የቴሌቪዥን ስርጭቱ ላይ 'ማንችስተር ዩናይትድ የማይረባ' የሚል ጽሑፍ በመታየቱ ቢቢሲ ይቅርታ ጠየቀ

ቢቢሲ በቴሌቪዥን ስክሪኑ ላይ "ማንችስተር ዩናይትዶች የማይረቡ ናቸው" የሚል ጽሑፍ ከታየ በኋላ ይቅርታ ጠየቀ።
ቢቢሲ ይህ ጽሑፍ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ የታየው የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ዘገባ እየተላለፈ ሳለ በስህተት መሆኑን ገልጿል።
የቢቢሲ ዜና አቅራቢዋ አኒታ ማክቬግህ በክስተቱ የተበሳጩ የማንችስተር ዩናትርድ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎችን ይቅርታ ጠይቃለች።
ዜና አቅራቢዋ ስህተቱ ያጋጠመው ስክሪን ላይ እንዴት እንደሚጻፍ እየተለማመደ የነበረ ሰው "በዘፈቀደ የጻፈው" ጽሑፍ ስክሪን ላይ ከወጣ በኋላ ነው ብላለች።
"ከትንሽ ጊዜ በፊት ምናልባት ጽሑፍ የሚቀርብበት የስክሪን ቦታ ላይ አንድ ያልተለመደ ማንችስተር ዩናትድን የተመለከተ ነገር አይታችሁ ሊሆን ይችላል፤ የማንችስተር ደጋፊዎች በሁኔታው እንዳልተበሳጫችሁ ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች።
ዜና አቅራቢያዋ ክስተቱ ያጋጠመው ሙሉ በሙሉ በስህተት መሆኑን ገልጻለች።
ቢቢሲም ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በቴሌቪዢን መስኮቱ ላይ ለመጻፍ የሚረዳው የመለማመጃ ሥርዓት ለጥቂት ሰከንዶች ቀጥታ እየተላለፈ ባለው የቴሌቪዥን ስክሪን ላይ በመውጣት ክስተቱ ማጋጠሙን ገልጿል።
ለዚህም ስህተት ቢቢሲ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።












