ቀይ ባሕር በዓለም ንግድ እና ፖለቲካ ላይ ለምን ወሳኝ ቦታ ሆነ?

በቀይ ባሕር ላይ የሚጓዙ ግዙፍ የጭነት መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቀይ ባሕር ላይ የሚጓዙ ግዙፍ የጭነት መርከቦች

ከጥንታዊው ዘመን አንስቶ የባሕር ጉዞ መስመሮች ለፍልሰት፣ ለንግድ እና ለወታደራዊ ዘመቻዎች ወሳኝ ሆነው አሁን ድረስ ዘልቀዋል።

በተለይ ነዳጅ እና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች በከፍተኛ መጠን በግዙፍ የጭነት መርከቦች ለማንቀሳቀስ እና ለማቅረብ የባሕር መስመሮች ዋሳኝ ናቸው። በዓለም ባንክ እና በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት ከ80 በመቶ በላይ የዓለም ሸቀጦች የሚዘዋወሩት በባሕር ላይ ነው።

በዚህም የባሕር ላይ ትራንስፖርት ለዓለም አቀፍ ንግድ፣ ለጥሬ እቃዎች እና በከፊል ለተዘጋጁ እና ላለቀላቸው ምርቶች ዝውውር ወሳኙ መንገድ ነው። ስለዚህም አገራት የሚያስገቧቸውን እና የሚያስወጧቸውን ምርቶች በዋነነት በባሕር በኩል በትላልቅ መርከቦች አማካኝነት የጓጉዛሉ።

በዓለም ዙሪያ ለዚህ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆኑ መስመሮች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ቀይ ባሕር ቀዳሚው ነው።

አህጉረ አፍሪካን፣ እስያን እና አውሮፓን የሚያገናኛው ይህ ባሕር የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ወሳኝ መስመር እንደሆነ ይታመናል።

በቀይ ባሕር ምን አለው?

ቀይ ባሕር የሕንድ ውቅያኖስን እና ሜዲትራኒያን ባሕርን በማገናኘት በተለይም በዓለም ዙሪያ ተፈላጊ የሆነውን ነዳጅ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ለማጓጓዝ አጭር መንገድ በመሆኑ በዓለም ንግድ እና ፖለቲካ ላይ ወሳኝ ቦታ አለው።

በዚህም የተነሳ ባሕሩን ከሚጎራበቱት ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኤርትራ፣ የመን፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ በተጨማሪ ከአካባቢው ርቀው በሌሎች አህጉራት የሚገኙ በርካታ አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አካባቢ ይገኛሉ።

ቀይ ባሕር ረጅሙን በሕንድ ውቅያኖስ በኩል ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ የሚደረገውን የባሕር ላይ ጉዞ በማሳጠር አገራት ቀልጣፋ የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦታቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል።

እንዲሁም ከአውስትራሊያ፣ ከጃፓን፣ ከቻይና፣ ከሕንድ እና ከሌሎችም አገራት የሚገኙ ወሳኝ የቴክኖሎጂ ምርቶች እና ሸቀጦችን የጫኑ ግዙፍ መርከቦች የሚያቋርጡት ወሳኝ የባሕር መስመር ነው።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የዓለማችንን አንድ ጫፍ ከሌላኛው ጋር በሰከንዶች ውስጥ ለማገናኝት እና መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ የመረጃ ማስተላለፊያ ግዙፍ ገመዶች በቀይ ባሕር ወለል ላይ ተዘርግተው ይገኛሉ።

ግጭቶች እና አለመረጋጋት በተደጋጋሚ በሚከሰቱባቸው የአፍሪካ ቀንድ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የባሕረ ሰላጤው አካባቢዎች ላይ ፍላጎት ያላቸው አገራት ለወታደራዊ እንቅስቃሴያቸው ቀይ ባሕር ስልታዊ መስመር ነው።

ካርታ

አጭሩ የንግድ መስመር

ከዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ12 እስከ 15 በመቶው እንዲሁም ከኮንቴይነር ጭነቶች መካከል 30 በመቶውን በየዓመቱ የሚያስተናግደው ቀይ ባሕር፤ በእስያ እና በአውሮፓ አህጉራት መካከል የሚደረግ የመርከብ ጉዞን ወጪ እና ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና የኮንቴይነር ጭነቶች የሚያልፍበት በመሆኑ የዓለማችን ንግድ እና የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ኬላ በመባል ይጠቀዋል።

በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ መካከል በቀይ ባሕር በኩል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ምርቶች በዓመት 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጡ እንደሆነ ይታመናል።

ከእስያ የተነሳ አንድ የጭነት መርከብ በሱዩስ ካናል በኩል በአጭሩ አውሮፓ ለመድረስ ቀይ ባሕርን አቋርጦ ሜዲትራኒያን መድረስ አለበት። ካልሆነ ግን በደቡብ አፍሪካ ጫፍ በኩል ዞሮ መጓዝ ይጠበቅበታል።

በደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ይህ ጉዞ ደግሞ በቀይ ባሕር በኩል ካለው አቋራጭ መንገድ የሰባት ሺህ ኪሎ ሜትሮች ጭማሪ መንገድ አለው። በቀን ሲሰላ ደግሞ ከስምነት አስከ 12 ተጨማሪ የባሕር ላይ ጉዞ ስለሚጠይቅ ወጪው ከፍ ይላል።

የጭነት መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቀይ ባሕር ጂኦፖሊቲካዊ ጠቀሜታ

የቀይ ባሕር መልክዓ መድራዊ አቀማመጥ፣ ከፍተኛ የነዳጅ ምርት የሚወጣበት አካባቢ መሆኑ፣ በሃይማኖት እና በፖለቲካ አኳያም ተቀናቃኝ ኃይሎች ያሉበት ቦታ መሆኑ የአካባቢው አገራት እና የዓለም ኃያላን በአካባቢው ያላቸውን ጥቅም ለማስከበር የቻሉትን ያደርጋሉ።

በደቡባዊው መስመር በኩል የሚመጡ መርከቦች ወደ ቀይ ባሕር የሚገቡበት የባቤል መንደብ ሰርጥ እና በሰሜን ጫፍ ያለው የሱዩዝ መተላለፊያ በሮች ቁልፍ የባሕሩ ቦታዎች ናቸው። በተለይ ትላልቅ የጭነት መርከቦች ጉዞን በመቆጣጠር የዓለም አቀፍ ንግድ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽእኖን የሚያሳድረው በግራ የጂቡቲ፣ በቀኝ ደግሞ የመን የሚቆጣጠሩ የባቤል መንደብ ሰርጥ ወሳኝ ቦታ ነው።

በዚህም ምክንያት የዓለም ወታደራዊ እና የምጣኔ ሃብት ኃያላን እንዲሁም ሌሎች አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እና የመርከቦቻቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር ኃይላቸውን አሰማርተዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ቻይናን ጨምሮ ሌሎች አገራት የቀይ ባሕር መግቢያ በር በሆነው ወሳኝ ቦታ ላይ በምትገኘው ጂቡቲ ውስጥ ወታደራዊ ሰፈር አላቸው። ሩሲያም በአካባቢው ወታደራዊ ሰፈር ለመከፈት ፍላጎት ያላት ሲሆን፣ ቱርክም በሶማሊያ በኩል ወደ ቀይ ባሕር ቀረብ ብላለች።

ካርታ

ቀይ ባሕር እና በዙሪያው ባሉ አገራት ውስጥ ባለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ምክንያት ተፎካካሪ አገራት ተጽእኗቸውን ለማጠናከር ሲሉ በሚያደርጉት ፉክክር የአፍሪካ ቀንድ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እንዲሁም ግጭቶች የማይለየው አካባቢ ነው።

ቀይ ባሕርን በሚጎራበቱ አገራት ውስጥ ግጭት እና አለመረጋጋት በሚከሰት ጊዜ የንግድ እንቅስቃሴ ስለሚስተጓጎል የዓለም ምጣኔ ሃብት መንገጫገጭ ይገጥመዋል። ምክንያቱም ወሳኝ የሆኑት የነዳጅ እና ሌሎች አቅርቦቶች ስለሚስተጓጎሉ እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ ይከሰታል።

አገራትም የጭነት መርከቦቻቸው ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ ምጣኔ ሃብታቸው እንዲረጋጋ እና የሚያስፈልጓቸው አቅርቦቶች በሚፈለገው ጊዜ እና መጠን እንዲደርሳቸው የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ወታደራዊ እርምጃ እስከመውሰድ ይደርሳሉ።

ቀይ ባሕር ወሳኝ የዓለም የኢኮኖሚ የደም ሥር ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመታትም ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ይታመናል።

በዚህ መስመር የሚያጋጥም የትኛውም የደኅንነት ስጋት የጭነት መርከቦች የጉዞ መስመራቸውን እንዲቀይሩ ያስገድዳል።

በቅርቡ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች የምዕራባውያን መርከቦችን ቀይ ባሕር ላይ በመምታት ጉዳት እና የእንቅስቃሴ መስተጓጎል አስከትለዋል።

ይህንንም ለማስቆም በአሜሪካ መሪነት ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ከአካባቢው በሚነሱ የጦር አውሮፕላኖች ተፈጽመዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የጦር መርከብ በቀይ ባሕር ላይ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ ኪንግደም የጦር መርከብ በቀይ ባሕር ላይ

የቀይ ባሕር መጠነ ሰፊ ተጽእኖ

በአሁኑ ጊዜ በቀይ ባሕር ላይ ጉልህ ተጽእኖ ያላቸው አገራት ግብፅ እስራኤል እና ሳዑዲ አረቢያ ናቸው፤ ሌሎቹ በደካማ ኢኮኖሚ፣ በድህነት እና በጦርነቶች ምክንያት ሚናቸው ጠንካራ አይደለም።

የቀይ ባሕር ስትራተጂካዊ ጠቀሜታ ከአካባቢው ባሻገር አስከ ሜዲትራኒያን ባሕር፣ ሱዩዝ ቦይ፣ ሕንድ ውቅያኖስ እና እስከ ባሕረ ሰላጤው የሆርሙዝ ሰርጥ ይደርሳል።

በዚህም ምክንያት የቀጣናው እና ከአካባቢው ርቀው የሚገኙ ሌሎች አገራት በቀይ ባሕር ላይ ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። አዳዲሶቹም በአካባቢው ሚና እንዲኖራቸው የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ።

በእርስ በርስ ጦርነት ስር ያለቸው የየመን ሁቲዎች በመርከቦች ላይ በሚፈጽሟቸው ጥቃት ስጋት የፈጠሩ ሲሆን፣ ባሕሩን የሚዋሰኑ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ያላቸው ነዳጅ እና ጋዝ፣ የባሕር ውስጥ ሃብት፣ የመርከብ እና የወደብ አገልግሎት ተፈላጊነት እየጨመረ ነው።

ለዘመናት ወሳኝ የምጣኔ ሃብት እና የወታደራዊ ትኩረት ማዕከል የሆነው ቀይ ባሕር ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው በርካታ አገራት ጥረት እያደረጉ ነው።

አገራቱ ከቀይ ባሕር ተጎራባች አገራት ጋር ምጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ ስምምነቶች በመድረስ ሚናቸውን እያሰፉ ነው።

ለዚህም ከአካባቢው ርቀው የሚገኙ አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር በአካባቢው የጦር ሰፈር በማቋቋም የባሕር ኃይላቸውን ያሰማራሉ።