ቦሪስ ድግስ በመታደማቸው ይቅርታ ቢጠይቁም ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው

የፎቶው ባለመብት, UK Parliament
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮቪድ ወቅት ሕግ ተላልፈው በመገኘታቸው ከፖሊስ ቅጣት ከተላለፈባቸው በኋላ ላይኛው ምክር ቤት ቀርበዋል።
አብዛኛዎቹ የቶሪ እንደራሴዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠይቀዋልና ይታለፉ ብለዋል።
ነገር ግን የተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ መሪ ጌታ ኪር ስታርመር የቦሪስ ይቅርታ "ቀልድ" ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሌሎች ፓርቲዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲወቅሱ ነው ያመሹት።
የቶሪው እንደራሴ ማርክ ሃርፐር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ የማይደረግለት ድርጊት ፈፅመዋል፤ "ሥልጣን ይልቀቁ" ብለዋል።
ሌበር ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱን ዋሽተው ይሆን የሚለውን ለማወቅ ምርመራ እንዲደርግባቸው የሚያስችል ድምፅ አግኝቷል።
በእንግሊዝ ሕግ መሠረት ምክር ቤቱን እያወቁ ማሳሳት ከሥራ ያስባርራል።
ሰባት እንደራሴዎችን ያዋቀረው የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ የጠቅላዩን ድርጊት መርምሮ ጥፋተኛ ከሆኑ ከመንበራቸው ሊያፈናቅላቸው ይችላል።
ነገር ግን አብዛኛዎቹ ወግ አጥባቂ እንደራሴዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆማቸው በድምፅ ብልጫ የኮሚቴውን ውሳኔ ሊሽሩት ይችላሉ።
የቶሪ እንደራሴው ፒተር ቦን፤ ቦሪስ ጆንሰንን ምክር ቤቱን አሳስተዋል ወይ ብለው ጠይቀዋቸው ቦሪስ 'በፍፁም' ሲሉ መልሰዋል።
ባለፈው ሳምንት ፖሊስ ሕግ ተላልፈዋል በሎ የቀጣቸው ቦሪስ ጆንሰን በሥልጣን ዘመናቸው ቅጣት የተላለፈባቸው የመጀመሪያው የዩኬ መሪ ሆነዋል።
ሰኔ 2020፤ ኮቪድ ዓለምን ባሸበረበት ዘመን የልደት ድግስ ታድመዋል ተብለው ባለቤታቸው ኬሪና ቻንስለር ሪሺ ሱናክም ቅጣት ተቀብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ይህን ድግስ የታደሙ ሰዎች ፖሊስ ምርመራውን ሲጨርስ ተጨማሪ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
"ስለኮቪድ ከባድ ስብሰባ እያለብኝ የካቢኔ ክፍል ውስጥ ገብቼ ድግስ መታደሜ ጥፋት ነው ብዬ አላሰብኩም ነበር። ለዚህም ይቅርታ ጠይቃለሁ" ብለዋል ቦሪስ።
የፖሊስ የምርመራ ውጤትንም በፀጋ እንደሚቀበሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙት።
ነገር ግን ኪር ስትራመር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር "ቅቤ የተለወሰ" ነው ብለዋል።
የሌበር መሪው ስትራመር፤ ቦሪስ ጆንሰን የኮቪድ ሕግጋትን በመጣሳቸው የሕዝቡንና የሙያ አጋሮቻቸውን እምነት ሽረዋል ይላሉ።
ስትራመር መጀመሪያ ቦሪስ ጆንሰንን "ዋሾ" ካላቿው በኋላ አፈ-ጉባዔ ጌታ ሊንሴ ሆይል እንደራሴዎች እርስ በርስ ስለዋሾነት እንዲያወሩ አይፈቀድላቸውም ብለዋል።
የሊበራል ዴሞክራት መሪው ጌታ ኤድ ዴቪ በበኩላቸው "የዩኬ ሕዝብ እምነት በማይጥልበት መሪ መመራቱ ያሳዝናል" ብለዋል።
አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ወር ክልላዊ ምርጫ ይጠብቃቸዋል።
ነገር ግን የዩክሬኑ ጦርነት ለቦሪስ ጆንሰን ሲሳይ ይዞ የመጣ ይመስላል።
አሁን ባለው የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት ምክንያት የዩኬ ፖለቲከኞች ከምርጫ በፊት የሥልጣን ሽግግር ያደርጋሉ ተብሎ አይታሰብም።
ከዚህ በፊት ላይኛው ምክር ቤት ቀርበው ሕግ ተላለፈዋል ወይ ተብለው የተጠየቁት ቦሪስ "ሁሉም የኮቪድ ሕግጋትን አክብረናል" ሲሉ መልሰው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድግስ ሲታደሙ የሚያሳይ ምስል ከወጣ በኋላ ደግሞ "ድግስ የሚባል ነገር አልነበረም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ቦሪስ፤ በስተመጨረሻ ድርጊታቸውን አምነው ዶውኒንግ ስትሪት በተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት በተዘጋጀው ድግስ ላይ በመታደማቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።












