30 የቻይና አውሮፕላኖች የታይዋንን የአየር መከላከያ ቀጠናን ጥሰው ገቡ

የቻይና ተዋጊ ጀት (ፋይል ፎቶ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ትናንት ሰኞ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም. 30 ተዋጊ አውሮፕላኖቿን በታይዋ የአየር መከላከያ ቀጠና ውስጥ አበረረች።

ታይዋን የአየር መከላከያ ዞን ጥሰው ለገቡት የቻይናዋ ተዋጊ አውሮፕላኖች ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ተዋጊ አውሮፕላኖቿን አሰማርታ እንደነበረ ገልጻለች።

የቻይና አውሮፕላኖች ዋናውን የታይዋንን የአየር ክልል ጥሰው አልገቡም። ይህ ቢሆን ኖሮ የቻይና እርምጃ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የትንኮሳ ተግባር ተደርጎ ይቆጠር ነበር።

የአየር መከላከያ ዞን ከአንድ አገር ድንበር እና የአየር ክልል ውጪ ያለ ቢሆንም ለአንዲት አገር ብሔራዊ ደኅንነት ሲባል በቀጠናው ውስጥ የሚገቡ የውጭ አገር አውሮፕላኖች መለየት ይገባቸዋል፣ እንዲሁም ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

ቻይና አውሮፕላኖቿን ወደ ታይዋን የላከችው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ቤይጂንግ ታይዋንን ብትወር ፈተና እንደሚገጥማት ማስጠንቀቂያ ከሰጡ ከቀናት በኋላ ነው።

ቻይና የጦር ልምምድ እያደረጉ ነው የምትላቸው ተዋጊ አውሮፕላኖቿ የታይዋንን አየር ክልል ጥሰው ሲገቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

ይህ የቻይና ተግባር ታይዋንን ከማበሳጨቱ በተጨማሪ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል።

ቻይና ታይዋንን እንደ አንድ ተገንጣይ ግዛቷ አድርጋት ነው የምትመለከታት። ቤይጂንግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ታይዋንን በኃይል መልሳ መጠቅለል እንደምትችል ታስባለች።

ትናንት ወደ ታይዋን ከገቡት 30 አውሮፕላኖች መካከል 22 የሚሆኑት ተዋጊ ጀቶች ሲሆኑ፤ ፀረ-ሰርጓጅ መርከብ እና ቅኝት የሚያደርጉ የጦር አውሮፕላኖች እንደሚገኙበት የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የቀጠናውን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች፤ ቻይና ተደጋጋሚ በሆነ መልኩ የጦር አውሮፕላኖቿ ወደ ታይዋን እየላከች ያለችው፤ የታይዋን መሪዎች አገሪቱ ነጻነቷን እንድታውጅ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው ይላሉ።

ባይደን በኢሲያ ጉብኝታቸው ማጠናቀቂያ ላይ፤ ቻይና ለታይዋን የቀረቡ በረራዎችን በማድረግ ለአደጋ እየተጋበዘች ነው ካሉ በኋላ ቤጂንግ ወረራ ብትፈጽም አሜሪካ ታይዋንን እንደምትከላከል ዳግም አረጋግጠዋል።

አሜሪካ ታይዋን እራሷን እንድትከላከል እንድትረዳ የሚያስገድድ ሕግ አላት። ይህ ሕግ ግን ሆነ ተብሎ ግልጽ እንዳይሆን ተደርጓል። በዚህም ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ የአሜሪካ ምላሽ በትክክል ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም።

ይሁን እንጂ ባይደን ከዚህ ቀደም አሜሪካ ታይዋንን ከቻይና ጥቃት ለመከላከል አገራቸው ቆራጥ መሆኗን ተናግረው ነበር።

ታይዋን ዓለም አቀፍ እውቅና ያላት አገር ናት?

ቻይና እና ታይዋን የተለያዩት እእአ 1940ዎቹ በነበረው የእስር በእስር ጦርነት ወቅት ነው። ከዚያ በኋላ ታይዋን እራሷን እንደ ነጻ ሉዓላዊት አገር ትመለከታለች። ቻይና ግን እንደ አንድ ተገንጥለ እንደወጣች ግዛቷ ትቆጥራታለች።

ታይዋን የምትመራበት የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት አላት። በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሪዎችም አሏት። ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት አባላትም አላት።

ይህ ይሁን እንጂ ታይዋንን እንደ አገር እውቅና የሚሰጡት ጥቂት አገራት ከመሆናቸውም በተጨማሪ በተጽእኖ ፈጣሪነታቸው እዚህ ግባ የማይባሉ አገራት ናቸው።

ለታይዋን ጠንካራ አጋርነቷን የምታሳየው አሜሪካም ብትሆነ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላትም። የጦር መሳሪያዎችን ግን ለታይዋን ትሸጣለች።

አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሳሪያ የምትሸጠው ታይዋን እራሷን እንድትከላከለ የመርዳት ኃላፊነት ስላለብኝ ነው ትላለች።