የዓለማችን የንጹህ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ከአየር ውሃን ማመንጨት የሚያስችል ፈጠራ

የፎቶው ባለመብት, Uravu
በአውሮፓውያኑ 2016 ላይ ኮዛሂኮዴ ተብላ የምትጠራው የሕንድ ከተማ በከባድ ድርቅ ስትመታ ነዋሪዎቿ በውሃ ጥም ተቃጥለው ነበር።
በወቅቱ ተማሪ የነበረው ስዋፕኒል ሽሪቫስታቭ “በቀን ሁለት ባሊ ውሃ ነበር የሚደርሰን” ሲል ያስታውሳል።
ምንም እንኳ ከፍተኛ ሙቀት እና ድርቅ በማያጣት ሕንድ የውሃ እጥረት አዲስ ነገር ባይሆንም፤ በኮዛሂኮዴ ከተማ የነበረው ከፍተኛ ሙቀት የከተማዋ ነዋሪዎች ከምንም በላይ ውሃ ይቀድማል እንዲሉ አድርጓቸዋል።
ለውሃ እጥረት መፍትሄ ለመስጠት ጽኑ ፍላጎት የነበረው ሽሪቫስታቭ የአካባቢውን የውሃ እጥረት መቅረፍ አለብኝ ብሎ ተነሳ።
በአንድ ልብ ወለድ ፊልም ላይ የተመለከተውን ሐሳብ ወደ እውነታ ለመቀየር ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ‘ኡራቩ ላብስ’ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያን አቋቋመ።
በዚህም ሦስቱ ወጣቶች ከአየር ላይ ውሃ ለመሰብሰብ አቅደው ተነስተዋል።
የዘረጉት ሥርዓት አየር ላይ ያለን እርጥበት ወደ ውሃ የሚቀይር ነው።
የፀሐይ ብርሃንን ወይም ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይልን በመጠቀም ሙቀት በመፍጠር ከአየር ውስጥ እርጥበት በማውጣት ወደ ውሃ ይቀይራሉ።
ሽሪቫስታቭ እንደሚለው 12 ሰዓት በሚፈጅ ሂደት አንድ ማሽን እስከ 2 ሺህ ሊትር የመጠጥ ውሃ ያመርታል።
ወጣቶቹ ሐሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር ቢችሉም ሥራውን በስፋት ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የቴክኖሊጂ ውጤቶቹ ብዙ መዋዕለ ንዋይ ስለሚጠይቅ ነው።
“ቴክኖሊጂው አዋጭ በሆነ መንግድ ጥቅም ላይ ለማዋል ብዙ ጊዜ እና ገንዘብ እንደሚፈልግ ተረድተናል” የሚለው ሽሪቫስታቭ ፤ “ድጋፍ ያስፈልገናል። እስካሁን ግን የምንፈልገውን ድጋፍ ሕንድ ውስጥ ማግኘት አልቻልንም” ይላል።
በአሁኑ ወቅት በመዝናኛ ኢንደስትሪ ውስጥ ለሚገኙ 40 ደንበኞቻቸው ባልተለመደ መንገድ የሚያርቱትን ውሃ እየሸጡ ይገኛሉ።
“ያለ ትርፍ ወይም ማኅበራዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጅቶች መሥራት ፈልገን ነበር። ግን ይህን ማድረግ የሚያስችል ድጋፍ ማግኘት አልቻልንም። ሰዎች ከቴክኖሊጂ ይሸሻሉ። የሚሠራ አይመስላቸውም። ስለዚህ በንግድ ሥራ ለተሰማሩ በክፍያ አገልግሎት እየሰጠን ነው” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳል።
ከሕንድ በተጨማሪ በተለይ እያደጉ ባሉ አገራት የሚገኙ ዜጎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እየገጠማቸው ይገኛል።
በሚቀጥለው ዓመት 8 ቢሊዮን ከገሚገመተው የዓለም ጠቅላላ ሕዝብ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ የውሃ እጥረት ያጋጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ትንበያ ከሆነ 1.8 ቢሊዮን ሕዝብ ደግሞ ከፍተኛ የውሃ እጥረት በሚኖርባቸው አገራት ይኖራል።
ሕንዳውያኑ ወጣቶች ለውሃ እጥረት ችግር ምፍትሄው ከከባቢ አየር ውሃ የማፍለቅ ቴክኖሎጂ ነው ብለው ያምናሉ።
ይህ የቴክኖሎጂ ሥርዓት በታዳሽ ኃይል ሊንቀሳቀስ የሚችል ኃይል ቆጣቢ ሲሆን፣ ውሃን ተጠቃሚዎች ጋር ለማድረሰም የተለመደው ዓይነት የውሃ መስመር ዝርጋታን አይጠይቅም።
ይህ ደግሞ ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ተጠቃሚዎችን ለመድረስ ተመራጭ ያደርገዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 ላይ ከከባቢ አየር ውሃን የማውጣት ቴክኖሎጂ ገበያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳለው ተገምቶ ነበር። በቀጣይ አስርት ዓመታት የዘርፉ ገበያ ዋጋ ወደ 13.5 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል የግሎባል ማርኬት ኢንሳይት ሪፖርት ያመለክታል።
ከከባቢ አየር ውሃ ማውጣት ሁለት መንገዶች አሉት። የመጀመሪያው ማቀዝቀዝ እና ወደ ጠብታ የመቀየር ሂደትን ይከተላል። ወበቃማ አየር የቅዝቃዜ ደረጃ ላይ ደርሶ የሚፈጠር እርጥበት ወደ ጠብታ ውሃ መቀየር ቀዳሚው ነው።
ከከባቢ አየር ላይ እርጥበትን የመሰብሰብ አቅም ያላቸውን መሳሪያዎችን በመጠቀም እርጥበትን ወደ ሞቃታማ ሥርዓት ውስጥ በማስገባት ውሃ ማምረት ሁለተኛው ሂደት መሆኑን ሽሪቫስታቭ ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Majik Water
መገኛዋ በምሥራቅ አፍሪካ ኬንያ የሆነችው ቤዝ ኮኢጊ ከአየር ላይ እርጥበት በመሰብሰብ ውሃ የሚያመነጩ 40 የውሃ ጄኔሬተሮችን በመጠቀም ደረቅ በሆኑ የኬንያ አካባቢዎች ውሃ ታመርታለች።
ቤዝ እአአ 2017 ላይ ያቋቋመች ‘ማጂክ ዋተር’ የተባለው በጎ አድራጊ ኩባንያዋ በውሃ እጥረት የሚቸገሩ ኬንያውያንን ስቃይ ለመቀነስ የተቋቋመ ድርጅት ነው።
ቤዝ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ተማሪ ሳለች ሰዎች ምግብ ለማብሰል እና ለእጥበት አብዝተው ከሚጠቀሙት ወንዝ የሚቀዳን ውሃ መጠጣት ይቀፋት እንደነበረ ታስታውሳለች።
የቤዝ ትልቁ ጄኔሬተር በ24 ሰዓት 500 ሊትር ውሃ ነው የሚያመነጨው። ውሃ የሚያመነጩት ማሽኖች በትምህርት ቤቶች እና በየመንደሮቹ ተተክለዋል።
ቤዝ ግን ይህ የውሃ እጥረትን ለመቅረፍ ሁነኛ አማራጭ አድርጋ አትመለከተውም። “እውነት ለመናገር ይሄ ለውሃ እጥረት ትክክለኛው መፍትሄ ነው ብዬ አላስብም። ጊዜያዊ መፍትሄ ነው . . . ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያት ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ ነው” ትላለች።
መቀመጫውን በጣሊያን ያደረገው እና በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ከአየር ውሃ የሚያርቱ ማሽኖችን ተክሎ ውሃ የሚሸጠው ቬራጎን ኩባንያ የአንድ ማሽን ዋጋ ከ60 እስከ 70 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደሚገመት ይገልጻል።
ቤዝ በበኩሏ የምትጠቀማቸው ጄኔሬተሮች ዋጋቸው በአማካይ 18 ሺህ ዶላር መሆኑን ትገልጻለች።
በግሎባል ማርኬት ኢንሳይት የጥናት እና ማማከር ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት አቪናሽ ሲንጋህ አምራቾች ከአየር ውሃ የሚያመርቱ ጄኔሬተሮች ኃይል ቆጣቢ ርካሽ እንዲሆኑ እየሠሩ ነው ይላሉ።
ባለሙያው የመንግሥታት ድጋፍ እና የአካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ፖሊሲዎች ቢቀረጹ በዘረፉ ለውጥ ይመጣል ይላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእነ ሽሪቫስታቭ ኩባንያ ኡራቩ ላብስ ማሽኑን ለመገንባት ግብዓት የሚሆኑ ቁሶችን በማሻሻል ወይም ደግሞ ከአየር ወደ ውሃ ለመቀየር በሚደረገው ሂደት ላይ ለውጥ በማምጣት የሥርዓቱን ዋጋ ለመቀነስ እየሠራ ይገኛል።












