ግብፅ የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በፅኑ ትደግፋለች - አል ሲሲ

የፎቶው ባለመብት, presidency.eg
ግብፅ የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በፅኑ እንደምትደግፍ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ለቀናት ጉብኝት ካይሮ ለገቡት የኤርትራ ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
ግብፅ በምታስመርቀው ግዙፍ ሙዚየም ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም እና በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ካይሮ ለገቡት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ፕሬዝዳንት ሲሲ አገራቸው የኤርትራ ደጋፊ መሆኗን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ግብፅን በተደጋጋሚ የጎበኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአሁኑ ጉብኝታቸው በፕሬዝዳንት አል ሲሲ ግብዣ የሚካሄድ ሲሆን፣ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ነው።
ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ተገናኝተው በተወያዩበት ጊዜ አል ሲሲ ግብፅ "የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለመደገፍ ቁርጠኛ" መሆኗን ተናግረዋል።
ይህ የፕሬዝዳንት አል ሲሲ እና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ውይይት የተካሄደው ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ስታነሳው የነበረውን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተወካዮች ምክር ቤት በዝርዝር ኤርትራን በመጥቀስ ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ "ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነው" መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስሩ ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር የቀረችበት ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበር።
በኤርትራ በኩልም በኢትዮጵያ እየተነሳ ያለው ጥያቄ ሉዓላዊነቷን የሚጻረር በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ስትቃወመው ቆይታለች።
ቢሆንም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገሪቱ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገበት መንገድ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና በየትኛው የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ወይም በሕዝቡ ያልተወሰነ መሆኑን በመጥቀስ በንግግር መፍትሔ ሊገኝለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር "በሰላም አብሮ ለማደግ" ፍላጎት እንዳላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አገራቸው የጦርነት ፍላጎት እንደሌላት ነገር ግን ወደ ጦርነት ከተገባ ግን "አስተማማኝ አቅም ስላለን ውጤቱ ግልጽ ነው፤ ማንም አያስቆመንም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን በኤርትራ ላይ የተነጣጠረ ንግግር ካደረጉ ከአንድ ቀን በኋላ ወደ ካይሮ በማቅናት ከግብፁ ፕሬዝዳንት ጋር የተገናኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በተለያዩ ጉዳዮች ጋር መወያየታቸው ተነግሯል።
ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ የምትገኘው ግብፅ ሶማሊያን ጨምራ ባለፈው ዓመት ከኤርትራ ጋር የጋራ ግንባር መፍጠሯ ይታወሳል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ተከትሎ ከኢትዮጵያ በኩል ስጋት የተደቀነባት ኤርትራ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ በኩል የድጋፍ ማረጋገጫ ያገኘች ሲሆን፣ በአሁኑ ጉብኝትም ፕሬዝዳንቱ ይህንኑ በድጋሚ እንዳረጋገጡላቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ሁለቱ መሪዎች በተጨማሪም በጦርነት እየታመሰች በምትገኘው በሱዳን እና በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ሕግ በተለይም የቀጣናው አገራት ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር በውይይታቸው ላይ አጽንኦት መስጠታቸው ተገልጿል።
መሪዎቹ ካይሮ ላይ የተገናኙት ሁለት ዓመት ባለፈው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በምትገኘው ሱዳን ዋነኛ ተፋላሚ የሆነው እና በኤርትራ እና በግብፅ የሚደገፈው የሱዳን ጦር በዳርፉር ከባድ የተባለ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ ነው።
ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ባለፈው ዓመት ጥቅምት የጋራ ግንባር የመሠረቱት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ነበር።
በ1990 ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት አድርገው ለ20 ዓመታት በላይ በፍጥጫ ውስጥ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግንኙነታቸውን አሻሽለው በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ በጋራ አስከ መዋጋት ደርሰው ነበር።
የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ግንኙነታቸው የሻከረው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ተከትሎ የበለጠ ወደተካረረ ሁኔታ ውስጥ ገብተው ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋት ተፈጥሯል።















