ያለ ውሃ ምን ያክል መቆየት እንችል ይሆን?

ሐረር በፈረቃ ውሃ ማግኘት ጀምራለች

የፎቶው ባለመብት, Godong

ውሃ በዓለማችን ላይ በእጅጉ ለሕይወት አስፈላጊ ከሆኑት ንጥረነገሮች ዋነኛው ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ ውሃ ማግኘት ባይችል ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት በታም ከባድ ነው።

ውሃ ለሰው ልጅ እጅግ ጠቃሚ ነው። የሰውነታችንን ሁለት ሶስተኛ ክብደትንም ይይዛል፣ ሰውነታችን ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችና አላሰፈላጊ ቆሻሻዎችን ያጓጉዛል፣ የሰውነታችንን ሙቀት ይቆጣጠራል፣ ሰውነታችን እንዲለሰልስና መገጣጠሚያዎቻችን ላይ የሚፈጠርን መጎርበጥ እንዲቀንስ ያደርጋል፣ ሰውነታችን ውስጥ የሚካሄድ የኬሚካል ውህደትን ያግዛል።

ሰዎች ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ በላብ፣ በሽንትና በትንፋሽ በኩል ሰውነታቸው ውስጥ ያለው ውሃ እየቀነሰ ይሄዳል። በሰውነታችን ውስጥ በቂ የውሃ ክምችት እንዳለን ማረጋገጥ ድርቀትን ለመከላከል ወሳኝ ነው።

ከ1-2 በመቶ የሰውነታችንን የውሃ መጠን ስናጣ ድርቀት እንደሚያጋጥመን ይታወቃል። የድርቀት ምልክቶችን ማወቅ ቀላል ነው፤ ሰውነታችን እንደገና ፈሳሽ እሰከሚያገኝ ድረስ ድርቀቱ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል። የተለመደ ነገር ባይሆንም ድርቀት ለሞት እስከማብቃትም ሊያደርስ ይችላል።

ባደጉት አገራት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት በአቅራቢያ ያለ ቧንቧን የመክፈት ያክል ቀላል ነው። በነዚህ አገራት የሚገኙ ሰዎች በየቀኑ በሚሊየኖች የሚቆጠር ሊትር ውሃ እንደቀልድ ይጠቀማሉ። ነገር ግን ደሃ በሚባሉት አገራት ወይም 1.1 ቢሊየን የሚሆኑ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንኳን ማግኘት አይችሉም።

ውሃ በዓለም ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የቅርብ ጊዜ ጉዳይ አይደለም። ከጥንት ጀምሮ የነበረ እንጂ። ብዙ ጊዜ የወንዝ መነሻ እና ከፍታ ቦታ ላይ የሚገኙ ሀገራት በታችኞቹ ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። እነዚህ የዓለማችን ክፍሎች ደግሞ ብዙ ጊዜ ውጥረት የነገሰባቸው ናቸው። በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኘው የዮርዳንስ ወንዝ ፍልስጤም፥ ዮርዳኖስ እና እስራኤልን ጨምሮ በአካባቢው ለሚገኙ በርካታ ሀገራት የውሃ ምንጭ ነው።

ኢትዮጵያ እና ግብፅ ደግሞ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ማብቂያውን በግብፅ በኩል ሜዲትራንያን ውቅያኖስ ላይ ባደረገው ኣባይ ወይም በናይል ወንዝ ጉዳይ ለዘመናት ሲጎነታተሉ ኖረዋል። እ.አ.አ. በ2015 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ግብፅ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ እንደሚሆን በሚጠበቀው 'በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ' ዙሪያ እሰጥ እገባ ውስጥ ገብተው ነበር። ሀገራቱ ፍትሀዊ የውሃ ክፍፍል የሚያረጋግጥላቸውን ስምምነትም እስከመፈረም ደርሰዋል።

በሌላ በኩል ውሃ በሰውነታችን ውስጥ ለ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ቦታ ይይዛል።

በየቀኑ አንድ ሊትር ውሃ የምንጠጣ ከሆነ የመልካም ጤንነት ምስጢር ነው፣ ብዙ ጉልበት እና ጥሩ ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል፣ ክብደት ይቀንሳል፣ ካንሰርም ያጠፋል የሚል መረጃ ስንሰማ ኖረናል።

በደንብ ያልተረጋገጠው ህግ ውሃ ካልሆኑ መጠጦች በተጨማሪ 240 ሚሊ ሊትር በሚይዝ ብርጭቆ በቀን ስምንት ግዜ ውሃ እንድንጠጣ እንመከራለን። አጠቃላይ ድምሩ በቀን 2 ሊትር አካባቢ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1945 የአሜሪካ ምግብና የአመጋገብ ስርዓት ቦርድና ብሄራዊ የጥናት ካውንስል እንዳሳሰበው አዋቂዎች ለእያንዳንዱ በምግብ ውስጥ ለሚገኝ ካሎሪ አንድ ሚሊ ሊትር ውሀ መውስድ እንዳለባቸው ይመክራል።

አዋቂ ሴቶች ለ2 ሺ ያህል ካሎሪ ሁለት ሊትር፣ ወንዶች ደግሞ ለሁለት ሺ አምስት መቶ ካሎሪ ሁለት ከግማሽ ሊትር ፈሳሽ እንዲወስዱ ይመክራል። ይህ ማለት ግን ውሃ ብቻ ሳይሆን እስከ 98 በመቶ ውሃ ያላቸው ፍራፍሬ እና አትክልትንም ያጠቃልላል።

ከ1-2 በመቶ የሰውነታችንን የውሃ መጠን ስናጣ ድርቀት እንደሚያጋጥመን ይታወቃል። የድርቀት ምልክቶችን ማወቅ ቀላል ነው፤ ሰውነታችን እንደገና ፈሳሽ እሰከሚያገኝ ድረስ ድርቀቱ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል። የተለመደ ነገር ባይሆንም ድርቀት ለሞት እስከማብቃትም ሊያደርስ ይችላል።

ለአመታት በቂ መረጃ ሳይቀርብበት ሲተች የነበረው የውሃ አጠጣጥ ሕግ ጥም ሲሰማን በአደገኛ ሁኔታ ሰውነታችን ደርቋል ብለን እንድናምን አድርጎናል።

የአንድ ጤናማ ሰው ጭንቅላት በራሱ የውሃ እጥረትን አነፍንፎ መለየት ይችላል። ጥምን በማነሳሳት ውሃ እንድንጠጣ ያደርገናል። ሆርሞኖች በማመንጨትም ኩላሊታችን ሽንታችንን በማወፈር ውሃ እንዲቆጥብ ምልክት ይሰጣል።

ሰውነታችንን የምናሰተውል ከሆነ መቼ እንደሚጠማን ይነግረናል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

ሞቃታማ በሆነ አካባቢ አካላዊን እንቅስቃሴ ስናደርግ የአንድ አዋቂ ሰው ሰውነት ከ1 እስከ 3 ሊትር ውሃ ሊያጣ ይችላል። ተጨማሪ ከ200 እስከ 1500 ሚሊ ሊትር የሚደርስ ውሀ ደግሞ ስንተነፍስ ሊጠፋ ይችላል።

በዚህ አይነት መልኩ ሰውነታችን ውሃን ሲያጣ ሊከተል የሚችለው ችግር ከፍተና ነው። ቀላል የሚባለው እንኳን የውሃ እጥረት በቀላሉ እንድንደክምና አካላችን እንደልብ እንዳናዘው ሊያደርገን ይችላል።

ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች በከባድ ሁኔታ ውስጥ ሆነውና ሰውነታቸው ውሃ አጥሮትም ለረጅም ጊዜ መቆየት ይችላሉ።

የረጅም ርቀት ሩጨዓ አሰልጣኙ አልቤርቶ ሳላዛር በአውሮፓውያኑ 1984 ተካሂዶ በነበረው የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ ወቅት በሰአት 3.06 ሊትር ውሃ ሰውነቱ ያጣ ሲሆን 8 በመቶ የሚሆነውን የሰውነቱን ክብደትም በሩጫው ወቅት አጥቶ ነበር።

ነገር ግን ከውድድሩ በኋላ በተደረገለት እንክብካቤ ወዲኣው ወደቀድሞው አካላዊ ብቃቱ መመለስ ችሏል።

በአንድ ጤናማ አዋቂ ሰው ሽንት ውስጥ 95 በመቶው ውሃ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በኩላሊት በኩል የሚወገድ ቆሻሻ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ጨው እና አሞኒያ ያሉ ንጥረነገሮችን ያካትታል።

የሰው ልጅ ሰውነት ውሃ ሲያጥረውና ድርቀት ሲያጋጥመው የአንጎሉ ስራ ላይ ተጽህኖ የሚፈጠር ሲሆን አጠቃላይ ባህሪያችንንም ይቀያይረዋል።

ውሀ በየቀኑ መጠጣት ለሰውነታችን ያለው አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ለምሳሌ ከከባድ የሰውነት እንቅስቃሴ ወይም አልኮል መጠጥ ከጠጣን በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ውሃ መጠጣት ጉዳት ያስከትላል።

'ሃይፖናትሬሚያ' በመባል የሚታወቀው ይህ የጤና እክል ኩላሊቶቻችን ውሃን በአግባቡ እንዳያስወግዱ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ውሀ መጠጣት አለብን ብለን በግድ ሳይሆን መጠጣት ያለብን፤ ሰውነታችን ተፈጥሮአዊ ጊዜውን ጠብቆ ውሀ አጠጡኝ ሲል መሆን ያለበት ባይ ናቸው።

ለመሆኑ አንድ ሰው ያለውሃ መቆየት የሚችለው ምን ያክል ጊዜ ነው?

በርካታ ተመራማሪዎች አንድ ሰው ያለ ውሃ መቆየት የሚችለው ምናልባት እንደየሰዉ ሊለያይ ቢችልም ከጥቂት ቀናት በላይ አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 1944 ሁለት ተመራማሪዎች እራሳቸውን ከውሃ አርቀው አንድ ሙከራ ሰርተው ነበር። አንደኛው ለሶስት ቀናት ያለ ውሃ ሲቆይ ሌላኛው ደግሞ ለአራት ቀናት መቆየት ችሏል።

ነገር ግን አራት ቀን የቆየው ተመራማሪ የተመጣጠነ ምግብ በየቀኑ ይቀርብለት ነበር። በሙከራቸው መጨረሻ ላይ ሁለቱም ተመራማሪዎች ምግብ መዋጥ ተስኗቸው የነበረ ሲሆን የፊታቸው ቀለምም ቢሆን ተቀይሮ ነበር።

በዚህ ምክንያት የጤና ሁኑታቸው ከዚህ ወደባሰ ደረጃ ሳይሸጋገር በፊት ሙከራውን በማቋረጥ ውሃ ጠጥተዋል።

ያለውሃ መቆየት ከሰው ሰው ሊለያይ የሚችል ነገር ነው። ሰውነታችን ሁሌም በየቀኑ የምንሰጠውን ያክል ውሃ ብቻ እያገኘ እራሱን ማቆየት ይችላል። ትንሽ እየሰጠን ካስለመድነው በዛው ይቀጥላል። ብዙ ካስለመድነውም እንደዛው።

እስካሁንድ ድረስ ለረጅም ጊዜ ውሃ ሳይጠጣ መቆየት የቻሉ በርካቶች አሉ። አውስትራሊያዊው አንድሬስ ሚቺቫትዝም አንደኛው ነው። በወቅቱ የ18 ዓመት ወጣት የነበረ ሲሆን ያለውሃ ለ18 ቀናት መቆየት ችሎ ነበር።

በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ላይም ተመዝግቦ ይገኛል።