በአሜሪካ በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ ጥቃት አራት ሰዎች ሲሞቱ የ14 ዓመቱ ታዳጊ በቁጥጥር ስር ዋለ

በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡ በተካሄደው የሻማ ማብራት ላይ እናትን ልጅ ሲያለቅሱ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡ ረቡዕ የሻማ ማብራት ተካሂዷል

በአሜሪካ አትላንታ ጆርጅያ በሚገኝ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ አራት ተማሪዎች መሞታቸው እና ዘጠኝ መቁሰላቸውን ተከትሎ የ14 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ስር ዋለ።

የጆርጅያ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሁለት ተማሪዎች እና ሁለት መምህራን መሞታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋለው የ14 ዓመት ታዳጊ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ይጠየቃል ብሏል።

በትምህርት ቤቱ ተማሪ የሆነው ኮልት ግሬይ፣ በሁለት የፖሊስ አባላት በትምህርት ቤት ውስጥ ያለምንም ችግር በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑንም ጨምሮ አስታውቋል።

የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ጁድ ስሚዝ ጥቃቱን “ግልጽ ጭካኔ” የተሞላበት ሲሉ ኮንነውታል።

ፖሊስ ጥቃት መድረሱ በተነገረው በደቂቃዎች ውስጥ 1900 ያህል ተማሪዎች ይገኙበታል ወደ ተባለው ትምሀርት ቤት መድረሱ ተገልጿል።

ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ “የሕግ አስከባሪ አካላት በስፍራው በደቂቃዎች ውስጥ ደርሰዋል። በትምህርት ቤቱ ተመድበው የነበሩም ሁለት መኮንኖች ጥቃት አድራሹን ወድያውኑ ተጋፍጠውታል” ብሏል።

አክሎም “ጥቃት አድራሹ ያለምንም ማንገራገር ወድያውኑ ነው እጁን የሰጠው። . . . መኮንኖች ወደ ማረፍያ ቤት ወስደውታል” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።

ምንም እንኳ ጥቃት አድራሹ የ14 ዓመት ታዳጊ ቢሆንም ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ እንደ አዋቂ እንደሚታይ እና በማረሚያ ቤትም አያያዙ እንዲሁ እንደሚሆን ፖሊስ አስታውቋል።

ባለስልጣናት ለጥቃቱ መነሻ የሆነውን ምክንያት ገና አለመለየታቸውን ገልጸው የሕግ አስከባሪ አካላትም “በዚህ ሰዓት ዒላማ የሆነ ሌላ አካል” ስለመኖሩ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

ኤፍቢአይ በበኩሉ በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ይህ ታዳጊ ባለፈው ዓመት በኦንላየን ማንነቱን ሰውሮ ዛቻ በማድረስ ተጠርጥሮ ፖሊስ እንዳናገረው ገልጿል።

በወቅቱ ታዳጊው ኮልት ግሬይ፣ በድረገጽ ላይ "የጠመንጃ ምስል ለጥፌ በትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃት ለማድረስ አላስፈራራሁም" ሲል አስተባብሎ ነበር።

በትምህርት ቤቱ አካባቢ የጸጥታ አካላት እና የሕክምና ባለሙያ መኪኖች ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፖሊስ ጥቃት አድራሹ ምን ዓይነት የጦር መሳርያ እንደተጠቀመ እንዲሁም ምን ያህል ጥይት እንደተኮሰ ያለው ነገር የለም።

ስሚዝ ተጠርጣሪው በማረፍያ ቤት እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ መርማሪዎች ቃሉን መቀበላቸውን አክለው ገልጸዋል።

“ምን እንደተከሰተ እና ለምን እንደተከሰተ ለማወቅ በርካታ ቀናት ይወስድብናል" ሲሉ ምርመራው ረዘም ያለ ጊዜ አንደሚወስድ ተናግረዋል።

ጥቃት የተከፈተበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርካታ የፀጥታ አካላት በፍጥነት የደረሱ ሲሆን፣ ረዘም ላለ ሰዓት ወደ ትምህርት ቤቱ መግባትም ሆነ መውጣት በመከልከሉ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ከመሄዳቸው በፊት በግቢው ውስጥ በሚገኝ የስፖርት ማዘውተርያ ሜዳ ላይ እንዲቆዩ መደረጉ ተገልጿል።

ሲኤንኤን ጥቃት አድራሹ ጋር በአንድ ክፍል ተማሪ የሆነችው ለይላ ሳያርዝን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ተማሪው ከሚማርበት ክፍል ወጥቶ ነው ጥቃት ያደረሰው።

ተማሪው ወደ ሚማርበት ክፍል ሲመጣ በሩ ተዘግቶ የነበረ በመሆኑ በሃይል ሲደበድብ መሳርያ መያዙን ያየ ሌላ ተማሪ እንዳይገባ መታገሉን ተናግራለች።

ጥቃት አድራሹ ወደ መማርያ ክፍሉ መግባት መከልከሉን ተከትሎ ቀጥሎ ወደሚገኘው ክፍል ሄዶ መተኮስ መጀመሩን አክላ ገልጻለች።

አሌክሳንድራ ሮሜሪዬ የተባለች ሌላ ተማሪ በበኩሏ አንድ ሰው መጥቶ ድንገት በሩን በርግዶ ገብቶ ተማሪዎች ላይ መጮህ ሲጀምር መመልከቷን ተናግራለች።

“ከፍርሀቴ እና ከመደንገጤ የተነሳ እጆቼ ሲንቀጠቀጡ አስታውሳለሁ” ያለችው አሌክሳንድራ “ ሁሉም እያለቀሰ ነበር። ሁሉም እህት ወንድሙን ለመፈለግ ይራወጥ ነበር። ጩሀቱ፣ የፈሰሰው ደም እስካሁን ድረስ አእምሮዬ ውስጥ ጥርት ብሎ ይታየኛል” ብላለች።

ማርከስ ኮልማን የተባለ ሌላ የ14 ዓመት ተማሪ በበኩሉ ጥቃት አድራሹ መተኮስ ከመጀመሩ በፊት “ትልቅ ሽጉጥ” ይዞ መመልከቱን ገልጿል።

“ተነስቼ መሮጥ ጀመርኩ፤ መተኮስ ጀመረ፣ ቢያንስ 10 ጊዜ ተኩሷል። አስር ጊዜ ያህል ተኩሷል” ሲል የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግሯል።

ቀጥሎ የሆነውንም ሲናገር “መምህሬ የክፍሉን በር በመቀመጫ ወንበሮች መዝጋት ጀመረ። ከጥቂት ደቂቃ በኋላ አንድ የክፍል ጓደኛዬ ወለሉ ላይ ወድቆ ክፈኛ ደም ሲፈሰው አይቻለሁ” ብሏል። ሌላ ተማሪ ደግሞ እግሯን የተመታች ሲሆን ሌላ ጓዳኛው ደግሞ ሆዱ ላይ ተመትቶ መቁሰሉን ተናግሯል።

የጆርጅያ አገረ ገዢ የሆኑት ብራያን ኬምፕ በኤክስ ገጻቸው ላይ “በመመርያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ክፉ እንዳይነካቸው እጸልያለሁ” ካሉ በኋላ “ ግዛቲቱ ያላትን አቅም ሁሉ አንደሚያሰማሩ” የሚገልጽ መልዕክታቸውን ጥቃቱ እንደተሰማ አጋርተው ነበር።

በምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሳ ላይ የሆኑት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ ጥቃቱን “ ርህራሄ ያልታየበት አሳዛኝ ክስተት” ሲሉ ገልጸውታል።

“ በአገራችን በየዕለቱ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምሀርት ቤት ሲልኩ በሕይወት መልሰው ያገኟቸው መሆን አለመሆኑን ሲያስጨንቃቸው ማየት በጣም ያበሳጫል። እንደዚህ መሆን አልነበረበትም።" ብለዋል።

የሪፐብሊካኑ እጩ ተወዳዳሪ ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ትሩዝ በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “እነዚህ ብርቅዬ ልጆች ከእድሜያቸው በፊት በታመመ ጭራቅ ሕይወታቸው ተቀጥፏል” ብለዋል።

የፌደራል ወንጀል መርማሪዎች ከአካባቢው የፖሊስ ኃይል ጋር በመሆን ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ሜሪክ ጋርላንድ ገልጸዋል።