"ኢትዮጵያ አሁን ዕዳ ለመክፈል ምንም ዓይነት ችግር የለባትም" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister
የኢትዮጵያ ከአበዳሪ አገራት ጋር ባደረገችው "የተሳካ ንግግር" ምክንያት በአሁኑ ሰዓት "ዕዳ የመክፈል ምንም ዓይነት ችግር" እንደሌለባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ከአበዳሪዎች አገራት ጋር እየተደረገ ባለው ድርድር "አራት ቢሊዮን ዶላር" የዕዳ ሽግሽር እንደሚደረግ "መረጋገጡን" ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 18/2018 ዓ. ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብረሪያ የመጀመሪያ ክፍል ያተኮረው በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነው።
ዐቢይ ያለፈውን 2017 ዓ. ም. "በኢትዮጵያ ታሪክ እና የታሪክ እጥፋት ውስጥ ትላልቅ ጉዳዮችን ያሳካንበት" እና "የስኬት ዓመት" ሲሉ ገልጸውታል።
መተግበር ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ የሆነውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም "አምስት ዋና ዋና ዓላማዎችን" ይዞ እንደተነሳ አስረድተዋል። "ማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማረቅ"፣ "የንግድ እና ኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል፣ ማዘመን" እንዲሁም "የዘርፎችን ምርታማነት እና የመወዳደር አቅም ማሳደግ" የሚሉትን ግቦች በቀዳሚነት ጠቅሰዋል።
የመንግሥትን "የማስፈጸም አቅም መሳደግ" እና "ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓት እና ጥራት ያለው ዕድገትን ማረጋገጥ" የሚሉትን የሪፎርሙ ግቦች እንደነበሩ ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።
ዐቢይ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት የነበሩ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ቁጥሮችን ካለፈው ዓመት ጋር በማነጻጸር በዚህ የሪፎርም ሥራ የተገኙ "ስኬቶችን" አብራርተዋል።
የመንግሥት ገቢ በምን ያህል ደረጃ እንደጨመረ ሲያስረዱ፤ "በለውጡ ጊዜ 170 ቢሊዮን ብር ነበር የመንግሥት ገቢ፤ በዚህ ዓመት አንድ ትሪሊዮን ብር ይጠበቃል" ብለዋል። የኤክስፖርት ገቢ ላይም ጉልህ መሻሻል መኖሩን የገለጹት ዐቢይ፤ "በዚህ ዓመት በአራት ወር ብቻ" የተገኘው ገቢ በ2016 ሙሉ በጀት ዓመት ከተገኘው እኩል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዐቢይ፤ "ኢትዮጵያ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ትገኛለት" የሚለውን ሐሳብ እንደሚስማሙበት ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። ነገር ግን አገሪቱ ያለባት የዕዳ መጠን "ከ23 ቢሊዮን ዶላር" እንደማይበልጥ በመግለጽ፤ የአፍሪካን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት የሚመሩ ሦስት አገራት "ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ ዕዳ እንዳለባቸው" አስረድተዋል።
"የእኛ ዕዳ ከ23 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም። በንጽጽር ሲታይ ያንን ያህል አስደንጋጭ ባይሆንም የእኛ መጥፎ የሆነው ብድር የወሰድንበት መንገድ ነው። አብዛኛው ብድር ኮሚርሻል ብድር ነው" ሲሉ የአገሪቱ የብድር ዓይነት "በአጭር ጊዜ፣ ብዙ መክፈል የሚጠይቅ" መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአበዳሪዎች ጋር ሲያደርግ የነበረው ድርድር አገሪቱ የወሰደችው ኮሜርሻል ብድር "በረዥም ጊዜ የሚከፈል እና ዝቅተኛ ወለድ ያለው" (concessional loan) እንዲቀየር ያለመ እንደነበር ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከመጀመሩ በፊት የዕዳ ጫናው እና የአካፋፈል ሁኔታው "በዚህ ከቀጠለ ልንቸገር እንችላለን" የሚል ስጋት እንደነበረ አንስተዋል። ሪፎርሙ መተግበር ከተጀመረ በኋላ በተደረጉ ድርድሮች ግን "የተሳካ" እንደነበሩ ገልጸዋል።
"በዚህም በሪፎርሙ ምክንያት ከአራት እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ሽግሽግ ተደርጓል። ይሄ ታላቅ ድል ነው። የሪፎርሙ ውጤት ነው" ሲሉ መንግሥታቸው አግኝቶታል ያሉትን ስኬት አሞካሽተዋል።
ከዚህ የዕዳ ሽግሽግ ውስጥ "እስከ አራት ቢሊዮን [ዶላር] ያለው የተረጋገጠ" እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ቀሪ ድርድሮች" መኖራቸውን ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ አሁን ዕዳ ለመክፈል ምንም ዓይነት ችግር የለባትም" ሲሉም ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። "አሁን ዕዳችንን ለማስተዳደር ችግር የለብንም" ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ከያዙ የግል አበዳሪዎች ሲደረግ ስለነበረው እና በዚህ ወር መጀመሪያው ያለ ስምምነት ስለ ተቋረጠው ድርድርም አንስተዋል። ዩሮ ቦንድ አበዳሪዎቹ ኢትዮጵያ ያሉባትን ሌሎች ብድሮች ለማሸጋሸግ ሂደት ላይ ባለችት ማዕቀፍ ውስጥ "መታቀፍ አንፈልግም" የሚል አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል።
አበዳሪዎች ይህንን አቋም የያዙት "ኢኮኖሚያችሁ እያደገ ስለሆነ በሚል" እንደሆነም አክለው ተናግረዋል።
"ዕድገታችንን አጋንነው በማየት፤ 'መክፈል ስለምትችሉ በነበረው መንገድ ቢቀጥል' የሚል ሐሳብ ነው ያነሱት፤ ድርድር እያካሄድን ነው። የእኛ ጥያቄ ደግሞ ሁሉም ብድሮች በኮመን ፍሬምወርክ ማዕቀፍ ውስጥ ገብተው ሽግሽግ ይደረግላቸው ነው" ሲሉ የልዩነት ምንጭ የሆነውን ጉዳይ አብራርተዋል።
የውጭ ምንዛሬ ክምችት "ከለውጡ በፊት" ከነበረው "በአሥር እጥፍ ማደጉ" እንዲሁም ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ምርት የሚገኘው ገቢ "ለመጀመሪያ ጊዜ" ከአገልግሎት ዘርፍ ከሚገኘው ገቢ መብለጡም በስኬትነት ያሰነሷቸው ጉዳዮች ናቸው።
ዐቢይ፤ የዋጋ ግሽበት እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር ወደ "11.7 በመቶ" መውረዱንም ገልጸዋል። "ከሪፎርሙ ዘመን ጀምሮ ዝቅተኛው የሚባለው የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ይሄኛው ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥታቸው በዚህ ዓመት ይህንን ቁጥር "ከ10 በታች እንዲወርድ" እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።















