የዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት በኤፍቢአይ የተበረበረበት ምክንያት ይፋ ሊደረግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤፍቢአይ ወኪሎች የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ቤት የበረበሩበት የፍተሻ ማዘዣ ይፋ እንዲደረግ የአገሪቱ ፍትህ ቢሮ የፍሎሪዳውን ፍርድ ቤት ጠየቀ።
ያልተለመደ ነው የተባለለት ጥያቄ ፈቃድ ካገኘ የትራምፕ መኖሪያ ቤት እንዲፈተሽ የተደረገበት ምክንያት ለሕዝብ ይፋ ይሆናሉ ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ በተመሳሳይ የብርበራ ፍቃዱ ሰነድ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ፍላጎታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
የፍትህ ቢሮ ፍተሻው ለምን እንደተካሄደ እስካሁን ይፋ አላደረገም። የአሁኑ ጥያቄ ግን ለዚህ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰኞ ዕለት በኤፍቢአይወኪሎች የተደረገው ብርበራ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጥብቅ እና ሚስጢራዊ ሰነዶች አያያዝ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ተብሎ ነበር።
ስማቸው ያልተገለጸ አንድ ምንጭን ጠቅሶ ዋሽንግተን ፖስት እንዳስነበበው የኤፍቢአይ ወኪሎች ከኒውክለር መሣሪያዎች ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ጭምር በትራምፕ መኖሪያ ቤት ስፈልጉ ነበር።
ወኪሎቹ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕን ቁም ሳጥን እና የግል ቁሳቁሶቻቸውን መበርበራቸውን ትራምፕ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ሜሪክ ጋርላንድ በትራምፕ መኖሪያ ቤት ላይ ፍተሻው እንዲካሄድ መፍቀዳቸውን ገልጸዋል።
ከፍርድ ቤት ፍተሻ ማዘዣ ጋር የተገናኙ ሰነዶች ለሕዝብ ጥቅም ሲባሉ ይፋ እንዲሆኑ እየጠየቁ መሆኑን ጋርላንድ ተናግረዋል።
የፍትህ ቢሮ ሁሌም መደበኛ ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ እንደሚያደርገው ዝምታ የመምረጥ ልምዱን እየተከተለ ነው።
የፍትህ ቢሮ ጠበቆች ሐሙስ ዕለት በፌዴራል ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ "በዚህ ሁኔታ የተከሰተውን ነገር ለመረዳት የሕዝቡ ግልጽ እና ከፍተኛ ፍላጎት ስላለው ይፋ መሆኑ ይጠቅማል” ብለዋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት መኖሪያ ቤት ከወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ ሲፈተሽ የሰኞው በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ነው። ትራምፕ እና ሌሎች ሪፐብሊካኖች እርምጃውን ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ሲሉ አውግዘዋል።
ሐሙስ ዕለት በጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ጋርላንድ የኤፍቢአይ ወኪሎችን እና የፍትህ ክፍል ኃላፊዎችን ተከላክለዋል።
ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ታማኝነታቸው ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሲጠቃ በዝምታ አላይም” ብለዋል።
የፍተሻ ማዘዣውን ለማስፈጸም መወሰኑም ቀላል እንዳልነበር ተናግረዋል።
የትራምፕ ጠበቃ የሆኑት ሊንሴይ ሃሊጋን ፍርድ ቤት ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት የህግ ቡድናቸው ማዘዣውን በመልቀቅ ጉዳይ ላይ እየተወያ ነው።
የብርበራውን ፎቶ እና ቪዲዮ ይፋ ለማድረግም እያሰቡ ነው።
የኤፍቢአይ ወኪሎች የማር-አ-ላጎ የሲሲቲቪ ካሜራዎች እንዲጠፉ ጠይቀው ነበር። የትራምፕ ሠራተኞች ግን ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም ተብሏል።












