ሩሲያ ፑቲንን በመተቸት የሚታወቁትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ‘የውጭ ወኪል’ ስትል ፈረጀች

ሚካሄል ካስያኖቭን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሚካሂል ካስያኖቭ ክሬሚሊን በመተቸት ከሚታወቁ ሩሲያውያን አንዱ ናቸው።

የሩሲያ ፍትሕ ሚኒስቴር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካሂል ካስያኖቭን የክሬሚሊን ተቃዋሚዎችን ለመግታት በስፋት ጥቅም ላይ በሚውለው “የውጭ ወኪሎች” ዝርዝር ውስጥ አስገባ።

ፕሬዚደንት ፑቲንን በመተቸት የሚታወቁት ካስያኖቭ እንደ አውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከከፈተች በኋላ ነበር አገሪቷን ለቀው የወጡት።

ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2004 የፑቲን የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ካስያኖቭ፣ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ አውግዘዋል።

የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት ካስያኖቭ አሁን ላይ የሚኖሩት በስደት ነው።

በሩሲያ በርካታ የክሬሚሊን ተቺዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች በውጭ ወኪል ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሰፍሩትን ጨምሮ ስለጽሑፎቻቸው እንዲሁም የገንዘብ ምንጫቸውን በተመለከተ ለባለሥልጣናት ዝርዝር መረጃዎችን መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

በሩሲያ ፖለቲካ ያላቸው ተሳትፎም የተገደበ ነው።

ከሦስት ዓመት በፊት ፑቲን ያጸደቁት ይህ ሕግ፣ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የውጭ ተቋማትን ጥቅም ሊያስጠብቁ ይችላሉ የሚባሉትን የሚመለከት ነው።

ሕጉ ግለሰቦች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን እንደ የውጭ አካላት ወኪል አድርጎ ሊያስፈርጃቸው በሚችለውና አነጋጋሪ በነበረው የቀድሞ ሕግ ላይ ተጨማሪ ሆኖ የወጣ ሲሆን፣ የዲሞክራሲያዊ ሒደትን ያደናቅፋል በሚል በሰብዓዊ ድርጅቶችና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ከፍተኛ ትችት ገጥሞት ነበር።

የፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለው ካስያኖቭ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ያለውን ልዩ ዘመቻ የተቃወሙ ሲሆን የሩሲያን የውጭ እና የአገር ውስጥ ፖሊሲን ማጣጣል ዓላማ ያደረገው ማኅበር ‘የሩሲያ ፀረ ጦርነት ኮሚቴ ውስጥም አባል ነበሩ።

ይህ የውጭ ወኪሎችን የሚመለከተው ሕግ ተግባራዊ የሚሆነው የውጭ የገንዘብ ድጋፍ በሚቀበሉ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችን የነበረ ሲሆን፣ ግለሰቦችን እንዲሁም በውጭ ተፅዕኖ ሥር ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የሩሲያም ሆኑ የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ኢላማ ወደ ማድረጉ ተስፋፍቷል።

ግንቦት ወር ላይ የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በካስያኖቭ የሚመራው ፒፕልስ ፍሪደም ፓርቲ (ፓርናስ) እንዲፈርስ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።

እንደ አውሮፓውያኑ 2015 በክሬሚሊን አቅራቢያ በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉትና ከፑቲን ተቺዎች አንዱ የሆኑት ቦሪስ ኔምሶቭ የተቃዋሚ ፓርቲው አመራር ነበሩ።