ሩሲያ ወደ አውሮፓ የሚፈሰውን የጋዝ ቧንቧ ልትዘጋው ትችላለች ተባለ

የአውሮጳ አገራት የሩሲያ ጋዝ መጠን መቀነሱ አሳስቧቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያ ለአውሮፓ የምታቀርበውን ጋዝ ሙሉ በሙሉ ልታቋርጥ እንደምትችል ተመላከተ። 

ይህን የቅድመ ጥንቃቄ ቃል የተናገሩት የዓለም አቀፉ ኢነርጂ ተቋም ኃላፊ ፋቲህ ባይሮል ናቸው። 

የአውሮፓ ኅብረት አገራት ይህ ከመሆኑ በፊት ከወዲሁ ያስቡበት፣ ቅድመ ዝግጅትም ያድርጉ ብለዋል ኃላፊው። 

ባለፈው ሳምንት በርካታ የአውሮፓ አገራት ሩሲያ የምትልክልን ጋዝ መጠኑ እየቀነሰብን ነው ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል። 

የሩሲያ ባለሥልጣናት ግን ይህ የሆነው ስለተጣላን ሳይሆን በአንዳንድ ቴክኒካዊ ሰበቦች ነው ብለዋል። 

ሩሲያ ዩክሬንን ጨክና ከመውረሯ ቀደም ብሎ አውሮፓ በድምሩ 40 ከመቶ የተፈጥሮ ጋዝ ፍላጎቷን የምታሟላው ከሩሲያ በሚከፈት የጋዝ ቧንቧ ነበር።

አሁን ይህ አሐዝ በ20 እጅ ዝቅ ሳይል አልቀረም። 

ፋቲህ ባይሮል እንደሚሉት ግን ይህ የሩሲያ የጋዝ መጠንን ቀስ በቀስ እያሳነሱ መላክ ሆን ተብሎ የሚደረግና ስልታዊ ነው። 

ይህም የአውሮፓ አገራት ለመጪው ክረምት የሚሆን በቂ የጋዝ ክምችት እንዳያጠራቅሙና በሩሲያ ላይ ያላቸውን የጥገኝነት መጠን ባለበት እንዲቀጥል ለማድረግ ነው።

“ሩሲያ አዋጪ ይሆናል ያለቻቸውን መንገዶች ሁሉ መሞከሯ አይቀርም፤ ይህም የጋዝ ቧንቧውን ሙሉ በሙሉ መዝጋትን አያካትትም አይባልም” ብለዋል ኃላፊው። 

ባለፈው ሳምንት ከ’ኖርድ ስትሪም-1’ መስመር ወደ አውሮፓ የሚፈሰው ጋዝ በመጠኑ እያነሰ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን ይህም በ40 ከመቶ ዝቅ እንዳለ ነው አገራቱ የሚናገሩት። 

ሩሲያ ግን አሁንም ይህን አውቄ አላደረኩም፤ እመኑኝ ትላለች። 

ባለፈው አርብ ለምሳሌ ኤኒ ተብሎ የሚጠራው የጣሊያኑ የኢንርጂ ተቋም ከወትሮው ግማሽ የሚሆን እንኳ ጋዝ ከሩሲያ አልደረሰኝም ሲል ቅሬታ አቅርቦ ነበር። 

የስሎቫኪያና የኦስትሪያ ኩባንያዎችም ተመሳሳይ ቅሬታ ነበራቸው። 

ፈረንሳይ በበኩሏ ከሰኔ 15 ወዲህ ጭራሽ ከሩሲያ የደረሰኝ ጠብ ያለ ነገር የለም ብላለች። 

ፖላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ፊንላንድ፣ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ በሩብል አንከፍልም ስላልን ሩሲያ የጋዝ ቧንቧ ዘግታብናለች ብለዋል። 

አሁን አሳሳቢ እየሆነ የመጣው ሩሲያ ለአውሮፓ አገራት የጋዝ ሥርጭትን ሙሉ በሙሉ ብታቋርጥ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው ነው። 

አንዳንድ አገራት የኑክሊየር ኃይላቸውን ለተወሰነ ጊዜ ዕድሜውን ማራዘም፣ እየተዉት የነበረውን የከሰል ኃይልን እንደገና መጠቀም መጀመር እና ከወዲሁ በቂ የጋዝ ክምችት ለክፉ ጊዜ ማጠራቀም እንደ አማራጭ እያሰቡበት ነው። 

የኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊው ባይሮል እንደሚሉት ከሆነ ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም። 

“አውሮፓ ኃይልን በፈረቃ ለመጠቀም መሰናዳት አለባት” ብለዋል።