በቱጃሮች ዘንድ እየተለመደ የመጣው እጅግ ውዱ የቅንጦት ውሃ

በፊት በፊት ውድ ወይኖች የቱጃሮች ምርጫ ነበሩ። ሠርገኞችም በሻምፓኝ ወይም በፍራፍሬ ጭማቂ ፈንታ በውድ ውሃ ሠርግ ድል አድርገው እየደገሱ መሆኑንስ ሰምተዋል?
ይህ ውሃ ከመደበኛው ማዕድን ወይም የቧንቧ ውሃ እጅግ የላቀ ጥቅም ይሰጣል ይባላል። ለእንዲህ ዓይነቱ አንድ ጠርሙስ ውሃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለመመዥረጥ ይገደዳሉ።
ከስቴክ፣ ከዓሳ ወይንም ከየትኛወም ምግብ ጋር ተጣምሮ እንደ ወይን ይቀርባል።
ከፍተኛ ዋጋ የወጣላቸው እነዚህ ውሃዎች ‘ፋይን ዋተር’ [ምርጥ ውሃ] በመባል ይታወቃሉ። ከእሳተ ገሞራ ድንጋዮች፣ ከሚቀልጥ ግግር በረዶ ወይም እንደጭጋግ ጠብታ ካሉ የተፈጥሮ ምንጮች ይገኛሉ። በቀጥታ ከደመናም ሊገኝ ይችላል።
ሁሉም ውሃ እንደተገኘበት አካባቢ የተለያየ ባህሪ ይኖረዋል። ከተለመደው የታሸገ ውሃ በተለየ መልኩ ሙሉ በሙሉ በፋብሪካ ሂደት ውስጥ ያላለፈ ነው።
በዓለም ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእነዚህ የውሃ ምርት ዓይነቶች አሉ። በጉዳዩ ላይ ምክር ሊሰጡዎት የተዘጋጁ ባለሙያዎችም አሉ።

ውሃ ጣዕም አለውን?
የወይን ቀማሾች አሉ። ይህንን ውድ ውሃ የሚቀምሱ ባለሙያዎችም ብቅ እያሉ ነው። ልክ እንደ ወይን ሁሉ እያንዳንዱን ምርት በማዕድን፣ በጣዕም እና አፍ ላይ በሚፈጥረው ስሜት ይለያሉ።
“ውሃ፣ ውሃ ብቻ አይደለም። በዓለማችን ላይ ያለው እያንዳንዱ ውሃ የተለየ እና የራሱ ጣዕም አለው” ሲል መቀመጫውን በለንደን ያደረገው እና ውሃ ቀማሹ ሚሊን ፓቴል ተናግሯል።
የቧንቧ እና የታሸጉ የውሃ ዓይነቶችን ጨምሮ ስለውሃ ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የቅምሻ ትምህርት ይሰጣል።
ሰዎችን በተለይም ወጣቱን ትውልድ ስለተለያዩ የውሃ ዓይነቶች እና ጣዕሞች የማስተማር ተልዕኮ ላይ መሆኑን ፓቴል ለቢቢሲ ተናግሯል።
“በትምህርት ቤት ስለ ተፈጥሯዊ የውሃ ዑደት፣ ትነት፣ እርጥበት እና ዝናብ ተምረናል” ብሏል።
“ዝናብ መሬት ላይ ካረፈ በኋላ በተለያዩ ቋጥኞች እና አፈር ውስጥ ዘልቆ በመግባት እንደ ካልሲየም፣ ማግኒዥየም፣ ፖታሲየም፣ ሲሊካ እና የመሳሰሉትን ማዕድናት ያገኛል። ይህ ሂደት ነው ለውሃው ጣዕም የሚሰጠው” ሲል ፓቴል አክሏል።

ከበረዶ ወይም ዝናብን ከመሳሰሉ ምንጮች የሚገኘው ውሃ ከምንጭ እና ከጉድጓድ ውሃ አንጻር ጠጣር አካላትን የማሟሟት ደረጃው ዝቅተኛ ይሆናል።
ፓቴል በጠርሙስ እስከ 318 ዶላር ከሚያወጣ ምርጥ ውሃ እስከ ከቧንቧ ውሃ ድረስ ከዓለም ዙሪያ የተገኙ የተለያዩ ዓይነት የውሃ ስብስቦች አሉት።
በሚያሰለጥንበት ወቅት ሰዎች ውሃን ከቀመሱ በኋላ፣ እያንዳንዱ ውሃ እንዴት የተለየ ጣዕም እንዳለው ለመግለጽ ይሞክራሉ።
“ውሃን ጣዕም የሌለው ብቻ እንዳልሆነ ለማሳየት ዕድል እንሰጣቸዋለን። ውሃ ማወቅ እና በጥንቃቄ መጠጣት ስትጀምሩ በሚፈጥራቸው የጣዕም ስሜቶች ትገረሙ ይሆናል። ለስላሳ፣ ክሬም፣ የማይሻክር፣ መራራ እና አንዳንድ ጊዜም ጎምዛዛ የሚሉ ቃላትን እናገኛለን። እኔ አኳታስቲዮሎጂ ብዬ እጠራዋለሁ።”
“ብዙ ሰዎች ‘ይገርማል፣ ይህ ልጅነቴን ያስታውሰኛል’፣ ‘ይህ በዓላትን ያስታውሰኛል’ ወይም ‘ይህ የአያቶቼን ቤት ያስታውሰኛል’ ይላሉ” ሲልም አክሏል።
ውሃ የመቅመስ ውድድር
የፋይን ዋተር ሶሳይቲ በየዓመቱ ይሰበሰባል። ከቡታን እስከ ኢኳዶር ከዓለም ዙሪያ ያሉ የተወጣጡ የፋይን ውሃ አምራቾችን ያሰባስባል። እናም ዓለም አቀፍ የቅምሻ ውድድሮችን ያሰናዳል።
በዓመታዊው ጉባኤ ላይ የሚሳተፉት አብዛኞቹ በቤተሰብ ከሚተዳደሩ የንግድ ድርጅቶች ነው። ውሃን የሚያመርቱ ደግሞ ሩቅ አካባቢዎች በመሄድ ነው።

“የውሃ መቅመስ ውድድር መጀመሪያ ላይ በጣም አስቂኝ ሃሳብ ተደርጎ ይወሰድ ነበር” ሲሉ የፋይን ዋተር ሶሳይቲ እና ፋይን ዋተር አካዳሚ መሥራች ዶ/ር ማይክል ማስቻ ገልጸዋል።
“ሂደቱን የጀመርኩት ከ20 ዓመት በፊት አልኮል መጠጣት ሳቆም ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ወይኑ በድንገት ሲቆም ጠረጴዛውን ዞር ብዬ ተመለከትኩኝ እና በድንገት ከዚህ በፊት አይቼው የማላውቀው የጠርሙስ ውሃ አየሁኝ። ምናልባት የማወቅ ጉጉቴን ተጠቅሜ በወይን ምትክ ውሃ ላይ ማተኮር እችላለሁ ብዬ አሰብኩ” ሲሉም አክለዋል።
ፋይን ዋተር ጥምን ከመቁረጥ የበለጠ ነገርን ይሰጣል ብለውም ያምናሉ።
ሰዎች ለየት ያለ ነገር እንዲመረምሩ፣ እንዲካፈሉ እና እንዲዝናኑበት ዕድልን ይፈጥራል። ከወይን በተለየ መልኩም እርስዎም ከልጆችዎ ጋር ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ነው።
አሁን ለውሃው ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ዶ/ር ማስቻ ይናገራሉ። በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ለስላሳ መጠጦችን እና አልኮሎችን መውሰድ እየቀነሰ እና ይበልጥ ወደ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ማተኮርን እንደምክንያት ያቀርባሉ።
እነዚህ ብርቅዬ ውሃዎች ከወይን ጋር በሚመሳሰል መልኩ ለገበያ እንዲቀርቡ አስችሏቸዋል። ይህም ይበልጥ ማራኪ እንዲሆኑ ረድቷል።

ውሃ እና ምግብ
በስፔን እና በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ አንዳንድ ምግብ ቤቶች የተወሰኑ የውሃ ዓይነቶችን ከምግቦቻቸው ጋር ያጣመረ አማራጭ እያቀረቡ ነው።
“በአሜሪካ ላለው ባለሦስት ኮከቡ ሚሼሊን ሬስቶራንት የውሃ ሜኑ እያዘጋጀሁ ነው። ከ12 እስከ 15 በጥንቃቄ የተመረጡ ውሃ ካለው ምግብ እና ድባብ ጋር በሚሄድ መልኩ ለማቅረብ አቅደናል” ብለዋል ዶክተር ማስቻ።
“ዓሣ ሲያዙ ስቴክ ከሚያዙበት ጊዜ የተለየ ውሃ ይቀርብልዎታል። ዓሳ ሲመገቡ ውሃው ዝቅተኛ ማዕድን ሊኖረው ይገባል።”
ዶ/ር ማስቻ ከወይን ዓይነቶች ይልቅ የውሃ ዓይነቶችን ከሚያቀርቡ እጅግ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶች እና አፓርታመነቶች ጋር ይሠራሉ።
እንደ ዶ/ር ማስቻ ከሆነ ይህ ውሃ በተለይም በሠርግ ወቅት በሃይማኖታዊ ምክንያቶች አልኮልን በሚከለክሉ ባህሎች ዘንድ ተወዳጅ ነው። ውድ ሻምፓኝን በመተካትም ጥሩ የስጦታ አማራጭ ነው ብለዋል።
ይህንን የሚተቹ ግን አልጠፉም።

“ከሥነ ምግባር አንጻር ስህተት ነው”
በዓለም ዙሪያ ንፁህ ውሃ ለማግኘት የሚንከራተቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ይህን ብዙዎች ያልደረሳቸውን መሠረታዊ ነገር ወደ ገንዘብ መቀየሩን ይተቻሉ።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት እአአ በ2022 ብቻ 2.2 ቢሊዮን ሰዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ አያገኙም።
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 703 ሚሊዮን የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ መሠረታዊ የውሃ አገልግሎት እንኳን የላቸውም።
ሌሎች ተቺዎች ደግሞ ይህ ዘመን አመጣሽ ፋሽን ማጭበርበሪያ ብቻ ነው ብለው ይከራከራሉ። ውሃ ውሃ ነው በማለት።
ከዋጋው ውጪ በሚጠጣ የቧንቧ ውሃ፣ የታሸገ ውሃ እና ፋይን እየተባለ በሚጠራው ውሃ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የትኛውም የታሸገ ውሃ መያዣ መጨረሻው ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ነውና በምድራችን ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነም ይገልፃሉ።
በለንደን የግሬሻም ኮሌጅ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮፌሰር የሆኑት ካሮሊን ሮበርትስ በተለይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ንጹህ ውሃ ለማግኘት በሚቸገሩበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለአንድ ጠርሙስ ውሃ ማውጣት ሥነ ምግባር የጎደለው ነው ብለው ያምናሉ።
“ከሰዎች ጋር ለእራት ስትወጣ ሃብትህን እንደማሳየት ያህል ነው። ‘እኔ ከአንታርክቲካ ወይም ከሃዋይ ለተገኘው ለዚህ አስደናቂ ውሃ እከፍላለሁ' ሲሉ ሰዎች ጥሩ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ለሰውነት ምንም ጥቅም የለውም። ሁሉም ነገር የገንዘብ ጉዳይ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ከሁሉም በላይ ደግሞ አካባቢን በጣም የሚጎዳ ነው። የታሸገው በጠርሙስም ሆነ በፕላስቲክ መያዣ አካባቢ ላይ ጉዳት ያስከትላል” ብለዋል።
“ስለዚህ ጉዳዩ የገንዘቡ ብቻ አይደለም። እነዚህ ፋይን ዋተር የሚባሉት የሚያደርሱት አካባቢያዊ ጉዳትንም ጭምር ነው።”
ዶ/ር ማስቻ ግን ይህንን አይቀበሉትም። ‘ፋይን ዋተር’ የሚመረተው ለቱጃሮች ብቻ አይደለም፤ ሁለት ዶላር የሚሸጥ ‘ፋይን ዋተር’ አለ በማለት ይከራከራሉ።
በተፈጥሮ ‘ፋይን ዋተር’ እና በተቀነባበረ ውሃ መካከል ያለውን ልዩነትን በማሳየትም በአካባቢ ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ገልጸዋል።
“ከዘላቂነት አንጻር የቧንቧ ውሃን በፕላስቲክ መያዣ ውስጥ መጨመር ፋይዳ የለውም። መኪናዎትን እየነዱ ሱፐርማርኬት ደርሰው የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ወደ ቤት ይዘው ይመለሳሉ። ውሃውን ጠጥተው ፕላስቲኩን ይጥሉታል። ይህ ብከነት ለማመን የሚከብድ ነው።”
ለውሃ ጥም የታሸገ ውሃ ከመጠቀም ይልቅ የቧንቧ ውሃ መጠቀምን ይመክራሉ።
“በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች የቧንቧ ውሃ እንኳን እንደማያገኙ ብዙውን ጊዜ እንረሰዋለን” ሲሉም ተናግረዋል።












