የአፍሪካዊው ስደተኛ ግድያ ጣሊያን ውስጥ ቁጣን ቀሰቀሰ

ፖሊስ ይፋ ያደረገው የሟች አስከረን ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ

የፎቶው ባለመብት, POLIZIA DI STATO/QUESTURA DI MACERATA

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ ይፋ ያደረገው የሟች አስከረን ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ

በማዕከላዊ ጣሊያን አንድ ስደተኛ በጠራራ ፀሐይ በተፈጸመበት ጥቃት መገደሉን ተከትሎ ቁጣ ተቀሰቀሰ።

ባለፈው አርብ ሲቪታኖቫ ማርቼ በተባለችው ከተማ ዋነኛ ክፍል ውስጥ በጎዳና ላይ ንግድ በተሰማራ ናይጄሪያዊ ላይ በአንድ ግለሰብ የተፈጸመበት ጥቃት በጣሊያናውያን ዜጎች፣ በፖለቲከኞችና በስደተኞች ዘንድ ቁጣን አስከትሏል።

ጥቃቱ ሲፈጸም የሚያሳይ ቪዲዮ የተቀረጸ ሲሆን፣ ይህም ለማስጣል ምንም ባለደረገ ተመልካች ግለሰብ የተቀረጸ ሲሆን፣ አንድ ነጭ ግለሰብ ናይጄሪያዊውን ስደተና መሬት ላይ ጥሎ ይዞት ያሳያል።

ከጥቃቱ በኋላ አንድ የ32 ዓመት ጣሊያናዊ በግድያና በዘረፋ ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ጥቃቱን የሚያሳየው ቪዲዮ በጣሊያን የዜና ድረ አምባዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በስፋት ከተሰራጨ በኋላ፣ በሕዝቡ ውስጥ ድንጋጤን ፈጥሯል።

በርካቶችም ጥቃቱ ሲፈጸም በዙሪያ ሆነው “በምናገባኝ” ስሜት ምንም ሳያደርጉ ድርጊቱን ይመለከቱ የነበሩት ሰዎች ጉዳይን መነጋገሪያ አድርገውታል።

ግድያው በምን ምክንያት እንደተፈጸመ አስካሁን ግልጽ የሆነ መረጃ አልወጣም።

በተፈጸመበት ጥቃት የተገደለው ናይጄሪያዊ የጎዳና ላይ ነጋዴ አሊካ ኦጎርቹኩዉ እንደሚባልና የሁለት ልጆች አባት መሆኑ ታውቋል።

ባለቤቱ ቻሪቲ ኦሪያቺ የባለቤቷ አስከሬን መሬት ላይ እንዴት ወድቆ እዳየች ለመገናኛ ብዙኃን ስትናገር እንባዋን መቆጣጠር አቅቷት ታይታለች።

ግድያውን ተከትሎ ትናንት ቅዳሜ በማዕከላዊዋ የጣሊያን ግዛት ማርቼ፣ ሲቪታሰኖቫ ማርቼ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የናይጄሪያ ማኅበረሰብ ለሟች ወገናቸው ፍትሕ ለመጠየቅ ወደ አደባባይ በሰልፍ ወጥተው ነበር።

የተፈጸመውን ጥቃት የጣሊያን ፖለቲከኞች ጭምር አውግዘውታል።

የቀኝ ክንፍ ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ የሆኑት ኤንሪኮ ሌታ፣ ጥቃቱን “አስደንጋጭ” ሲሉ አውግዘውታል።

“ተሰምቶ የማያውቅ የጭካኔ ድርጊት ሲፈጸም በርካቶች በምን አገባኝ ስሜት ሲመለከቱ የነበረበት ሁኔታ ምንም አይነት ምክንያት የሌለው ነው” ሲሉ ፖለቲከኛው በትዊተር ገጻቸው ላይ ቁጣቸውን አስፍረዋል።

የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ የሆኑት ማቲዮ ሳልቪኒም “ደኅንት የትኛውንም ቀለም አይለይም፤ ወደ ትክክለኛው ነገር መመለስ አለብን” በማለት በግድያው ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል።