በዓለም ትልቁ እና በዐይን ሊታይ የሚችል ባክቴሪያ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Olivier Gros
በሥነ ሕይወት ባክቴሪያ በዐይን እንደማይታይ ተምረናል።
ባክቴሪያን ለመመልከት አጉሊ መሣሪያ (ማይክሮስኮፕ) እንደሚያሻም ሳይንስ ነግሮናል።
አሁን ግን የእስከዛሬውን ዕይታ የሚለውጥ ባክቴሪያ ተገኝቷል።
ቲዮማርጋሪታ ይባላል። በእንግሊዘኛው "Thiomargarita" ይባላል።
ባክቴሪያው ከዓለማችን ትልቁ ነው። መጠኑም የአንድ ሽፋሽፍት ፀጉር ያህል እንደሆነ ተነግሯል።
በፍሬንች ካረቢያን ውሃ ውስጥ የሰጠመ ዛፍ ላይ ተጣብቆ ነበር ባክቴርያው የተገኘው።
ባክቴርያው እንደ ሌሎች ባክቴርያዎች ሰዎችን ለሕመም የሚያጋልጥ አይደለም።
በአሜሪካ የሚገኘው ላውረንስ በርክሊ ብሔራዊ ቤተ ሙከራ ውስጥ የሚሠራው ዣንማሪ ቮላንድ እንዳለው፣ ባክቴርያው ከሌሎች ባክቴርያዎች 5,000 እጥፍ ይበልጣል።
ባክቴርያው በምድራችን ካሉ ባለ አንድ ሕዋስ ነፍሳት ትልቁ አይደለም።
ካሌርፓ ታክሲፍሎ የተባለው አልጌ ከዚህ ባክቴርያ አሥር እጥፍ ይበልጣል።
በሰው ዐይን መታየት የማይችሉ ጥቃቅን ነፍሳት በሞሉበት ዓለም የዚህ ባክቴርያ መገኘት አስገራሚ ነው።
ባክቴርያው ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው እአአ በ2009 ጉአድሉፔ ውስጥ ነበር። ነገር ግን ሳይጠና እስካሁን ቆይቷል።
በቅርቡ በተደረገበት ምርምር፣ የባክቴርያው ዘረ መል ከሌሎች ባክቴርያዎች የተለየ እንደሆነ ተደርሶበታል።
የባክቴርያዎች ዘረ መል አብዛኛውን ጊዜ በፈሳሽ መልክ ሰውነታቸው ውስጥ ይንሳፈፋል።
ቲዮማርጋሪታ ግን ዘረ መሉን በአንድ የሰውነቱ ክፍል ነው የሚያከማቸው።
ሳይንቲስቶች ይህንን ክፍል ፔፒንስ የሚል ስም ሰጥተውታል።
በአንድ የሰውነት ክፍል ዘረ መልን ማከማቸት በብዛት የሚስተዋለው እንደ ሰው ባሉ አካለ መጠናቸው ግዙፍ በሆነ ፍጥረታት ላይ ነው።
የዚህ ባክቴርያ ዘረ መል በቁጥር ብዙ መሆናቸውም አስገራሚ ያደርገዋል። ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ዘረ መሎች ያሉት ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ህዋሱ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን የጂኖም ቅጂዎች ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, PIERRE YVES PASCAL
በላውረንስ በርክሊ ተመራማሪ የሆነችው ዶ/ር ታንጃ ዎይኬ እንደምትለው፣ 12 ሚሊዮን ዘረ መል በግማሽ ሚሊዮን የጂኖም ቅጂ ሲባዛ አጠቃላይ የዘረ መል ቁጥሩ ወደ 6,000 ጊጋ ወይም ቢሊዮን ይጠጋል።
የሰው ልጅ ጂኖም በመጠን ስድስት ጊጋ ነው።
ስለዚህ የባክቴርያው ዘረ መል የሰው ልጆች ህዋሳት ከሚይዙት መጠን ይበልጣል።
የባክቴርያውን ቁመት የሚጨምሩት የዘረ መል ዓይነቶች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነና ራሳቸውን እንደሚያባዙ በጥናት ተረጋግጧል።
ባክቴርያው በሕይወት ለመቆየት ጠጣር አካልን መጠጋት አለበት።
አትክልት ላይ ተጣብቆ ሲኖር፣ አትክልቱ የሚያመነጨውን ሰልፈር ወደ ስኳር በመለወጥ ሕይወቱን ያስቀጥላል።
ባክቴርያው ላይ ምርምር ያደረገው ፕሮፌሰር ኦሎቨር ግሮስ “ባክቴርያውን ያገኘነው በኦይስተር ዓሣ ሽፋን፣ በቅጠል፣ በግንድ እንዲሁም በጠርሙስ እና በገመድ ላይ ተለጥፎ ነው” ብሏል።
ባክቴርያው ጠጣር ነገር ከተጠጋ በኋላ ኦክስጅን እና ካርቦንዳይኦክሳይድ ለማግኘት የባሕር ውሃ ይፈልጋል።
ስለ ባክቴርያው የተሠራው ጥናት በሳይንስ መጽሔት የዚህ ሳምንት ዕትም ላይ ወጥቷል።
ከዚህ በኋላም ተጨማሪ ጥናቶች መሠራት እንዳለባቸው ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የሚገኘው ሜንሎ ፓርክ ቤተ ሙከራ ውስጥ የምትሠራው ዶ/ር ሻሊሴህ ዴት፣ “ይህ ባክቴርያ ገና ብዙ ያላጠናቻቸው ነፍሳት እንዳሉ ጠቁሞናል” ብላለች።












