ቻይና ጥቃት ከፈጸመች አሜሪካ ታይዋንን እንደምትከላከል ባይደን ተናገሩ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ታይዋን ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ከጥቂት ሳምንታት በፊት ታይዋን ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች

ቻይና “ጥቃት ከፈጸመች” አሜሪካ ታይዋንን እንደምትከላከል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በድጋሚ አስጠነቀቁ።

ፕሬዝዳንቱ ከሲቢኤስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የአሜሪካ ኃይሎች ታይዋንን ይከላከላሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ “አዎ” ብለው መልሰዋል።

እሑድ በተሰራጨው ቃለ መጠይቅ የአሜሪካ ፖሊሲ እንዳልተለወጠ ዋይት ሐውስ በድጋሚ እንዲናገር አስገድዶታል።

የዋሽንግተን ፖሊሲ ሁሌም “ስትራቴጂካዊ አሻሚነት” ያለው ሲሆን ታይዋንን ለመከላከል ቃል ባይገባም አማራጩን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አያስቀርም።

ታይዋን በምሥራቅ ቻይና የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኝ ራስ ገዝ ደሴት ስትሆን ቤይጂንግ የግዛቴ አካል ናት ስትል ትገልጻለች።

በጉዳዩ ላይ ዋሽንግተን ቁርጥ ያለ አቋም ሳትይዝ ለረዥም ጊዜ በዲፕሎማሲያዊ ዥዋዥዌ ተጉዛለች። በአንድ በኩል ከቤይጂንግ ጋር ላላት ግንኙነት መሠረት የሆነውን የአንድ ቻይና ፖሊሲ ታከብራለች።

በዚህ ፖሊሲ ታይዋን የቻይና አካል ስትሆን አቋሙም መገዳደሪያ የለውም። ስለዚህ አሜሪካ ታይዋንን እንደ የተለየ አገር ዕውቅና የማትሰጥ ሲሆን ከደሴቱ ጋር ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም የላትም። ነገር ግን የጠበቀ ግንኙነት ፈጥራለች።

አሜሪካ ከግዛቲቱ ጋር ባላት ውል መሰረት ለታይዋን የጦር መሳሪያ ትሸጣለች። ውሉ ደሴቲቱ ራሷን የምትከላከልበትን መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል ይላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባይደን ከሲቢኤስ ቴሌቪዥን 60 ደቂቃ ከተሰኘው ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ይህንን በድጋሚ አስረግጠዋል።

“የአንድ-ቻይና ፖሊሲ አለ። ታይዋንም ነጻነቷ ላይ ራሷ ትወስናለች። እኛ አንንቀሳቀስም፣ ነፃነታቸውን አናበረታታም። ይህ የራሳቸው ውሳኔ ነው” ብለዋል።

ባይደን ታይዋን ጥቃት ከደረሰባት ለመከላከል ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንደሚኖር በግንቦት ወር ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። ዋይት ሐውስም በፍጥነት አሜሪካ ከረዥም ጊዜ ፖሊሲዋ አትወጣም በማለት በፍጥነት ምላሽ ሰጥቶ ነበር።

አሁንም ዋይት ሐውስ ባይደንን የሚቃረን መግለጫ አውጥቷል። “ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደምም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በቶኪዮ ይህንኑ ተናግረዋል። የታይዋን ፖሊሲ እንዳልተለወጠም ግልፅ አድርገዋል። ይህ እውነት ነው” ብሏል።

ይህ ግን በአንድ ዓመት ውስጥ ፕሬዝደንቱ ከይፋዊ የአገሪቱ አቋም ርቀው ለወታደራዊ እርምጃ ቃል ሲገቡ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በጥቅምት እና በግንቦት ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ለታይዋን 1.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች እና ፀረ ሚሳኤሎች ለመሸጥ ተስማምታለች። ይህም የቻይናን ክፉኛ አስቆጥቷል።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ በነሐሴ ወር በደሴቲቱ ያደረጉት አወዛጋቢ ጉብኝት በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለውን ውጥረት አባብሶታል። ባይደን ጉብኝቱን ቀደም ብለው “ጥሩ ሃሳብ አይደለም” ብለው ነበር።

በምላሹ ቤይጂንግ በታይዋን ዙሪያ ለአምስት ቀናት የቆየ ወታደራዊ ከበባ በማድረግ ልምምድ አካሂዳለች።

ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ደሴቲቱ ሚሳኤል መተኮሱን ብትናገርም ቤይጂንግ ግን ይህንን አላረጋገጠችም። ቻይና የተኮሰችው ሚሳኤሎች ምንም አይነት ስጋት እንዳልፈጠሩ ታይዋን ተናግራለች።

ቀደም ብሎ ተቀርጾ እሑድ በተላለፈው ቃለ መጠይቅ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የኬሚካል ወይም የታክቲካል የጦር መሳሪያ እንዳትጠቀም ባይደን አስጠንቅቀዋል።