ጣሊያን ከዩሮ 2024 ስትሰናበት፤ ጀርመን እና ስዊትዘርላንድ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ስዊትዘርላንድ እና ጀርመን ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል የቻሉ የመጀመሪያዎቹ አገራት ሆኑ።
ስዊትዘርላንድ የ2020 ሻምፒዮናዋን ጣልያንን 2 ለ 0 በመርታት ነው ሩብ ፍጻሜውን መቀላለቀል የቻለችው።
ከጨዋታው ጅማሬ የበላይነት መያች የቻለችው ስዊትዘርላንድ የመጀመሪያውን ጎል በሬሞ ፍሩለር ማግኘት ችላለች።
የመጀመሪያው አጋማሽ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የአምናዋ ሻምፒዮና ጣልያን ተጠናክራ ትገባለች ተብሎ ቢጠበቅም የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ27ኛው ሰከንድ ሩበን ቫርጋስ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ የስዊትዘርላንድን መሪነት ወደ 2 ለምንም አሳድጎታል።
ጣልያን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ 73 ደቂቃ ለመጠበቅ ተገዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአምናዋ ሻምፒዮን ለጎል የቀረበ ሙከራ ያገኘችው የስዊዘርላንዱ ተከላካይ ፋብያን ሻር የመታውን የጭንቅላት ኳስ የጎሉን አግዳሚ ገጭቶ የወጣበት ነው።
ከዚያ በኋላም ጂያንሉካ ስካማካም ያደረገው ሙከራ በተመሳሳይ መንገድ የጎሉን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።
በውድድሩ ላይ ደብዝዛ የቀረበችው ጣልያን ይህ ነው የሚባል ቆይታ ሳታደርግ ከውድድሩ ተሰናብታለች።
ውጤቱን ተከትሎም ስዊትዘርላንድ በሩብ ፍጻሜው ከእንግሊዝና ስሎቫኪያ አሸናፊ ጋር የምትፋለም ይሆናል፡፡
በሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ ጀርመን በደጋፊዎቿ ፊት ዴንማርክን 2 ለ 0 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀሏን አረጋግጣለች።
በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው ያለምንም ጎል ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ዴንማርክ በዮኪም አንደርሰን ቀዳሚ ለመሆን በቅታ ነበር። ሆኖም ጎሉ ሲቆጠር ዴቪድ ራውም ከጨዋታ ውጭ በመሆኑ በቫር ጣልቃ ገብነት ጎሉ ሳይጸድቅ ይቀራል።
ጎሉ የተሻረበት አንደርሰን በደቂቃዎች ልዩነት ኳስ በእጅ በመንካቱ አሁንም በቫር ጣልቃ ገብነት የፍጹም ቅጣት ምት ለጀርምን ተሰጥቶበታል።
የፍጹም ቅጣት ምቱን ካይ ሃቨርትዝ አስቆጥሮ ጀርመንን ቀዳሚ አድርጓል።
ሁለተኛዋን ጎል ለጀርመን ያስቆጠረው ደግሞ ጀማል ሙስያል ነው።
ጀርመን ባላት ጠንካራ የፊት መስመር ታግዛ በመጀመሪያዎቹ አራት ጨዋታዎች 10 ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚ ሆናለች።
ጀርመን በሩብ ፍጻሜው ከስፔን እና ጆርጂያ አሸናፊ ጋር የምትገናኝ ይሆናል።
የጥሎ ማለፉ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ሲቀጥሉ እንግሊዝ ከስሎቫኪያ እና ስፔን ከጆርጂያ እንዲገናኙ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።












