በደቡብ አፍሪካ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው ተመዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው የተገኘ ሲሆን፣ አገሪቱ ከሞሮኮ በመቀጠል በአፍሪካ ወረርሽኙ የተገኘባት አገር ሆናለች።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከዚህ በፊት በሽታው መከሰቱን በተመለተ ሪፖርት አልተደረገም።
የአገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ተቋም በጉተንግ አውረጃ የሚኖር የሰላሳ ዓመት ሰው ላይ በሽታው መገኘቱን ገልጿል።
ሰውዬው ከሌሎች ሰዎች ጋር የነበረው ንክኪ እየተጠና ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሌሎች አገራት አለመጋዙም ተረጋግጧል።
በሽታው ወደ ተከሰተባቸው አገራት ሳይጓዙ ወይም በአገር ውስጥ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ሳይኖር በአፍሪካ በበሽታው ሰዎች የሚያዙበትን ምክንያት ለማወቅ ተመራማሪዎች ጥረት እየደረጉ ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዝቅተኛ የመሰራጨት አቅም ያለው በሽታ ሲሆን፣ አብዝቶ የሚከሰተው በጥቅጥቅ ደን በተሸፈኑ እና ዝናብ በሚበዛባቸው ገጠራማ የምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪካ ነው።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ እንደ አይጥ ያሉ እንስሳት ደግሞ በሽታውን ወደ ሰዎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በሚኖር የቅርብ ንክኪ ሊተላለፍ የሚችል ነው። ቫይረሱ በቆሰለ ቆዳ፣ በመራቢያ አካል ወይም በዐይን፣ በአፍንጫ እና በአፍ አማካኝነት ወደ ሰውነት ሊገባ የሚችል ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ቫይረሱን ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ ከወሲብ እንዲታቀቡ ተመክረዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ስርጭት በአፍሪካ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ወይም ሲዲሲ አሳውቋል።
የማዕከሉ ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር አህመድ ኦግዌል ባለፈው ሳምንት በአህጉሪቱ በበሽታው እንደተያዙ የሚጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር በ38 በመቶ፣ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ደግሞ በ12 በመቶ መጨመሩን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በማዕከሉ የዚህ ዓመት መረጃ መሰረት እስካሁን 1,571 ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ እንደተያዙ ተጠርጠረው ነጻ ሲሆኑ 71 ሰዎች ደግሞ በሽታው ተገኝቶባቸዋል።
73 ሰዎች ከበሽታው ጋር በተገናኘ ለህልፈት ተዳርገዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የጤና ስጋት ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ የሚሰጠው ማብራሪያ እየተጠበቀ ነው።
በተጨማሪም የቫይረሱ ስያሜን በመቀየር በሽታው ከአፍሪካ ጋር ተያይዞ እንዳይነሳ እየሰራ ነው።












