ከኢትዮጵያ ጋር ያለስምምነት የተለያዩት የ1 ቢሊዮን ዶላር አበዳሪዎች "ሕጋዊ አማራጭ" ሊከተሉ እንደሚችሉ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, BBC/AMENSISA IFA
ኢትዮጵያ በጊዜው ያልከፈለችውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮ ቦንድ በተመለከተ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በግል አበዳሪዎች ኮሚቴ መካከል ሲደርግ የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ።
ገንዘብ ሚኒስቴር ለቀናት በቆየው ንግግር "ጉልህ መሻሻል" መታየቱን ቢገልጽም የአበዳሪዎች ኮሚቴ ግን ድርድሩ "ፍሬ አልባ" ደረጃ ላይ በመድረሱ "ሕጋዊ አማራጭ" ሊከተል እንደሚችል አስታውቋል።
ገንዘብ ሚኒስቴር፤ የብድሩን አከፋፈል ሁኔታ ለማስተካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ያስታወቀው ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 4/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
ከመስከረም 15 እስከ ሰኞ ጥቅምት 3 የተካሄደው ድርድር የጊዜ ገደብ ተቀምጦለት የተከናወነ ነው።
ኢትዮጵያ 6.625 በመቶ ዓመታዊ ወለድ የሚከፈልበት እና በ10 ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የሚመለስ የአንድ ቢሊዮን ብር ቦንድ ለሽያጭ ያቀረበችው በ2007 ዓ. ም. ነበር።
መንግሥት በዓመት ሁለት ጊዜ በሐምሌ እና ታኅሣሥ ወራት እንዲከፍል የሚጠበቅበትን ወለድ እስከ 2015 ዓ. ም. ድረስ ሲፈጽም የቆየ ቢሆንም ከታኅሣሥ 2016 ዓ. ም. አንስቶ ይህንን ግዴታውን አልተወጣም።
በተጨማሪም ቦንዱ በታኅሣሥ 2017 ዓ. ም. ሙሉ በሙሉ መመለስ የነበረበት ቢሆንም ይህም ሳይከናወን ቆይቷል። ኢትዮጵያ ቦንዱ የሚመለስበት ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ከአበዳሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ንግግሮችን አድርጋለች።
በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የተካሄደው የአሁኑ ድርድር ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ 'ዋይት ኤንድ ኬዝ' የተሰኘውን የሕግ አማካሪ እና 'ላዛርድ' የተባለውን የፋይናንስ አማካሪ ይዞ ቀርቧል።
የቦንዱ ገዢዎችን የወከለው የአበዳሪዎች ኮሚቴም በተመሳሳይ ድርድሩ ላይ የተገኘው ከሕግ እና የፋይናንስ አማካሪዎቹ ጋር ነው።
በዚህ ድርድር የቦንዱ አከፋፈል ሁኔታን በተመለከተ የመጀመሪያ ዕቅዷን ያቀረበችው ኢትዮጵያ ስትሆን ኮሚቴውም የራሱን ዕቅድ በማቅረብ ምላሽ ሰጥቷል። በመቀጠልም ኢትዮጵያ የመጨረሻ ያለችውን የብድር አከፋፈል ማስተካከያ ስታቀርብ፤ ኮሚቴውም ተመሳሳዩን አድርጓል።
ኢትዮጵያ በድርድሩ ወቅት፤ ሁሉንም አበዳሪዎችን በእኩልነት ለማስተናገድ በያዘችውን መርሕ ጸንታ እንደቀጠለች በገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
ገንዘብ ሚኒስቴር በታኅሣሥ 2016 ዓ. ም. የሚጠበቅበትን ወለድ ሳይከፍል ቀነ ገደቡ ባለፈ ወቅትም ይህንን መርሕ በምክንያትነት ጠቅሶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Industrial Parks Development Corporation
በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ አማካይነት እንደ ቻይና ካሉ አበዳሪ አገራት የዕዳ ሽግሽግ ለማግኘት ንግግር ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ "ወጥነት እና እኩልነትን ማረጋገጥ" እንደሚፈልግ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለቦንድ አበዳሪዎቹ መከፈል የነበረበትን ወለድ ለማዘግየት የወሰነው፤ ይህንን ውል በመደበኛ አካሄዱ ማስቀጠል እፎይታ እንዲሰጡት ከጠየቃቸው "ሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር የሚደረገውን ውይይት አደጋ ላይ ይጥለዋል" በሚል ነው።
ሦስት ሳምንት ገደማ የቆየው ድርድር፤ ሁለቱ አካላት ፍላጎቶቻቸውን በተመለከተ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ እንዲቋረጥ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።
ገንዘብ ሚኒስቴር "ምንም እንኳን በዚህ ጊዜ በጉዳዮቹ ላይ የመጨረሻ ስምምነት ላይ መድረስ ባይቻልም፤ ኢትዮጵያ ጉልህ የሆነ መሻሻል መመዝገቡን ታምናች" ብሏል።
ተደራዳሪዎቹ እና አማካሪዎቻቸው በድርድሩ ወቅት ለነበራቸው ተሳትፎ እንዲሁም ላሳዩት "ገንቢ ባህሪ እና ግልጽነት" አመሰግኗል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ "በሁለቱ ወገኖች መካከል የቀረውን ክፍተት ለማጥበብ" በቅርብ ጊዜ ውስጥ "ውይይቶች ይቀጥላሉ" የሚል ተስፋ እንዳለውም ገልጿል።
የአበዳሪዎች ኮሚቴው በበኩሉ ኢትዮጵያ "ማሻሻያ የተደረገበት" ሌላ ዕቅድ የምታቀርብ ከሆነ ለድርድር "ክፍት" እንደሆነ መግለጹን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
ሁለቱ አካላት ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ፤ የግል አበዳሪዎች ከአበዳሪ አገራት ጋር በእኩል ዐይን መታየት አለባቸው የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ነው።
ኮሚቴው በአሁኑ ሰዓት ድርድሩ "ፍሬ አልባ" ደረጃ ላይ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱንም ተናግሯል። "የሕግ እርምጃን ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች እያጤነ" መሆኑን እንዳስታወቀም ሮይተርስ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Finance - Ethiopia
ኢትዮጵያ ያቀረበችው የማስተካከያ ዕቅድ ምን ነበር?
ገንዘብ ሚኒስቴር የድርድሩን ያለስምምነት መጠናቀቅ አስመልክቶ ያወጣው ባለ 14 ገጽ መግለጫ፤ የኢትዮጵያ ልዑክ እና የአበዳሪዎች ኮሚቴ ያቀረቧቸውን የብድር ማስተካከያ ዕቅዶች ይዟል።
የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው አበዳሪዎቹ ኢትዮጵያ ያቀረበቸውን የማስተካከያ ሁኔታዎች በብዛት የተቀበሉ ሲሆን በተወሰኑት ላይ ደግሞ ወሳኝ ማስተካከያ እንዲደረግ ፍላጎት አላቸው።
ገንዘብ ሚኒስቴር ካቀረባቸው ነጥቦች አንዱ፤ የአንድ ቢሊዮን ዶላሩ የቦንድ ዋጋ እንዲቀነስ የሚጠይቅ ነው። 'haircut' በመባል የሚታወቀው ይህ ቅናሽ፤ አገራት ያቀረቡት ቦንድ ገበያው ላይ ያለው ዋጋ በሚቀንስበት ወቅት ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
ኢትዮጵያ፤ የአንድ ቢሊዮን ዶላሩ ቦንድ ዋጋ ላይ የ15 በመቶ ቅናሽ ተደርጎ፤ ለአበዳሪዎች የሚመለሰው አጠቃላይ ገንዘብ 850 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን ጠይቃለች።
ለአበዳሪዎች የቀረበው ዕቅድ እንደሚያስረዳው፤ መንግሥት በታኅሣሥ 2016 ዓ. ም. ጊዜ ባለመክፈሉ የተጠራቀመውን በድምሩ 99.3 ሚሊዮን የሆነ ወለድ ከመክፈሉ በፊት አዲስ የቦንድ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ይፈልጋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ ውል እንዲታሰር ጥያቄ ያቀረበው ታኅሣሥ 2017 ዓ. ም. ላይ ሙሉ በሙሉ መመለስ የነበረበት ቦንድ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ለማድረግ ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር፤ አዲሱ የቦንድ ውል ስምምነት ከጥር 2018 ዓ. ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆን እንዲጀምር እና ከሦስት ዓመት በኋላ በ2021 ዓ. ም. እንዲጠናቀቅ ፍላጎት አለው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥም በሦስት ጊዜ ክፍያ 850 ሚሊዮን ዶላሩን ከፍሎ ለመጨረስ አስቧል።
በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የመጀመሪያው 350 ሚሊዮን ዶላር ሚከፈል ሲሆን፤ በ2020 ዓ. ም. ሐምሌ ወር ተመሳሳይ መጠን ያለው ሁለተኛው ክፍያ ይፈጸማል። ቀሪው 150 ሚሊዮን ብር የሚከፈለው በሐምሌ 2021 ዓ. ም. እንዲሆን ተጠይቋል።
አዲሱ የቦንድ ስምምነት ተግባራዊ በሚሆንባቸው ዓመታት አበዳሪዎች ወለድ የሚያገኙ ይሆናል። ይሁን እንጂ መንግሥት እስካሁን ተግባራዊ ሲሆን የነበረውን የ6.625 በመቶ ዓመታዊ ወለድ ምጣኔ እንዲቀንስ ይፈልጋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ያቀረበው አዲስ የወለድ ምጣኔ 6.125 በመቶ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Mayor's Office of Addis Ababa
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ አፈጻጸሟ ጋር የተያያዙ ሁለት የክፍያ ሂደቶችን በዕቅዷ ውስጥ አካትታለች።
ከእነዚህ ሂደቶች አንዱ 'Value Recovery Instrument' የተሰኘው አሠራር ነው። ይህ አሠራር የቦንድ ዋጋ እና የወለድ ምጣኔ የተቀነሰባቸው እንዲሁም የክፍያ ጊዜ የተራዘመባቸው አበዳሪዎች ተጨማሪ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
ይህ አሠራር የቀረበው የአበዳሪዎች ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዕቅድ በሰጠው ምላሽ ላይ ነበር። ገንዘብ ሚኒስቴርም የመጨረሻ ዕቅዱን ሲያቀርብም ይህንን አሠራር አካትቶታል።
በገንዘብ ሚኒስቴር ዕቅድ መሠረት ኢትዮጵያ ከ2019 እስከ 2028 ዓ. ም. ባሉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ የሚኖራት ዓመታዊ ኤክስፖርት አፈጻጸም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ግምት ከፍ ያለ ከሆነ አበዳሪዎች ተጨማሪ ገንዘብ ይከፈላቸዋል።
በእነዚህ ዓመታት ለአበዳሪዎቹ የሚከፈለው ገንዘብ፤ በተጨማሪነት ከተገኘው የኤክፖርት ገቢ 1.5 በመቶ ያህሉ ነው። ይሁን እንጂ በአንድ በጀት ዓመት ውስጥ የሚከፈለው ገንዘብ ከ30 ሚሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ የገንዘብ ሚኒስቴር ዕቅድ ያሳያል።
በጠቅላላው ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ የሚከፈለው ገንዘብም ከ180 ሚሊዮን ዶላር እንዳይበልጥ ሌላ ገደብ ተቀምጦበታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ጋር አያይዞ ያቀርበው ሁለተኛው አሠራር፤ የአገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻም በ2020 በጀት ዓመት ከተጠበቀው በታች ከሆነ ኢትዮጵያ በሦስተኛ ዙር የምትከፍለው 150 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንዲቀንስ የሚጠይቅ ነው።
የአገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻፈም ከዕቅዱ ከ95 በመቶ በታች ከሆነ፤መንግሥት መፈጸም ያለበትን የመጨረሻ ዙር ክፍያ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ያደርገዋል። አፈጻጸሙ ከ85 በመቶ በታች ከሆነ ደግሞ የሚከፍለው 50 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአበዳሪዎች ኮሚቴ ምን ምላሽ ምን ይመስላል?
አበዳሪዎችን የወከለው ኮሚቴ፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን አዲስ የቦንድ ስምምነት ተቀብሎታል።
የቦንዱን የቆይታ ጊዜ እስከ 2021 ዓ. ም. ድረስ ማራዘም፣ በሦስት ዙር የብድር ምለሳ ክፍያ መፈጸም እንዲሁም የወለድ መጠኑን ወደ 6.125 በመቶ መቀነስ የሚሉት ኮሚቴው የተቀበላቸው ነጥቦች ናቸው።
የቦንዱ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲቀነስ የቀረበውን ዕቅድ መጀመሪያ ላይ ተቃውሞ የነበረ ቢሆንም ተቀብሎታል።
ኮሚቴው በኢትዮጵያ ዕቅድ ላይ የተካተቱትን ከወጪ ንግድ አፈጻጸም ጋር ተያያዙ የክፍያ ሁኔታዎችን ደግሞ በሐሳብ ደረጃ ቢቀበላቸውም አሠራራቸው ላይ የራሱን ማስተካከያ አስቀምጧል።
ኮሚቴው፤ ከዕቅድ በላይ የሆነ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በሚኖርበት ጊዜ ለአበዳሪዎች የሚከፈለው የገንዘብ መጠን የተጨማሪው ኤክስፖርት 4.75 በመቶ እንዲሆን ጠይቋል። ይህ የኮሚቴው ዕቅድ ኢትዮጵያ ካቀረበችው በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ነው።
በተጨማሪም አበዳሪዎቹ ይህ አሠራር ወደኋላ ተመልሶ ካለፈው የ2017 በጀት ዓመት እንዲጀምር እና እስከ 2028 ዓ. ም. ድረስ ለ11 ዓመታት እንዲቆይ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በ2017 ከኤክስፖርት ያገኘችው ገቢ 8.3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከመንግሥት ዕቅድ በ82 በመቶ የጨመረ ነው።
አበዳሪዎቹ በ2017 ዓ. ም. ከተመዘገበው ከዕቅድ በላይ የሆነ አፈጻጸም የሚከፈላቸው ተጨማሪ ገንዘብ ጣሪያ 65 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን ይፈልጋሉ። ይህ የገንዘብ ሚኒስቴር ካስቀመጠው የ30 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ጣሪያ በእጥፍ የሚበልጥ ነው።
በተጨማሪም በ11 ዓመታቱ ውስጥ በዚህ አሠራር ሚያገኙት ገንዘብ ላይ የተጣለው ገደብ ኢትዮጵያ ካቀረበችው 180 ሚሊዮን ዶላር ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል ጠይቀዋል።
የአበዳሪዎች ኮሚቴው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በ2020 በጀት ዓመት ዝቅተኛ የሚሆን ከሆነ ተግባራዊ የሚሆነው አሠራር ላይ የራሱን ማስተካከያ አድርጓል።
የመጨረሻውን ዙር ክፍያ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር እና 50 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ የሚደረግባቸውን ሁኔታዎች የተቀበለው ኮሚቴው፤ ይህ አሠራር ግን በአንድ ዓመት የኤክስፖርት አፈጻጸም ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዳይሆን ጠይቋል።
ይልቁንም ካለፈው የ2017 እስከ 2020 ዓ. ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ የሚመዘገበው የአራት ዓመት አፈጻጸም ለስሌት እንዲቀርብ ያለውን ፍላጎት ባቀረበው ዕቅድ ላይ አስፍሯል።















