"በብሪታኒያ የእርስ በእርስ ጦርነት ይነሳል" - ባለሀብቱ ኢላን መስክ የብሪታኒያ ጉዳይ የሚያንገበግበው ለምንድነው?

ባለሀብቱ ኢላን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2012 በለንደን እና ኦክስፎርድ የነበረውን የቢዝነስ ጉብኝት አጠናቆ የተመለሰው ኢላን መስክ "ብሪታኒያን እንዴት እንደወደድኳት" ሲል ነበር በትዊተር ገፁ ያጋራው።

እነሆ በ2024 ይህ የመስክ አተያይ የተቀየረ ይመስላል።

"የእርስ በእርስ ጦርነት ይነሳል" . . . "ብሪታኒያ በስታሊን ነው የምትመራው" . . . "የብሪታኒያ ሕዝብ ይህ የፖሊስ አገዛዝ በቅቶታል" የሚሉ አስተያየቶችን መስጠት ጀምሯል።

በተለይ ጠቅልሎ በገዛው የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ገፁ መሰል አስተያየቶችን መስጠቱ የተለመደ ሆኗል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ጀምሮ ከሌሎች የብሪታኒያ ፖለቲከኞች ጋር በይፋ ተጋጭቶ ያውቃል። ለአክራሪ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ድጋፉን ይገልፃል። ሪፎርም ዩኬ ለተባለው ፓርቲ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እንደወሰነ የፓርቲ መሪ ናይጅል ፋራጅ ተናግረዋል።

ለመሆኑ ኢላን መስክ የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው ብሪታኒያ ጉዳይ እንዲህ ያንገበገበው ለምን ይሆን? ማሳካት የሚፈልገውስ ምንድነው?

ቢቢሲ ከራሱ ከኢላን መስክ አንደበት ለመስማት ሙከራ ቢያደርግም ለቃለ-ምልልስ ተጠይቆ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ነገር ግን በኤክስ ገፁ የሚያጋራቸው አስተያየቶች የሚጠቁሙት ነገር አለ።

ራሱን "ቺፍ ትሮል ኦፊሰር" ሲል ይጠራል። በዘመናዊ ቋንቋ "የነቆራ ሥራ አስኪያጅ" ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚሰጣቸው አስተያየቶች የቀልድ ይሁኑ የምር መለየት ያዳግታል።

ለምሳሌ በአንድ ወቅት "ይህች ብሪታኒያ ናት ወይስ የሶቪዬት ሕብረት?" ሲል ጠይቋል። ብሪታኒያ ኮሚኒስት ሀገር ሆናለች ማለቱ አይደለም። ደሞ እንደዛም ዓይነት ሐሳብ አለው።

ብዙውን ጊዜ ሌሎች የኤክስ ተጠቃሚዎች የፃፉትን 'ሪፖስት' ያደርግና "የሚገርም" ነው ይላል። ካልሆነም ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቦ ኢሞጂ ይለጥፋል።

ኢላን መስክ በኤክስ ገፁ 200 ሚሊዮን ገደማ ተከታዮች አሉት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚለጥፋቸውን ሐሳቦች ያጤኑ ሰዎች ፖለቲካዊ አመለካከቱ የገባቸው ይመስላል።

አብዛኛውን ጊዜ ሊበርታሪያን የሚባለውን ፅንሰ-ሐሳብ ያንፀባርቃል። ይህ ሐሳብ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም እና በነፃ ገበያ የሚመራ፤ የዜጎች ግላዊነት መጠበቅ አለበት የሚል ነው።

የመስክ ፖለቲካዊ አመለካከት ማዕከላዊ እና ተራማጅ የሚባሉ ፅንሰ-ሐሳቦችን የሚቃወም ነው።

በዩኬ እየሆነ ያለው ምንድነው?

ባለፈው ክረምት ሶስት ታዳጊ ሴቶች በሰሜን-ምዕራብ እንግሊዟ ሳውዝፖርት ከተማ መገደላቸውን ተከትሎ በመላው ብሪታኒያ ተቃውሞው ተቀስቅሶ ነበር።

ጥቃቱን አድርሷል ስለተባለው ግለሰብ ሐሰተኛ መረጃዎች በኤክስ ተሰራጩ። ይህን ካሰራጩት መካከል ኢላን መስክ ኤክስን ከመግዛቱ በፊት ታግደው የነበሩ የአክራሪ ቀኝ ዘመም አቀንቃኞች ይገኙበታል።

ተቃውሞው እየተጋጋለ መጥቶ ወደ አመፅ ሲቀየር ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር "ለማኅበራዊ ሚድያዎች እና ለሚያስተዳድሯቸው ሰዎች - በኢንተርኔት አመፅ ማነሳሳት በግልፅ ወንጀል መሆኑን ሊያውቁ ይገባል" ሲሉ አስጠነቀቁ።

መስክ ለዚህ መግለጫ የሰጠው ምላሽ አንድ ቃል ነው። "ኢንሴን" የሚል። በግርድፍ ፍቺው "እብደት" እንደማለት ነው።

ከወራት በፊት በዩኬ የተነሳው አመፅ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ከወራት በፊት በሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ የተነሳው አመፅ በመላው ዩኬ ተስፋፍቶ ነበር

ከዚህ ቀጥሎ ነው በብሪታኒያ "የእርስ በእርስ አመፅ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው" ሲል የፃፈው።

አክሎ ስታርመር በፋክላንድ ደሴቶች ለአመፀኞች የሚሆን ማጎሪያ እየገነቡ የሚል ሐሰተኛ ዜና ከአክራሪ ቀኝ ዘመም ፓርቲ መሪ ወስዶ አሰራጨ።

ምንም እንኳ ይህን መልዕክቱን ቢያጠፋውም በወቅቱ በሚሊዮኖች ታይቶ ነበር።

መስክ ጆ ሮጋን ፖድካስት በተባለው ፕሮግራም ላይ ቀርቦ የብሪታኒያ "እስር ቤቶች ከልክ በላይ እየተጨናነቁ ነው" ሲል ተሰማ። ይህ ፕሮግራም በዩቲዩብ 19 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል።

መስክ የመናገር ነፃነት ያሳስበኛል ከሚለው አቋሙ ባሻገር የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጉዳይ እንደሚያስጨንቀው ይገልፃል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አክራሪነትን በተለመከተ አሜሪካዊው ታዋቂ ቀኝ-ዘመም የለጠፈውን አጋርቶ "በዩኬ እየሆነ ያለው ምንድነው?" ሲል ፅፏል።

ከዩኬ ጋር ያለው ቁርኝት ኤክስ ላይ በመፃፍ ብቻ የተገደበ አይመስልም። በቅርቡ ከናይጅል ፋራጅ ጋር ፎቶ ተነስቷል። ጠርቀም ያለ ገንዘብ ሪፎርም ዩኬ ለተባለው ፓርቲ ሊለግስ እንደሆነም ተሰምቷል።

መስክ የብሪታኒያ ጉዳይ ለምን ያሳስበዋል?

የስፔስኤክስ እና ቴስላ የተባሉት ግዙፍ ኩባንያዎች ባለቤት የፖለቲካ አቋሙ እየተቀየረ መምጣቱ እሙን ነው።

ከዚህ ቀደም ራሱን ማዕከል ላይ ያለ ከማለቱም በላይ ለሂላሪ ክሊንተን የምርጫ ዘመቻ ገንዘብ መለገሱ ይታወሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን "ዎክ ማይንድ ቫይረስ" ስለተባለ ሐሳብ ሲያቀነቅን ይሰማል። በሌላ ቋንቋ ተራማጅ ፅንሰ-ሐሳቦችን ይቃወማል ማለት ነው።

በቅርቡ በታተመ መፅሐፍ እና በሰጠው ቃለ-ምልልስ የልጁ ቪቪያን ዊልሰን ከወንድ ወደ ሴት ፆታ መቀየር በዚህ ምክንያት ከልጁ መቆራረጡ ተነስቷል።

አንዳንዶች መስክ ለዩኬ የሚቆረቆረው "ዩኬ ሊበራል ዲሞክራሲ የተወደለባት ሥፍራ ስለሆነች ነው" ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ቢሊየነሩ እንደሚለው ለንግግር ነፃነት የሚታገል ሰው አይደለም ሲሉ ይተቹታል።

መስክን የሚተቹ ሰዎች ባለሀበቱ ቻይናን በተለመከተ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይመክራሉ። ቴስላ የተባለው የኢላን መስክ የመኪና አምራች ኩባንያ በቻይና ትልቅ ገበያ አለው።

በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ኦንላይን ሴፍቲ አክት በተባለ በአውሮፓውያኑ 2023 በወጣው ሕግ መሠረት ቅጣት ሊጣልበት ይችላል። ሕጉ ግዙፍ ማኅበራዊ ሚድያዎች ሕጋዊ ያልሆኑ ይዘቶችን ችላ ካሉ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይቀጣሉ ይላል።

የዓለማችን ቱጃሩ ሰው ምን እያሰበ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም።

ነገር ግን ማኅበራዊ ሚድያውን ተጠቅሞ ፖለቲካዊ አመለካከቱን እያሰራጨ እንዳለ ግልፅ ነው።

ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያለው ውዝግብ ደግሞ የተቋጨ አይመስልም።