የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መግባት ለኢትዮ ቴሌኮም ፈተና ወይስ ዕድል?

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ

የፎቶው ባለመብት, EthioTelecom

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንደምታደርግ ካሳወቀች በኋላ ሁለት ፈቃዶችን ለዘርፉ ተሳታፊዎች በጨረታ አቅርባ ነበር።

ኅዳር 18/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ኩባንያዎች ይፋዊ የጨረታ ጥሪ አቅርቦ ሚያዝያ 16/2013 ዓ.ም ሁለት ተቋማት በጨረታው ተሳታፊ መሆናቸውን ማሳወቁ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት የተለያዩ ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ተቋም ከፍተኛውን ዋጋ፣ 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ ጨረታውን በማሸነፍ ተመራጭ ሆኗል። ነገር ግን ሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ ቀርቷል።

የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የዩናይትድ ኪንግደም ቮዳፎን እና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም፣ የጃፓኑ ሱሚቶሞ እንዲሁም ዲኤፍሲ ናቸው ወደዚህ ዘርፍ ለመግባት ፈቃድ ያገኙት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ የተሰጠውን ፈቃድ "ታሪካዊ ውሳኔ" በማለት አድንቀውታል።

በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ካላቸው ቀዳሚ አገራት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያ፤ የቴሌኮም ዘርፍ በአንድ አገልግሎት ሰጪ ያለተፎካካሪ በብቸኝነት ተይዞ በመቆየቱ ተጠቃሚዎች በዋጋም ሆነ በአገልግሎት ጥራት አማራጭ ሳይኖራቸው ቆይቷል።

በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው የተለያዩ ታዋቂ የቴሌኮም ኩባንያዎች ስብስብ የሆነው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ከ750 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል።

ይህ ጥምረትም ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት አገር ውስጥ ሰፊ የገበያ ዕድል ያለው ሲሆን፣ ዘመኑ ያፈራቸውን የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።

ነገር ግን ይህን ያክል ልምድና የገንዘብ አቅም ይዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎቹ ጥምረት እስካሁን በነበሩት ዓመታት ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት ለነበረው ኢትዮ ቴሌኮም ስጋትን ይፈጥርበት ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

'ያሉንን ደንበኞች የምናቆይበትን ስትራቴጂ ቀርጸናል'

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ግን ካላቸው ከፍተኛ የደንበኛ ቁጥርና መሰረተ ልማት አንጻር የእነዚህ ድርጀቶች ወደ ዘርፉ መግባት እንደማያሳስባቸው ገልጸዋል።

"ለማንኛውም የውድድር ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ስትራቴጂ ይቀረጻል፤ እኛም የራሳችንን ስትራቴጂ ቀርጸናል። አዲስ የሚገባው አገልግሎት ሰጪ ወደ ዘርፉ አዲስ ገቢ ሆኖ እንደሚቀላቀልና የጀማሪ ስትራቴጂ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። እኛ ደግሞ አሁን ያሉንን ደንበኞች የምናቆይበትን ስትራቴጂ ቀርጸናል" ብለዋል።

ድርጅቱ ለሦስት ዓመት በቀረጸው ስትራቴጂ እና እስካሁንም እየተገበረው በመጣው አካሄድ በከፍተኛ ሁኔታ የደንበኞችን ቁጥር፣ ገቢንና እና የኔትወርክ ሽፋንን ማሳደግ ችሏል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ዘርፉ የሚጠይቀውን በሙሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

"በእቅዳችን መሰረት በዘርፉ ተመራጭና አንደኛ የአገልግሎት አቅራቢ ለመሆን ነው የምንሰራው። ምንም እንኳን የሚመጡት ድርጅቶች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ቢሆኑም፣ ዓለም ላይ እየተሰራ ስላለው የቴሌኮም አገልግሎት በቂ መረጃና እውቀት አለን። ስትራቴጂያችንም ይህንኑ በሚገባ አጥንቷል፤ ተንትኗል።"

"ለኢትዮጵያ ገበያ ይሆናል ብለን የምናስበውንና የደንበኞቻችንን ፍላጎት በሚገባ ያሟላሉ ብለን የምናስባቸውን ሥራዎች እየተገበርን እንገኛለን" ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ላይ 97 በመቶ የሕዝብ ተደራሽነት ያለው አገልግሎት አቅራቢ ሲሆን 56 ሚሊየን ደንበኞችም አሉት።

ይሄ ቀላል የሚባል ቁጥር አይደለም። ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ይህን ያክል ቁጥር የሚያገኙት በተለያዩ አገራት አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ስለዚህ ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹ ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነና በመላው አገሪቱ የመሰረት ልማት ግንባታ ማካሄዱ በዘርፉ ተወዳዳሪና ተመራጭ ያደርገዋል።

የተለያዩ ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ተቋም የጨረታው አሸናፊ መሆኑ ይፋ በተደረገበት ወቅት የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ውሳኔው አገሪቱ በምታካሂደው የምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ሂደት ውስጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው "ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥራት ያለው አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል" ብለዋል።

በወቅቱም በጉዳዩ ዙሪያ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያውና ፌርፋክስ አፍሪካ ግሎባል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ክፍት መሆኑ ጥራት ያለው አገልግሎት በርካሽ ዋጋን ከማስገኘቱ ባሻገር "ለሥራ ፈጠራና ለውድድር በር ይከፍታል" ብለው ነበር።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ

የፎቶው ባለመብት, Ethio Telecom

ቴሌ ብር

ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ ጥምረት አካል የሆነው በተለይ በኬንያ እና በኡጋንዳ በበርካታ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሉት ሳፋሪኮም፣ ኬንያ ውስጥ ከ14 ዓመታት በፊት የጀመረው 'ኤምፔሳ' የተሰኘው የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት አሁን ላይ 72 በመቶ የሚሆነው የኬንያ ነዋሪ ይጠቀመዋል።

በሰባት አገራት የሚሰራው ኤምፔሳ 42 ሚሊዮን ደንበኞችና 400 ሺህ ወኪሎች ያሉት ሲሆን 50 በመቶ የሚሆነው የኬንያ ዓመታዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) በዚሁ ሥርዓት በኩል ይንቀሳቀሳል።

በኡጋንዳም ቢሆን ከጠቅላላ ሕዝቡ የባንክ አካውንት ያለው 11 በመቶ ሲሆን ኤምፔሳን የሚጠቀመው ሰው ግን 42 በመቶ ተሻግሯል።

ይህ ጥምረት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲቀላቀል መሰል የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።

ኢትዮ ቴሌኮምም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል ከወራት በፊት ቴሌብር የተሰኘውን የኢትዮጵያ ሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን አስተዋውቋል።

"ወደፊት ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን የአገራችንን ጂዲፒ በቴሌብር በኩል እንዲንቀሳቀስ ነው አልመን እየሰራን ያለነው። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ይህን እናሳካለን ብለን ነው የምናስበው" ይላሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ።

"መርሀ ግብሩን ካስጀመርን ወዲህ በ100 ቀናት ውስጥ ብቻ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ደንበኞቻችን ቁጥር 8.5 ሚሊየን ደርሷል። የወኪሎቻችን ቁጥር ደግሞ ከ18 ሺ በላይ ሆኗል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው ለእኛ" ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደሚሉት በዘርፉ በሌሎች አገራት የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች መካከል የትኛውም በ100 ቀናት ውስጥ ይህን ያክል ቁጥር ያለው ደንበኛ ማግኘት አልቻለም። "ምናልባትም ይህን ያክል ቁጥር ለመድረስ ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።"

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮ ቴሌኮም ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ለመጨመር ከስድስት ባንኮች ጋር አብሮ እየሰራ እንደሚገኝም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አክለዋል።

"በእነዚህ 100 ቀናት ውስጥ ከስድስቱ ባንኮች ጋር ያደረግነው ስምምነት ደንበኞቻችን በቀላሉ ገንዘብ ከባንክ ወደ ሞባይል፤ ከሞባይል ወደ ባንክ እንዲያዘዋውሩ አስችሏቸዋል።"

በሌላ በኩል ደግሞ 3643 የሚሆኑ የንግድ ተቋማት ደንበኞቻቸው ማንኛውንም አይነት ክፍያ በቴሌብር በኩል እንዲያደርጉ ተስማምተው እየሰሩ ነው።

እንደ ምሳሌም ሰዎች የትራፊክ ቅጣቶችን በአካል ቢሮ ድረስ ሄደው ከሚያደርጉ ይልቅ በቴሌብር በኩል እንዲከፍሉ ለማድረግ አንዳንድ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነና በአዲስ አበባም ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ነግረውናል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባታቸው እንደ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚያዩት የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጤናማ የሆነ ውድድር ዘርፉን ለማዘመን እና ደንበኞችን ይበልጥ ለማገልገል እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

አክለውም በዘርፉ ሁሉንም ሊፈጠሩ የሚችሉ ነገሮች ከግምት ውስጥ አስገብቶ ኢትዮ ቴሌኮም ስትራቴጂ መንደፉንና ያልታሰቡ ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳን በሂደት እየፈቱ ለመሄድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።