"ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው...ማንም አያስቆመንም"- ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቀይ ባሕር እና ከኤርትራ ጋር በተያያዘ "ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው"፤ "ያለን አስተማማኝ አቅም ነው፤ ማንም አያቆመንም" ሲሉ አስጠነቀቁ።

ኢትዮጵይ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ "አይቀሬ" በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "እንዲያሸማግል" እና "መፍትሔ እንዲያመጣ" ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሰኞ ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀይ ባሕር ጉዳይን በተመለከተ ሰፊ ጊዜ ሰጥተው በአጽንኦት ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎቻቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡበት ጊዜም በቀይ ባሕር እና "በሻዕቢያ" ምክንያት ተፈጥሯል ያሏቸውን የፀጥታ ስጋቶች የተመለከቱ ጉዳዮችን አንስተዋል።

ዐቢይ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት የማብራሪያቸው ክፍል የጀመሩት ሁሉም አገር የራሱ "ብሔራዊ ጥቅም" እና "ብሔራዊ ስጋት" እንዳለው በመግለጽ ነው።

እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የሚበየኑት አገራቱ ባላቸው "መረጃ እና ዕውቀት ልክ" እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገራት ይህንን መሠረት አድርገው ዛሬ ብሔራዊ ጥቅም ወይም ስጋት ያሉትን ጉዳይ "ሊያሰፉ" ወይም "ሊያጠቡ" እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

"ኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚመለከት የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘብ የሚያስፈልገው ኢርዕታዊ፣ ኢፍትሐዊ፣ የበደል የመጨረሻው በደል የተፈጸመበት አገር ነው - ኢትዮጵያ። ቢያንስ ይህንን መናገር አትከልክሉን" ብለዋል።

"ጦርነት የለም ማለት፣ የተኩስ ድምጽ አይሰማም ማለት አይደለም" በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "እውነተኛ ፍትሕ ካልተረጋገጠ በማንኛውም ሰዓት ጦርነት ሊፈጠር ይችላል" ሲሉ ተደምጠዋል። "ኢፍትሐዊ እና ኢርዕታዊ ውሳኔ ባለበት ሁኔታ የተሟላ ሰላም ሊፈጠር" እንደማይችልም ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዐቢይ መንግሥታቸው የቀይ ባሕር ጉዳይ "ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልካዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነው" ብሎ እንደሚያምን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ያጣችበት መንገድ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ያነሱት ዐቢይ፤ ውሳኔው "በካቢኔ"፣ "በምክር ቤት" ወይም "የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕዝበ ውሳኔ" ያልስተላለፈው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

"[ቀይ ባሕርን] የሚያክል ነገር ያጣንበት መንገድ የሕጋዊነት ችግር እንዳለበት ማሳያው ተቋሞች አልገቡበትም፣ ካቢኔው አያውቀውም። እንዴት እንዳጣነው የሚያስረዳ አንድ ገጽ ወረቀት ማግኘት አልቻልንም" ሲሉ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ነገር "የኅልውና ጉዳይ" በመሆኑ በቀላሉ እንደማይታይ ገልጸዋል።

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መጥተው ከኤርትራ ጋር ዕርቅ በተፈጸመበት ወቅትም ይህንን ጉዳይ ሲያነሱ እንደነበር ለምክር ቤቱ አስታውሰዋል።

በወቅቱ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በነበረ "ስምምነት" አማካኝነት "ወደ አሰብ የሚሄደው መንገድ እንደተጠረገ" ነገር ግን ጉዳዩ በታሰበው ልክ አለመሳካቱን አንስተዋል።

"[መንገዱን] ከጠገንን በኋላ 'ችግር አለብን ወደቡ ተዳክሟል አሉን'። አሁን አንዳንዶቹ ፀቡ በአንድ ሌሊት የመጣ የሚመስለው አለ። እንደዚያ አይደለም ታሪኩን ስለማንናገረው ነው" ሲሉ በወቅቱ የተፈጠረውን ጠቅሰዋል።

"ወደቡ ችግር አለበት ሲሉ የጋራ ወዳጅ የሆነ አገር ለምነን ጄኔሬተር እና ክሬን በእርዳታ ወደ ኤርትራ እንዲመጣ አድርገን አሰብ ወደብ ሲደርስ የኤርትራ መንግሥት 'አልፈልግም' ብሎ መለሰ። ይሄ ነገር ለካ ተስፋ የለውም የሚለው ያኔ ነው የገባን" ሲሉ ከዚህ ቀደም በይፋ ያልተነገረ ኹነት ይፋ አድርገዋል።

በወቅቱ የተከፈቱት የድንበር መንገዶች የተዘጉትም "ወዲያው" እንደነበር ጠቅሰዋል። በተጨማሪም በወቅቱ መንግሥታቸው "በራሱ ወጪ መስመር ቀጥሎ" ለኤርትራ "የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ" ላቀረበው ጥያቄ "ቆይ እናስብበት" የሚል ምላሽ መሰጠቱን አክለዋል።

የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ ጥያቄ "ምላሽ ለመስጠት ብዙም ዝግጁ" እንዳልነበረ ያነሱት ዐቢይ፤ ይህ የሆነበትን ምክንያት "በግልጽ እንደማያውቁ" አንስተዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር የጀመረው ሂደት "ፈር ለቆ የወጣው" የትግራዩን ጦርነት ባስቆመው "የፕሪቶሪያ ስምምነት" ምክንያት ነው።

"ፕሪቶሪያ ስንፈራረም 'ትክክል አይደለም፣ [ጦርነቱ] ለምን ይቆማል? ህወሓትም፣ ትግራይም ጠቅልለው ካልጠፉ ቀጣናው ሰላም አያገኝም" የሚል ቅሬታ ተነስቷል ሲሉ የኤርትራን መንግሥት ወንጅለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥታቸው የባሕር በር ማግኘት ጥያቄ "በሕጋዊ እና በንግግር ሊፈታ ይችላል" የሚል ሐሳብ እንዳለው ጠቅሰዋል። "በፍጹም የውጊያ መሻት የለንም" ሲሉ የተደመጡት ዐቢይ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ "እንዲያሸማግል" ጥሪ አቅርበዋል።

"ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለራሺያ፣ ለአውሮፓ፣ ለአፍሪካ አሁን በተከረው ምክር ቤት መግለጽ የሚፈገልገው ነገር የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር አክሰስ ጉዳይ አይቀሬ ስለሆነ፣ ቅድሚያ የምንሰጠው ሰላም እና ንግግር ስለሆነ እባካችሁን ሸምግሉን እና መፍትሔ አምጡልን" ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "እናሸማግላችኋለን፣ ሰላም ያስፈልጋል" እያለ "የማዘናጋት" አካሄድ የሚከተል ከሆነ፤ "ጉዳዩ ብዙ የሚሄድ" እንደማይመስላቸው ተናግረዋል።

"በአንድ ቀንም አንመልሰውም፣ በአንድ ቀንም አላጣነውም። በፈጥሯዊ ሂደቱን ተከትሎ ይሄዳል" ብለዋል። ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ያጣቸው "በ30 ዓመት ትግል" እንደሆነ ጠቅሰው፤ መልሶ ለማግኘት ግን "ሌላ 30 ዓመት ያስፈልጋታል ብዬ ግን አላስብም" ብለዋል።

"በተረጋጋ መንገድ፣ በሰከነ መንገድ፣ በውይይት መሄድ በጣም አስፈላጊ ነው። የፈለገ ብንወያይ ግን ለማጣት የፈጀብን 30 ዓመት፣ ለማግኘት ይፈጅብናል ብዬ አላስብም። ጊዜው ግን በቂ ስለሆነ በተረጋጋ መንገድ ማየት ያስፈልጋል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው "ለኤርትራ መንግሥት" ያሉትን መልዕክት አስተላልፈዋል። ኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች "ጥይት አስታላለፊ" እንዳይሆን ጠይቀዋል። የኤርትራ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ "ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን" እንዲያቆም እና "አሜሪካ ተቀምጦ የሚሠራ የጥቁር ገበያ" ምንዛሬ እንዲቀር ሲሉም ተናግረዋል።

እነዚህ ጉዳዮች የሚቀሩ ከሆነ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር "በሰላም አብሮ ለማደግ" ፍላጎት እንዳላት አክለዋል።

"ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለንም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው።... ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሠራም። አሁኑኑ አለመጀመር ማለት ነው" በማለት አስጠንቅቀዋል። "ማንም አይሞትልህም። ሞራል ይሰጥሃል እንጂ አይሞትልህም። መጨረሻ የምትሞተው አንተ ነህ፤ አያዋጣም" ብለዋል።

"ከማንም ጋር ግጭት ለማድረግ ፍላጎት የለንም። ከገባን ግን ግልጽ ነው ውጤቱ። አስተማማኝ አቅም ነው ያለን ማንም አያስቆመንም። ይሄ ግልጽ መሆን አለበት። ግልጽ ነው ውጤቱ። ወደዚያ እንዳንሄድ በኃላፊነት መሥራት አስፈላጊ ይመስለኛል" በማለት ተናግረዋል።

አክለውም "ሚሊዮን ፐርሰንት እርግጠኛ ነኝ፣ ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም፤ ማንም ፈለገም አልፈለገም" ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት አቋማቸውን ገልጸዋል።

በውንጀላ የታጀበው የፕሪቶሪያ ስምምነት ማብራሪያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ያለበትን ይዞታ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ጋር የተያያዘ የሰጡት ማብራሪያ የስምምነቱ አንዱ ፈራሚ የሆነውን ህወሓትን የተመለከቱ ወንጀላዎችን ያዘለ ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ "መሣሪያ መደበቅ፣ ማሠልጠን፣ ማስመረቅ አልተስማማንም። ስምምነቱ የታጠቀው ያስረክባል ነው። መሣሪያ ደብቆ ማስቀመጥ፣ በኮንትሮባንድ ማስገባት በስምምነቱ ላይ የለም" ሲሉ የትግራይ ክልል አመራሮች ላይ ያነጣጠረ ውንጀላ አሰምተዋል።

ማንኛውም ከውጭ አገራት ጋር የሚደረግ ግንኙነት መካሄድ ያለበት በፌደራል መንግሥት በኩል መሆኑን ያነሱት ዐቢይ፤ "እነሱ ከውጭ [አገር መንግሥት] ጋር ምን እያደረጉ ነው?" ሲሉ ውንጀላ አዘል ጥያቄ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በትግራይ ክልል ያሉ ተፈናቃዮች "ራያ ላይ እንደመለስነው፣ ፀለምት ላይ እንደመለስነው፣ ወልቃይት ላይም መመለስ አለበት፤ ይህ የመንግሥት ፅኑ አቋም ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ "ራሱ ሕገ መንግሥቱ ምላሽ አለው። በክልሎች መካከል ድንበር የለም፤ ወሰን ብቻ ነው ያለው. . . ሕገ መንግሥቱ ቀበሌ ግን አያሰምርም" ያሉት ዐቢይ፤ የአከራካሪ አካባቢዎች ጉዳይ መወሰን ያለበት በሕዝበ ውሳኔ መሆኑን አስምረውበታል።

"የወልቃይት ጥያቄ ልዩ አይደለም፤ ሁሉም ጋር ጥያቄ አለ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የወልቃይትም ይሁን በሌሎችም አካባቢዎች ያለው የይገባኛል ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ መመለስ እንዳለበት ተናግረዋል።

ወልቃይት "ከ25 እና 30 ዓመት ጎንደር ከነበረበት ወደ ትግራይ ተካሏል. . .ውጊያው ሲፈጠር ወደዚህ ተመልሷል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄው በሕዝበ ውሳኔ ካልተመለሰ "አንደኛው ደግሞ ጉልበት ሲያገኝ ይወስደዋል" ብለዋል።

"እስካሁን ለወልቃይት ፌደራል መንግሥት በጀት እየመደበ አይደለም" በማለት፣ ይህ የሆነው "ችግሩ ስታልተፈታ" እንደሆነ በመጥቀስ በጀት አለመመደቡ "ትክክል አይደለም" ብለዋል።

"መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ አቅም አለው"

ከወራት በኋላ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው እና ከወዲሁ በአገሪቱ ተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ችግሮች የፈጠሩት ስጋት ያጠላበት የሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጉዳይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ላይ ተዳስሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት አጠቃላይ ምርጫውን ለማከናወን "አቅም አለው" ሲሉ ስለ ደኅንነት ስጋቱ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

"እየተዋጋንም ምርጫ አካሂደናል" ያሉት ዐቢይ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚከናወን አስረግጠው ተናግረዋል።

". . .እንድታሸንፉ እንዲቀናችሁ ምኞቴ ነው" ሲሉም ተለተፎካካሪ ፓርቲዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። "ጠቅልሎ የመውሰድ ፍላጎት እኛ ጋር የለም. . . ሁሉም ነገር በመደመር ነው የሚሆነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ከፀጥታና ደኅንነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ፤ መንግሥታቸው "ችግር አለብኝ" ከሚል የትኛውም ኃይል ጋር "እንደሚወያይ" ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም ከትግራይ ኃይሎች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን አጣቅሰው "የአማራው ሸኔ፣ የኦሮሞውም ሸኔ. . .ተወያይቶ የመጣውን ተቀብለናል" ብለዋል።

በቀጣይም ከታጣቂዎች ኃይሎች ጋር ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስምረውበታል።

"ችግር ካለ እንደ አገር መክረን እንፍታ፣ ሕግ መንግሥት ይቀደድ፣ ባንዲራ ይቀደድ፣ ኢትዮጵያ ትቀደድ የምትሉ ሰዎች በእናንተ ፍላጎት ማድረግ አንችልም" ብለዋል።

ከብሔራዊ ውይይት ባሻገር "ተበድያለሁ" ለሚሉ ወገኖች "የሽግግር ፍትሕ" ለማስፈን መንግሥት ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል።