተገናኝተው ለአንድ ሰዓት ያህል ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።

የቻይናው መከላከያ ሚኒስትር ዌይ የሁለቱ ባለሥልጣናት ውይይት "በተሳካ ሁኔታ የተካሄደ እንደነበር" አመልክተው፣ ኦስቲንም አለመግባባቶችን ለማስወገድ ክፍት የሆነ የግንኙነት መንገድ መኖር አለበት ብለዋል።

ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በቁጥር ከፍተኛ የተባለላቸው 30 የቻይና የጦር አውሮፕላኖች የአየር መከላከያ ክልሏን ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ታይዋን ተዋጊ አውሮፕላኖቿን ማሰማራቷን አሳውቃ ነበር።

ይህንንም ክስተት ተከትሎ 22 የታይዋን ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ ኤሌክትሮኒክስ የውጊያ ሥርዓት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ፀረ ሰርጓጅ መርከብ አውሮፕላኖች ተሰማርተው እንደነበር የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።