ሩሲያ የምትገድላቸው የዩክሬን የጦር ምርኮኞች ቁጥር እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, Facebook
ዩክሬናዊው የዒላማ ተኳሽ ኦሌክሳንደር ማሪስቭስኪ በሩሲያ የተያዘው ጦርነቱ በተጀመረ ዓመት ነው።
የመጨረሻ ሲጋራውን ጫካ ውስጥ ሲያጨስ የሚያሳይ ቪድዮ ተለቋል። እዛው ቦታ መቃብሩን እንዲቆፍር ተደርጓል።
'ድል ለዩክሬን!' ካለ በኋላ በጥይት ሲመታ ይታያል።
ኦሌክሳንደር በሩስያ ከተገደሉ ብዞ የጦር ምርኮኞች አንዱ ነው።
ያለፈው ጥቅምት በኩርስክ ግዛት በሩሲያ የተያዙ ዘጠኝ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸው ተገልጿል። የዩክሬን ዐቃቤ ሕግ ምርመራ ከፍቷል።
መሬት ላይ ከፊል እርቃናቸውን የተኙ ወታደሮች ምሥልም ወጥቷል።
ከእነዚህ አንዱ የሰው አልባ አውሮፕላን ባለሙያው ሩስላን ሆልቤክኖ መሆኑን ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።
እናቱ ሰስፒሊን ቺሪኒቭ "በውስጥ ሱሪው ነው እሱ መሆኑን ያወቅኩት። እኔ ነኝ የገዛሁለት። ትከሻው ላይ በጥይት የተመታበት ቦታም ይታያል።" ብላለች።
አንገታቸው የተቀላ፣ እጃቸው የኋሊት ታስሮ በሰይፍ የተገደሉና ሌሎችም ዩክሬናውያን ወታደሮችን በተመለከተ የዩክሬን ዐቃቤ ሕግ ምርመራ እያደረገ ነው።
አንድ ቪድዮ 16 ዩክሬናውያን ወታደሮችን ከጫካ እጃቸውን ከፍ አድርገው ከወጡ በኋላ ተደርድረው በአውቶማቲክ ጥይት ሲገደሉ ያሳያል።
አንዳንዶቹን ግድያዎች የቀረጹት የሩሲያ ወታደሮች ናቸው። ሌሎች በዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን የተቀረጹ ናቸው።
ግድያዎቹ የሚፈጸሙት ጫካ ውስጥ ወይም የት መሆኑ በማይታወቅ ቦታ ነው።
የዩክሬን ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ቢያንስ 147 ዩክሬናውያን የጦር ምርኮኞች በሩሲያ ወታደሮች ተገድለዋል።
127 የሚሆኑን ዘንድሮ ነው የተገደሉት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ከአምና ጀምሮ ስልታዊ ግድያ እየተካሄደ ነው። የሚያሳዝነው ቁጥሩ አየጨመረ መምጣቱ ነው። በብዙ አካባቢዎች እየተፈጸመ መሆኑን ያሳየናል። በፖሊሲና በትዕዛዝ የሚፈጸም እንደሆነ ማስረጃ አለ" ሲሉ የዩክሬን ዐቃቤ ሕግ የጦርነት ክፍል መሪ ዩሪ ቤሎስቭ ይናገራሉ።
ሦስተኛው የጄኔቫ ስምምነትና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሕግጋት ለጦር ምርኮኞች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ያሳስባሉ።
የሩስያ ቺቺኒያ መሪ ሮማን ካድየቭ ወታደሮቻቸው የዩክሬን ወታደሮችን "የጦር ምርኮኛ" አድርገው እንዳይዙ አዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሂውማን ራይትስ ዋች የአውሮፓና መካከለኛው እስያ ምክትል ዳይሬክተር ሬቸል ዴንበር እንደሚሉት፣ የዩክሬን የጦር ምርኮኞች እየተገደሉ እንደሆነ ብዙ ማስረጃዎች አሉ።
በሩስያ ወታደሮች ዘንድ ተጠያቂነት አለመኖሩ ዋነኛው ምክንያት ነው ይላሉ።
"ምን ዓይነት ትዕዛዝ ነው እየተላለፈላቸው ያለው? ኮማንደሮቹ የጄኔቫ ስምምነትን ይገልጹላቸዋል? ስለ ጦር ምርኮኞች ይነግሯቸዋል? የሩስያ ኮማንደሮች ስለወታደሮቻቸው ድርጊት ምን ምላሽ ይሰጣሉ? ምርመራ ለማድረግ ምን ያህል ርቀት ሄደዋል? ወይስ ምርመራ ሳይደረግ ይታለፋል? ከፍተኛ አመራሮችም በወንጀል ድርጊት ተጠያቂ እንደሆኑ ያውቃሉ?" ሲሉም ይጠይቃሉ።
ሩሲያ ጉዳዩን እየመረመረች እንደሆነ የሚጠቁም ይፋዊ መረጃ የለም።
ሩሲያ ውስጥ ጉዳዩን ማንሳት ረዥም ዓመታት በእስር ያስቀጣል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የጦር ምርኮኞች "በዓለም አቀፍ መርህ መሠረት" ተይዘዋል ይላሉ።
የዩክሬን ወታደሮች የሩስያን የጦር ምርኮኞች በመግደል ቢከሰሱም፣ ቁጥሩ ከሩሲያ ጋር አይመጣጠንም።
ሂውማን ራይትስ ዋች እንዳለው፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ "በጦር ወንጀልና ሰብአዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ሥር መመርመር ያለባቸው" ግድያዎች ተፈጽመዋል።
የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ወታደሮች ከሚደርስባቸው ስቃይ ሞትን የሚመርጡበት ሁኔታ አለ።
"መቼም ቢሆን እጄን አልሰጥም ብሎኝ ነበር። ልጄ እንዲመለስልኝ የማላደርገው ነገር አይኖርም። ሞቷል ብዬ ማመን አልፈልግም" ስትል የዩክሬን ወታደሩ ሩስላን ሆልቤክኖ እናት ተናግራለች።












