ሩሲያ በዩክሬን ላይ አጠናክራ በቀጠለችው የአየር ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተጎዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት እንደ አዲስ መሰንዘሯን ተከትሎ በመላው ዩክሬን የአደጋ ጊዜ ደውሎች እየተደወሉ ነው።
በመዲናዋ ኪዬቭ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን ከንቲባው እንዳሉት አምስት ሰዎች በድሮን ስብርባሪ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቶች በኻርኪቭ፣ ኼርሶን፣ ኦዴሳ እና ሚኮሎቭ ግዛቶችም ተከፍተዋል።
ይህ በኪዬቭ ላይ በስምንት ቀናት ውስጥ የደረሰ የአየር ጥቃት ሲሆን፣ ጥቃቱ የተፈጸመው ሩሲያ የድል ቀን ከምታከብርበት ዕለት 24 ሰዓት በፊት ነው።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሩሲያ በናዚ ጀርመን ላይ የተቀዳጀችው ድል የሚታሰብበት ቀን ነው።
ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ከዚህ ጦርነት ጋር ነው የምታነጻጽረው።
ሩሲያ ባለፉት ወራት ንጹሀን ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃት ስትሰነዝር ቆይታለች።
በደቡብ ምሥራቃዊቷ ዛፖሪዢያ ግዛት ዩክሬን ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ ሩሲያ የአየር ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
የዩክሬን ጦር እንዳለው ለአራት ሰዓታት በቀጠለው የአየር ጥቃት በመላው አገሪቱ ዒላማ በተደረጉ ቦታዎች 16 ሚሳኤሎች ተተኩሰዋል።
52 ሮኬቶችን ጨምሮ አጠቃላይ 61 የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸው ተገልጿል። 35 ኢራን ሠራሽ ካሚካዚ ድሮኖች እንደወደሙም ባለሥልጣናት ገልጸዋል። ቢቢሲ እነዚህን ቁጥሮች በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ኪዬቭ ውስጥ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሰጪዎች የድሮን ጥቃቱን ተከትሎ ምላሽ እየሰጡ ነው።
በዙሊኒ አውሮፕላን ማረፊያ በድሮን ጥቃት ሳቢያ መንገድ ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ ከኪዬቭ ሁለት የንግድ አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ ነው።
በማዕከላዊ ሼቼንኪቭስኪ ግዛት በድሮን ስብርባሪ መኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
በኦዴሳ ግዛት ደግሞ በጥቁር ባሕር ወደብ አካባቢ መጋዘን ተቃጥሏል።
የኦዴሳ ወታደራዊ አስተዳደር ቃል አቀባይ ሼሪይ ብራቹክ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳሉት፣ የምግብ መጋዘን እንደሆነ የተገለጸ ሕንጻ በእሳት ተቃጥሏል።
የዛፖሪዢያ አስተዳዳሪ የሆኑት ቭላድሚር ሮጎቭ እንደገለጹት፣ የሩሲያ ኃይሎች መጋዘን ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
በምሥራቅ ግንባር፣ በባኽሙት የዩክሬን ኃይል አዛዥ እንዳሉት የሩሲያ ወታደሮች ድብደባ ተባብሷል።
በቫግነር ሥር ያሉ የሩሲያ ተዋጊዎች ባኽሙትን ለመቆጣጠር ለወራት ሲሞክሩ ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ የቡድኑ መሥራች የቬግኒ ፕሪጎዚን እንዳሉት ከሩሲያ የመሣሪያ ድጋፍ እንደሚጨመር መገንዘባቸውን ተከትሎ ባኽሙትን ለቀው ለመውጣት የታሰበው ዕቅድ ተቀልብሷል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንደተናገሩት ከሩሲያ ጋር በሚጻረር መልኩ እአአ ግንቦት 9 የአውሮፓ ቀን ተብሎ ይከበራል።












