ሲም ካርድ ያለው ሁሉ ገንዘብ መበደር የሚችልበትን ዕድል የፈጠረው ቴሌብር

የፎቶው ባለመብት, Ethio Telecom
ከአስራ አራት ወራት በፊት ወደ አገልግሎት የገባው ቴሌብር የተሰኘው የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት ባለፈው ሳምንት አርብ ከቁጠባ እና ብድር ጋር የተያያዙ አዳዲስ አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል።
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አዳዲሶቹ አገልግሎቶች በፋይናንስ ሥርዓት ያልተሸፈነውን 60 በመቶ የሚሆን የኅብተረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የነዳጅ ድጎማ እና የግብር ክፍያን ጨምሮ ባለፉት 14 ወራት ገንዘብ ለመላላክ፣ የግብይትና የአገልግሎት ክፍያን ለመፈጸም እንዲሁም ከውጭ አገራት ገንዘብ ለመቀበል ሲውል የነበረው ቴሌብር አሁን ደግሞ ‘መላ’፣ ‘እንደኪሴ’ እና ‘ሰንዱቅ’ የተሰኙ አገልግሎቶችን ይፋ አድርጓል።
ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብር ደንበኞች ገንዘብ እንዲቆጥቡ፣ ሲያስፈልጋቸው እንዲበደሩ የሚረዱት አዳዲሶቹን አገልግሎቶች ለማስጀመር አስራ አራት ወራት በላይ ዘግይቷል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም እነዚህን አገልግሎቶች ለማስጀመር ከአንድ ዓመት በላይ የዘገየበትን ምክንያት ሲያስረዱ “የተሰጠን ፍቃድ እሱን አልፈቀደልንም ነበር። ስለዚህ በቴሌ ብር ሌሎቹን አገልግሎቶች እየሰጠን ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ለማግኘት ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል” ብለዋል።
ለመሆኑ አገልግሎቶቹ ምንድን ናቸው?
የቴሌብር ቁጠባና ብድር
በቴሌብር አማካኝነት በቅርቡ የተጀመሩት ሦስት አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች ያለዋስትና/ማስያዣ እንዲበደሩ ወይም እንዲቆጥቡ የሚያስችሉ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
- ሳንዱቅ
ይህ የቴሌብር አገልግሎት ደንበኞች ገንዘብ የሚቆጥቡበት ሲሆን፣ ለተቀማጭ ገንዘብ ወለድ የሚከፈልበትን እና ከወለድ ነጻ የሆነ አመራጮችን አካቷል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፣ ወለድ የሚከፈልበት ቁጠባ በየቀኑ የሚሰላ እና ደንበኞች በቀን ያገኙትን መጠን የሚያመላክት ነው።
- እንደ ኪሴ
የቴሌብር ደንበኞች ግብይት እየፈጸሙ ገንዘብ በሚያንሳቸው ጊዜ ቀሪውን ገንዘብ የሚያገኙት ሥርዓት ደግሞ እንደኪሴ ይሰኛል።
እንደኪሴ ደንበኞች ለግብይት ከሚያጥራቸው ገንዘብ በተጨማሪ እንደ የኤሌክትሪክ እና ውሃ ያሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመፈጸምም ያስችላል።
ይህ አሰራር ደንበኞች ለክፍያ የጎደላቸውን እስከ 2 ሺህ ብር የሚሸፍንም ነው።
- መላ
ቴሌብር መላ፣ ደንበኞች የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት መንገድ ሲሆን ግለሰቦችን እና የንግድ ተቋማትን የሚያካትት ነው።
በቴሌብር መላ ግለሰቦች በወር እስከ 10 ሺህ ብር፣ የንግድ ተቋማት ደግሞ እስከ 100 ሺህ መበደር እንደሚችሉ የሚያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ግለሰቦች የተበደሩትን በቀን፣ በሳምንት እና በወር መመለስ የሚችሉበትን አሰራር ማቀፉን ጠቅሰዋል።
ለንግድ ተቋማት ደግሞ ለግለሰቦች ከተጠቀሰው የጊዜ ገደብ በተጨማሪ የ3፣ የ6 እና የ9 ወር የሚመልሱበትን አሰራር አካትቷል።
ቴሌብር መላ “ለሥራ ማስኬጃ እንዲሁም አዳዲስ ሃሳብ ኖሯቸው ወደ ንግድ መግባት ለሚፈልጉ ሰዎችን ታሳቢ አድርጎ የቀረበ ነው። ለዚያ ነው በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነውን ማኅበረሰብ፣ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም ይሆናል ብለን ያሰብነው” ሲሉም አክለዋል።
መላ፣ እንደ ኪሴ እና ሰንዱቅ በተሰኙት የቴሌብር አገልግሎቶች በመጀመሪያ ዓመት ውስጥ በየወሩ በአማካኝ ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ደንበኞችን ለማገልገል እና ከ19.5 እስከ 20 ቢሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ ማቀዱን ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
ከዚህም ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የብድር አገልግሎቱ ወይም ቴሌብር መላ ሲሆን 9.8 ቢሊዮን ብር ይሸፍናል።
6.4 ቢሊዮን ብር ክፍያን ለማጠናቀቅ ወይም እንደ ኪሴ ለተባለው አገልግሎት እንዲሁም 3.3 ቢሊዮን ብር ደግሞ በቁጠባ ወይም ሳንዱቅ በተሰኘው አገልግሎት የሚጠቃለል ነው።
ደጋግመው ብድር የሚወስዱ ደንበኞችን ጨምሮ በዓመት 108 ሚሊዮን ደንበኞችን ለማገልገል ማታቀዱንም አስረድተዋል።
አገልግሎቶቹ በተጀመሩ በቀናት ውስጥ የዕለት ብድር ወስደው የሚመልሱ እንዲሁም የሚቆጥቡ ደንበኞች መኖራቸውን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተስፋ ሰጪ እና “አስገራሚ” ሁኔታዎች መኖራቸው ገልጸዋል።
በቴሌብር መላ የሚሰጠው ብድር በሙሉ ዋስትና ወይም ማስያዣ እንደማይጠየቅበትም ጨምረው አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ethio Telecom
ብድር ያለ ዋስትና? እንዴት?
የፋይናንስ ተቋማት ለሚያበድሩት ገንዘብ ዋስትና ወይም ማስያዣን መጠየቅ የተለመደ አሰራራቸው ነው።
ከዚህ አሰራር በተቃራኒ በቴሌብር የሚቀርቡ ብድሮች ዋስትና አይጠየቅባቸውም። ሆኖም ሥርዓቱን በሚንቀሳቀስበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት የደንበኞችን የወጪ ገቢ ዝውውር በመመልከት የብድሩን መጠን ይፈቀዳል።
ሥርዓቱ ደንበኛውን በገንዘብ ዝውውሩ በመመልከት በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለጽ ነጥብ የሚሰጥ ሲሆን፣ ብድር ለሚመልሱ ደንበኞች ደግሞ የተሻለ ቡድር ማግኘት የሚቻልበትን ነጥብ ይሰጣል።
አገልግሎቱ በቴሌብር ሞባይል መተግብሪያ ወይም #127# አጭር ቁጥር አማካኝነት የሚቀርብ ሲሆን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ሲምካርድ ላላቸው ደንበኞች በሙሉ በቴሌብር ያላቸውን የገንዘብ ዝውውር መሰረት አድርጎ ብድርን የሚያቀርብ ነው።
እነዚህ አገልግሎቶችን ለማስጀመር የአዋጪነት ጥናት መካሄዱን የሚያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ እንደ ማንኛውም የፋይናንስ አገልግሎት ስጋት ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ይህ አገልግሎት የኢትዮጵያን ባህል ከግምት ውስጥ ማስገባቱን በማንሳት “ሁሉም ደንበኛ አይመለስም ብለን ልንወስድ አንችልም። . . . ተበድሮ አልመለሰም መባልን የማይፈልግው የማኅበረሰባችን ክፍል ሰፊ ነው። እርሱን እንደ ጥንካሬ ወስደነዋል።”
አክለውም “ . . . አንዴ ብድሩን አልመለሰም ማለት በሚቀጥለው ብድር አያገኝም። ስለዚህ አንዴ ሁለት ሺህ ብር ተበድሮ ቢጠፋ ነው የሚሻለው ወይስ በዓመት ሁለቴም ሦስቴም ሁለት ሺህ፣ አራት ሺህ ቢበደር ነው የሚሻለው? ለማኅበረሰቡ የምናስረዳው ይህንን ነው። ይህ ይሆናል ብለን አንጠብቅም። ባለማወቅ ሊፈጠር ይችላል። ለዚያ ግን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንሰራለን። ምንም ችግር አያጋጥመንም ግን አንልም። በፋይናንስ ሴክተር ያሉ እንደሚያውቁት በዋስትና የሚሰጠው ብድርም ላይመለስም ይችላል። ግን ከቁጥጥር ውጪ አይሆንብንም። እሱን አጥንተን ነው የገባነው” ብለዋል።
ሥርዓቱ ላይ ይህ ችግር ሊያጋጥም ይችላል በሚል ይህንን ከመተግበር ወደ ኋላ አንልም የሚሉት ፍሬህይወት “60 በመቶ የኅበረተሰብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት የማያገኝበት አገር ላይ ሆነን ሪስክ [ስጋት] አለ ብለን የገንዘብ ችግር ከመፍታት አንጻር ትልቅ አቅም የሆነውን አለመጀመር ደግሞ ተገቢ ነው ብለን አናስብም. . .”
ስለዚህም ይህንን በአግባቡ ተጠቅመው ኑሯቸውን፣ ሕይወታቸውን፣ ቤተሰባቸውን ሊቀይሩ የሚችሉ ሚሊዮኖች ስላሉ የእነርሱን ዕድል ለማስፋት የተጀመረ ሥራ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ “ሙሉ በሙሉ ስጋት (ሪስክ) የለውም ብለን ሳይሆን መልካም ጎኑን ይዘን ነው የተነሳነው” ሲሉም አክለዋል።
የቴሌብር የአስራ አራት ወራት ጉዞ
ወደ አገልግሎት ከገባ 1 ዓመት ያለፈው ቴሌብር 22.2 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ያስረዳሉ።
በእነዚህ ጊዜያትም 34.1 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተከናውኖበታል። ከዝውውሩ 18 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ማውጣት እና ማስገባት ሲሆን 40 በመቶ ደግሞ የአየር ሰዓት መሙላትን ነው።
ገንዘብ መላላክ፣ የአገልግሎት ክፍያ እና ግብይት መፈጸም ደግሞ የተቀረውን ድርሻ ይይዛል።
የግብር፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ እና መሰል አግልግሎቶችን ከሚሰጡ በርካታ የመንግሥት ተቋማት፣ ከ13 ባንኮች እንዲሁም ከ22 ሺህ የንግድ ተቋማት ጋር የተሳሰረው ቴሌብር በመላው አገሪቱ ከ79 ሺህ በላይ ወኪሎች እንዳሉትም ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
“ይህንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳካታችንን እንደ ትልቅ ስኬት እንወስደዋለን” የሚሉት ኃላፊዋ ቴሌብር የገንዘብ ዝውውር እና ክፍያን ምቹ እና ቀልጣፋ ማድረግ፣ የክፍያ ሥርዓትን ማዘመን እና የዲጂታል ኢኮኖሚን በማስተዋወቅ በፋይናንስ አገልገሎት ያልተካተተውም ሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ዋነኛ አላማው እንደሆነ አንስተዋል።
እስካሁን ቴሌብር “የክፍያ ሥርዓቱን ሲያሳልጥ የቆየ” ሲሆን በፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽ ያልሆኑ ሰዎችን ተደራሽ የማድረግ ቀዳሚ ዓላማውን ለማሰካት በቅርቡ ይፋ የሆኑት ዓላማዎች ወሳኙን ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰዋል።












