የልጃቸውን ገዳይ እግር ያጠቡት ኢትዮጵያዊ

አቶ ማቲዎስ ደስታ

የፎቶው ባለመብት, GCIM/FB

የምስሉ መግለጫ, አቶ ማቲዎስ ደስታ

ድፍን የሐዋሳ ሕዝብ ያወቃቸዋል። ያከብራቸዋል። ‘ኢንጅነር’ እያለም ይጠራቸዋል።

‘ኢንጅነር’ የሚለውን ስያሜ በትምህርት ያገኙት አይደለም።

ለሰላሳ ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ በቤት እና ሕንጻ ግንባታዎች በመሳተፋቸው ነዋሪው የሰጣቸው እንጂ።

በሐዋሳም የኮንስትራክሽን ፍቃድ አውጥተው በርከት ያሉ ግንባታዎችን አከናውነው ተመስግነዋል።

‘ኢንጅነር’ በዚህ ብቻ አይደለም የሚታወቁት።

መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አነስተኛ ቢሮ በመክፈት ‘የእርቅ አገልግሎት’ ይሰጣሉ።

‘የእርቅ አገልግሎት’?! - ግር ሊያሰኝ ይችላል። የሐዋሳ ነዋሪ ግን በደንብ ያውቀዋል።

የ‘ኢንጅነር’ እውቅና ግን በዚህ ብቻ አያበቃም። እስከዛሬ ድረስ ‘ጉድ’ እየተባለ የሚወራ ነገር ፈጽመዋል - የልጃቸውን ገዳይ ማረሚያ ቤት ድረስ ሄደው ‘ይቅር ለእግዚያብሔር ብያለሁ’ ብለዋል።

ይቅርታ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እግሩንም አጥበዋል። ነገሩን አንድ በአንድ እንየው!

‘ኢንጅነር’ ማቲዎስ እና ሟቹ ልጃቸው

አቶ ማቲዎስ ደስታ የ85 ዓመት አዛውንት ናቸው። አሁን የሚኖሩት ሐዋሳ ከተማ ይሁን እንጂ ትውልድ እና እድገታቸው ወላይታ ነው።

በወጣትነት ዘመናቸው በመጀመሪያ የብረታ ብረት በመቀጠል የግንባታ ሥራዎች ላይ እየተቀጠሩ ሰርተዋል።

በኋላም በግንባታ ሙያው የያዙትን ልምድ በማጠናከር እና ፍቃድ በማውጣት በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ የግንባታ ሥራን ሲያከናውኑ ኖረዋል። በዚህ ሥራቸው ያልረገጡት የኢትዮጵያ ክፍል የለም።

ከ54 ዓመታት በፊት በ1960 ዓመተ ምህረት ደግሞ ትዳር መሰረቱ።

“በትዳሬ ደርዘን ልጆችን አፍርቻለሁ” የሚሉት አቶ ማቲዎስ ከ12 ልጆቻቸው፣ 12 የልጅ ልጆችን እንዳዩም ይናገራሉ።

ከልጅ ልጇቻቸው አንደኛዋ የሟቹ ልጃቸው የእስራኤል ማቲዎስ ልጅ ነች። አሁን የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን እየተከታተለች ነው።

እስራኤል “በጣም ሙያ ያለው የምወደው ልጄ ነበር” የሚሉት አቶ ማቲዎስ ከአስራ ሁለቱ ልጆቻቸው 5ኛው በሆነው እስራኤል ሞት እጅግ አዝነው እንደነበር ይገልጻሉ።

በ1998 ዓመተ ምህረት አንድ ቀን ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ እስራኤል በሚኖርበት አካባቢ ግጭት እንደተፈጠረ እና ልጃቸውም ጉዳት እንደደረሰበት ለአቶ ማቲዎስና ቤተሰባቸው ይነገራል።

“በዚያን ጊዜ ባለቤቴ በሕይወት ነበረች። ሌሎች ሰዎችም ነበሩ ሮጠው ሄዱ - ለማየት። እኔ ግን ተንበርክኬ ጸለይኩ። ጸሎቴን ጨርሼ ስሄድ ሰዎች ተሰብሰበው ደረስኩ።ልጄም ሕይወቱ እንዳለፈ ተነገረኝ።”

ከዚያ በኋላ ፖሊሶች ስለተፈጸመው ወንጀል ምርመራ አድርገው የሟች ልጃቸውን አስክሬን አምጥተው እንደሰጧቸው የሚያስታውስት አቶ ማቲዎስ፣ በተፈጠረ ጸብ ልጃቸው በስለት ተወግቶ መገደሉን ይናገራሉ።

አቶ ማቲዎስ ደስታ

የፎቶው ባለመብት, GCIM/FB

የምስሉ መግለጫ, አቶ ማቲዎስ ደስታ

“ልጄን የገደልከው አንተ ነህ እኔ ግን አንተን እወድሃለሁ”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የልጃቸው ገዳይ ለፈጸመው ወንጀል አስር ተፈርዶበት ማረሚያ ቤት ገባ። አቶ ማቲዎስ ግን ሐዘንና ቂም ይዘው መቆየት ስላልፈቀዱ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ።

“ወደ ማረሚያ ቤት ሄድኩኝና ሰዎች የልጄን ገዳይ በርቀት አሳየኝ። እኔም እሱ ሳያየኝ ከኋላው ሄድኩና እግሩን ያዝኩት። ደነገጠ ‘ለምን ያዝክ?’ አለኝ። ‘አይ ያንተን እግር ለማጠብ ነው የመጣሁት’ አልኩት።

“‘ለምን?’ አለ፣

“‘ልጄን የገደልከው አንተ ነህ እኔ ግን አንተን እወድሃለሁ’ አልኩት። ‘ልጄን እስራኤልን ገድለሃልና አንተ የኔ ልጅ ትሆናለህ’ አልኩት።

“[ይህንን ሲሰማ] መሬት ላይ ወድቆ ተንከባለለ። አትንከባለል አልኩት። በእጄ ሃይላንድ ይዤ ነበር በዚያ ነው ያጠብኩት። ...ዶክመንት አዘጋጀሁ እና ጉዳዩ ወደ ይቅርታ ቦርድ ሄደ። ከዚያም ተፈታ” ሲሉ የዚያን ጊዜውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

“ሰው እንኳን ልጁን የገደለበትን የሰደበበትን ይቅር ለማለት ሊቸገር እንደሚችል አውቃለሁ” የሚሉት አዛውንቱ አቶ ማቲዎስ ሰዎች ለማመን የሚቸግራቸውን ይህንን ነገር ፈጽመውታል።

ይሄ ነው ሰውን ‘ጉድ’ ያሰኘው። ሰውን ያስገረመው። እውነት አልመስልህ ያለው።

“‘አንተ ይቅርታ ስታደርግ ወንድሞች ልጆች ቤተሰቦች አይቀየሙህም ወይ? ያሉኝ አሉ።

“እኔ ይሄንን አላውቅም አእምሮዬ ውስጥ የተሞላው ይቅር በል የሚል ነገር ነው እንጂ ያን ነገር የሚያውቀው እግዚያብሔር ነው’ ነበር ያልኩት።

“ልጆቼም እግዚያብሔርን ስለሚያመልኩ ሌሎች [ደግሞ] ስለ እኔ ስለሚያውቁ ሌላ ነገር አልተናገሩም” ሲሉ ያስረዳሉ።

ቢቢሲ ይቅርታ ያደረጉለትን ሰው እግር ያጠቡት በምን ምክንያት ነው? ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ጌታ ኢየሱስ እግር አጥቧል። ይሄንን ለማስተማር ነው ራሱን ዝቅ ያደረገው” ስለዚህም በሚያምኑበት እምነት መሰረት ፍጹም ይቅርታ ማድረጋቸውን ለመግለጽ ይህንን ፈጽሜያለሁ ብለዋል።

‘ኢንጅነር’ ይቅርታ ማድረጋቸውን የሰሙት የገዳይ ቤተሰቦች “እርስዎ ይህንን ካደረጉ ምን እናድርግልዎት” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።

እሳቸው ግን “እኔ ዋጋውን ከሰማይ ነው የማገኘው” ብለው ምንም አይነት የውለታ ምላሽ አልተቀበሉም።

ከዚህ በኋላ ከገዳዩም ይሁን ከቤተሰቦቹ ጋር ተገናኝተው አይውቁም። እሳቸው ይቅርታ ያደረጉለትን ሰው ቢያገኙት እና ቢጠይቃቸው ደስ ይላቸዋል። ሆኖም ከዚያ ቀን በኋላ አልተገናኙም።

“ተጠራጥሮ ይሆናል። ይቅርታ ያደረገው ሌላ ነገር አስቦ ይሆናል ብሎ ይሆናል የጠፋው” ብለዋል።

‘ማንም የማይደፍረውን’ ይህንን በማድረጋቸው የመንፈስ እርካታ እንዳገኙ የሚጠቅሱት አቶ ማቲዎስ፣ ውሳኔያቸው በሕይወታቸው “እጅግ ደስተኛ” እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ።

“በአገር ስለሚወራ፣ የእግዚያብሔር ቃል ‘ይቅርታ አድርጉ’ ስለሚል [ያን ስላደረኩ] በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲሉም አክለዋል።

አቶ ማቲዎስ ደስታ እና በስለት ተወግቶ የተገደለው ልጃቸው

የፎቶው ባለመብት, Social Media/ FB

የ‘ኢንጅነሩ’ የእርቅ አገልግሎት

በነገራችን ላይ፣ ኢንጅነሩ በደቡብ ክልል የአገር ሽማግሌም ናቸው።

አቶ ማቲዎስ በመኖሪያ ቤታቸው በከፈቱት ቢሮ አማካኝነት ደግሞ ያለምንም ክፍያ የእርቅ አገልግሎት ይሰጣሉ።

በእርግጥ ይህንን አገልግሎት የጀመሩት ልጃቸው ከመገደሉ እና እሳቸውም ይቅርታ ከማድረጋቸው በፊት ነው። 1995 ዓመተ ምህረት አካባቢ።

አገልግሎታቸው ከሳቸው ስም ጋር በሐዋሳ ከተማ የገነነው ግን ከዚያ ክስተት በኋላ ነው።

‘ይቅር በሉ’፣ ‘ይቅርታም ጠይቁ’፣ ‘ታረቁ’፣ ‘ቂም አትያዙ’ እያሉ ይመክራሉ። በተግባር የተደገፈ ምክር!

ከቤታቸው መግቢያ ላይ ‘የእርቅ አገልግሎት እሰጣለሁ’ የሚል ማስታወቂያ ለጥፈዋል።

በራቸው ደግሞ እርቅ ለሚፈልግ ለየትኛውም ሰው ክፍት ነው።

እሳቸው ይህንን አገልግሎት በሁለት አይነት መልኩ ያከናውኑታል።

አንድ: ሁለት ያልተስማሙ ሰዎች ወደእርሳቸው መጥተው ‘አስማሙን’፣ ‘ፍረዱን’ ይላሉ።

እሳቸውም በቻሉት መንገድ ለማስታረቅ ይሞክራሉ። የማይታበየው ሃቅ ግን የመጡት ሰዎች ቢያንስ በእሳቸው ፊት ተማምነው እና ተስማምተው መውጣታቸው።

ሁለት: የተጣሉ ሰዎች መኖራቸውን ሲሰሙ ተበድያለሁ ብሎ የሚያስበው ሰው ጋር ሄደው እግር ላይ ወድቀው እና እግር አጥበው ይቅርታ እንዲያደርጉ ይለምናሉ።

“ከሳሽ እና ተከሳሽ እኔ ቢሮ ከመጡ በኋላ ከሳሹን ተንበርክኬ እግር አጥባለሁ። እሱ ‘እንደዚህ ያለ ዕድሜ ኖረው፤ እንደዚህ ያለ ኮንትራክተር የነበሩ፤ እንዲህ ያሉ የልጆች አባት ሆነው እግር ያጥባሉ ብለው እሺ’ ይላሉ’” ብለዋል።

ቁጥሩን በትክክል ባያውቁትም የተለያዩ ባለትዳሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በዚህ መልኩ ወደ እርቅ መመለሳቸውን ይናገራሉ።

ለዚህ ሥራዬ “ደመወዝ የማገኘው ከሰማይ ነው” የሚሉት አቶ ማቲዎስ ‘ለሥራ ማስኬጃ’ ልጆቻቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ይገልጻሉ።

ለዚህ አገልግሎት መቼም ቢሆን ገንዘብ እንደማይቀበሉ ገልጸው “ለምሳሌ ቢሮህን ላድስ የሚል ባገኝ ግን አልከለክልም” ይላሉ።

በሐዋሳ በመልካም ስምና ዝናቸው የሚታወቁት ‘ኢንጀነሩ’ አቶ ማቲዎስ እድሜ ቢጫናቸውም ዛሬም ሰዎችን ለማስታረቅ ይተጋሉ።

‘ተጣሉ ተቃቃሩ’፣ ‘ተኳረፉ’፣ ‘ተለያዩ’፣ ‘ተፋቱ’ የሚሉ ቃላትን ፈጽሞ መስማት አይፈልጉም።

ከሰሙት ግን ይወቋቸውም፤ አይወቋቸው ይቅረቧቸውም አይቅረቧቸው እግር ላይ ለመውደቅ፣ እግር ለማጠብ ‘ይቅር በል፣ ይቅር በይ’ ለማለት የ85 ዓመቱ አዛውንት ዛሬም አይሰንፉም።