የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር "ቅዠት" ያለችው ኤርትራ መሪዋ ወደ ግብፅ አቀኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለ ቀይ ባሕር ያደረጉትን ንግግር "ቅዠት" ስትል ያጣጣለችው ኤርትራ መሪዋ ወደ ግብፅ ማቅናታቸው ተገለጸ።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል "የብልጽግና የአሰብ ቅዠት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይመስላል" በማለት የኢትዮጵያን መንግሥት ሲወነጅሉ፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደግሞ ወደ ግብፅ ተጉዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከቀይ ባሕር እና ከኤርትራ ጋር በተያያዘ "ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው፤ ያለን አስተማማኝ አቅም ነው፤ ማንም አያቆመንም" ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር ምላሽ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ለአምስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ወደ ግብፅ ተጉዘዋል።
አቶ የማነ በኤክስ ገጻቸው ላይ "በፕሬዝዳንት አብደል ፋታሕ አል-ሲሲ ግብዣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ግብፅ አቅንተዋል። የጋራ ጠቀሜታ ባላቸው የሁለትዮሽ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ" ሲሉ አስፍረዋል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የፕሬዝዳንት ኢሳያስን የግብፅ ጉብኝት ይፋ ከማድረጋቸው አስቀድሞ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ "የብልጽግና ፓርቲ የአሰብ ቅዠት/ሕመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይመስላል፤ የቅርብ ጊዜው የሕመሙ ተቀጥላ "የሕዝብ ቁጥር ብዛት" ላይ ያተኮረ ነው" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሰኞ ጥቅምት 18/2018 ዓ. ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግሥታቸው የቀይ ባሕር ጉዳይ "ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነው" ብሎ እንደሚያምን አስረግጠዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ያጣችበት መንገድ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ያነሱት ዐቢይ፤ ውሳኔው "በካቢኔ፣ በምክር ቤት ወይም በኢትዮጵያ ሕዝብ በሕዝበ ውሳኔ" ያልተላለፈ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
"[ቀይ ባሕርን] የሚያክል ነገር ያጣንበት መንገድ የሕጋዊነት ችግር እንዳለበት ማሳያው ተቋሞች አልገቡበትም፣ ካቢኔው አያውቀውም። እንዴት እንዳጣነው የሚያስረዳ አንድ ገጽ ወረቀት ማግኘት አልቻልንም" ሲሉ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ነገር "የኅልውና ጉዳይ" በመሆኑ በቀላሉ እንደማይታይ ገልጸዋል።
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር በበኩላቸው ጥቅምት 19/2018 ዓ. ም. በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ". . .እንደተነገረን ከሆነ በኢትዮጵያ ከተሞች ከሚኖረው ሕዝብ አንጻር የኤርትራ፣ አሰብ ነዋሪዎች ውስን ናቸው" ብለዋል።
አያይዘውም "ይህም የብልጽግናን የተንሸዋረረ ስሌት ፍትሐዊ ገጽታ ያላብሳል" ሲሉ ከሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel
"...በምክር ቤት በነበረው ንግግር 'አሰብን ከተሳካ በድርድር ካልሆነ ግን በወታደራዊ ወረራ ስለመያዝ' ተነስቷል" ሲሉ የማነ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ኮንነዋል።
ዐቢይ፤ መንግሥታቸው የባሕር በር ማግኘት ጥያቄ "በሕጋዊ እና በንግግር ሊፈታ ይችላል" የሚል ሐሳብ እንዳለው ጠቅሰው፤ "በፍጹም የውጊያ መሻት የለንም" ብለዋል።
አያይዘውም፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ "እንዲያሸማግል" ጥሪ አቅርበዋል።
"ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለራሺያ፣ ለአውሮፓ፣ ለአፍሪካ አሁን በተከበረው ምክር ቤት መግለጽ የሚፈገልገው ነገር የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር አክሰስ ጉዳይ አይቀሬ ስለሆነ፣ ቅድሚያ የምንሰጠው ሰላም እና ንግግር ስለሆነ እባካችሁን ሸምግሉን እና መፍትሔ አምጡልን" ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "እናሸማግላችኋለን፣ ሰላም ያስፈልጋል" እያለ "የማዘናጋት" አካሄድ የሚከተል ከሆነ፤ "ጉዳዩ ብዙ የሚሄድ" እንደማይመስላቸው ተናግረዋል።
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር በሰጡት ምላሽ "በታሪክም የቅኝ ግዛት መታበይ ምክንያታዊ ገጽታ እንዲላበስ ይደረጋል። 'ከፍተኛ ተልዕኮ አለን፣ የሥልጣኔ ግብ አለን' ይባላል" ብለው አጣጥለዋል።
"የብልጽግና ቂላቂል አካሄድ በዘመናዊ ታሪክ ተሰምቶም አይታወቅም። ከማጭበርበር ሚዛን ልኬትም በላይ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ዐቢይ ቀይ ባሕርን "በአንድ ቀንም አንመልሰውም፣ በአንድ ቀንም አላጣነውም። በፈጥሯዊ ሂደቱን ተከትሎ ይሄዳል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ያጣቸው "በ30 ዓመት ትግል" እንደሆነ ጠቅሰው፤ መልሶ ለማግኘት ግን "ሌላ 30 ዓመት ያስፈልጋታል ብዬ ግን አላስብም" ሲሉም አክለዋል።
"ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለንም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው።... ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሠራም። አሁኑኑ አለመጀመር ማለት ነው" በማለት አስጠንቅቀዋል።
አክለውም "ሚሊዮን ፐርሰንት እርግጠኛ ነኝ፣ ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም፤ ማንም ፈለገም አልፈለገም" ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት አቋማቸውን ገልጸዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ በመጣው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የቃላት ውጊያ የቀይ ባሕር ጉዳይ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖ ቆይቷል።
የትግራይን ጦርነት ካስቆመው የፕሪቶርያ ስምምነት በኋላ በሁለቱ አገራ መካከል ያለው ግንኙነት ክፉኛ ሻክሯል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የፈጠሩ ሲሆን፣ ሶማሊያን ጨምረው የሦስትዮሽ የጋራ ትብብር መመሥረታቸው ይታወቃል።
በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት የውዝግብ ምክንያት ሆኖ የቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ ግብፅ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበውን ክሰ አጠናክራ ቀጥላለች።















