የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ ሕግን አጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በጦር መሣሪያ ቁጥጥር ላይ አዲስ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ።
ይህ ሲሆን ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ወትሮም የዲሞክራቶችና የሪፐብሊካንን ጎራ የሚለየው የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ጉዳይ ከረዥም ዘመን ትግል በኋላ ነው ለዚህ የበቃው።
15 የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴዎች ረቂቁን ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል።
ረቂቁ በ65 ድጋፍና በ33 ተቃውሞ አልፏል።
ይህ የሆነው ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የተኩስ እሩምታን የከፈቱ ግለሰቦችን ተከትሎ በርካቶች ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ ነው።
በኒውዮርክ፣ ቡፋሎ ባለፈው ወር በአንድ ሱፐርማርኬት ውስጥ ጥቁሮችን እየነጠለ ተኩስ የከፈተው ወጣት እንዲሁም በቴክሳስ፣ ዩቫልዲ ከተማ፣ በአንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ በድምሩ 31 ሰዎች መገደላቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ይህ ረቂቅ በሚቀጥለው ሳምንት የታችኛው ምክር ቤት ከመከረበት በኋላ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፈርመውበት ሕግ ይሆናል።
ይህም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የሚፈጸም ተግባር ነው።
ምንም እንኳ ይህ ረቂቅ እዚህ ለመድረሱ ብዙ ውጣ ውረድ ቢያይም የታሰበውን ያህል አንጀት አርስ እንዳልሆነ በጉዳዩ ላይ ብዙ ሕዝባዊ ንቅናቄን ሲመሩ የነበሩ ተሟጋቾች እየተናገሩ ነው።
ረቂቁ አያሌ ውስንነቶች አሉበት የሚሉ የሕግ አዋቂዎችም ጥቂት አይደሉም።
ይህ ረቂቅ ሕግ ሆኖ በቅርቡ ሲጸድቅ የጦር መሣሪያ ገዝቼ ማንገት እፈልጋለሁ የሚል ሰው በተለይ ዕድሜው ከ21 በታች ከሆነ የጀርባ ታሪኩ በብርቱ እንዲጠና ይደረጋል።
ከዚህ ሌላ 15 ቢሊዮን ዶላር ከፌዴራል መንግሥት ለግዛቶች ይመደባል።
ይህም ከጦር መሣሪያ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ለሚከናወኑ ሥራዎች በሚል ፈሰስ የሚደረግ ነው።
በተለይም በትምህርት ቤቶች አካባቢ የጥበቃ ቁጥጥርን ለማጠናከር እና ለአእምሮ ጤና ማጎልበቻ መርሐ ግብር ማስፈጸሚያ የሚውል ይሆናል።
ከዚህ ሌላ ግዛቶች የደኅንነት ስጋት ናቸው ብለው ለሚያምኗቸው ግለሰቦች አስቀድመው ትጥቅ ማስፈታትን ያበረታታል።
ይህ “ሬድ ፍላግ” ተብሎ የሚጠራው የሕግ ሐሳብ ፖሊስ፥ ቤተሰብ ወይም የሥራ ባልደቦችም ሊሆኑ ይችላሉ አንድ ግለሰብ ለደኅንነት ስጋት ነው ብለው በጽኑ ካሰቡ፣ የታጠቀውን መሣሪያ እንዲፈታ ጥያቄ የሚያቀርቡበት ዘዴ ነው።
ሌላው በዚህ ረቂቅ የተካተተው “ቦይፍሬንድ ሉፕሆል” በሚል በይበልጥ የሚታወቀው ሐሳብ ሲሆን ይህም ያልተጋቡ ፍቅረኛሞች፣ በመጠናናት ዘመናቸው ምናልባትም ከሁለቱ አንዱ ቀደም ብሎ የጾታ ጥቃት ታሪክ ያለው ሰው ከሆነ ከዚያ ወዲህ መሣሪያ እንዳይታጠቅ የሚከለክል ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከዚህ በፊት የፌዴራል ሕግ ያገቡ፣ ወይም ልጅ ያላቸው ወይም በእጮኛነት ደረጃ ያሉ እና በጾታ ጥቃት ታሪክ ያላቸው ሰዎችን ብቻ መሣሪያ እንዳይታጠቁ ክልከላ ያደርግ ነበር።
አሁን በአዲሱ ረቂቅ ግን ይህ ሕግ አዲስ እየተጠናኑ ያሉ አፍላ ፍቅረኛሞች ጭምር እንዲያካትቱ ተደርጓል።
አሁን በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የመሣሪያ ቁጥጥር ረቂቁ በሰፊ ድጋፍ ማለፉ ልዩ ያደረገው።
በርካታ ሪፐብሊካን እንደራሴዎች ለመሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ ይህን ያህል ድጋፍ ሲሰጡ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
በታሪክ ለዘመናት በዲሞክራቶች ይቀርብ የነበሩ የመሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ የሕግ ሐሳቦች ወዲያውኑ በሪፐብሊካን ተወካዮች ውድቅ ሲደረጉ ኖረዋል።
የዲሞክራት እንደራሴዎች ተጠሪ ቸክ ሹመር “ይህ ረቂቅ ሕግ ማለፉ ሁሉን ችግር ይቀርፋል ባንልም ሐቀኛውን መንገድ መያዛችንን አመላካች ነው” ብለዋል።
የብሔራዊ ጠመንጃ ማኅበር (NRA) ረቂቅ ሕጉን በጽኑ ተቃውሞታል።
ጆ ባይደን ውሳኔው የሚበረታታ ነው ቢሉም እሩምታ ተኩስ መክፈት የሚያስችሉ ዘመናዊ ጠመንጃዎች ላይ ዕቀባ እንዲደረግ የነበራቸውን ፍላጎት አለማሟላቱ ግን ቅር አሰኝቷቸዋል።
በቡፋሎም ሆነ በቴክሳሱ ጥቃት 31 ሰዎች የተገደሉት አከታትለው ጥይት በሚተፉ አውቶማቲክና ከፊል አውቶማቲክ መሣሪያዎችን ገዝተው በታጠቁ ወጣቶች ነበር።
በአሜሪካ አሁን በአማካይ በግለሰቦች እጅ 390 ሚሊዮን ጠመንጃና ሽጉጦች ይገኛሉ።
በ2020 ብቻ 45 ሺህ አሜሪካዊያን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በጦር መሣሪያ ተገድለዋል።












