አማዞን 1ሺህ 800 የሰሜን ኮሪያውያን የሥራ ማመልከቻዎችን አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አማዞን በሰሜን ኮሪያውያን ወኪሎች አማካኝነት የተደረጉ ከ1 ሺህ 800 በላይ የሥራ ማመልከቻዎችን ማገዱን አስታወቀ።
ሰሜን ኮሪያውያን የተሰረቀ እና ሐሰተኛ የሆኑ ማንነቶችን በመጠቀም ከርቀት ሆነው ለሚሰሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ሥራዎች ለማመልከት መሞከራቸውን የአማዞን የደኅንነት ኃላፊ ስቴፈን ሽሚት በሊንክዲን ባጋሩት ጽሑፍ ላይ ገልጸዋል።
"ዓላማቸው ቀጥተኛ ነው፤ መቀጠር ፣ ክፍያ ማግኘት እና የሚያገኙትን ገንዘብ የቀጠናውን አስተዳደር የጦር መሣሪያ ፕሮግራም መደገፍ ነው" ያሉት ኃላፊው፤ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች በተለይም በአሜሪካ በዘርፉ ላይ በስፋት መከሰቱን ተናግረዋል።
የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ፕዮንግያንግ በኦንላይን እየፈፀመች ያለውን ማጭበርበር በተመለከተ አስጠንቅቀዋል።
ሽሚት በሊንክድን ባጋሩት ጽሑፍ እንዳሉት አማዞን ባለፈው ዓመት ከሰሜን ኮሪያ የሚመጡ የሥራ ማመልከቻዎች ሲሶ ያህል ጨምሯል።
ሥራው በዋናነት 'የላፕቶፕ ፋርም' በሚል የሚጠራውን እና ከአገር ውጭ የሚሰሩና በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ኮምፒዩተሮችን ከሚያስተዳድሩ ሰዎች ጋር በመሆን የሚሰራ እንደሆነ ስቺሚዲት አስረድተዋል።
ተቋሙ እነዚህን የሥራ ማመልከቻዎችን ለማጣራት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ( ኤአይ) መሣሪያዎችን እና በሠራተኞቹ ማረጋገጫ በጥምረት መጠቀሙን ኃላፊው አክለዋል።
በአጭበርባሪዎች የሚፈፀሙ እንዲህ ዓይነት ስልቶች በጣም ውስብስብ እየሆኑ መጥተዋልም ብለዋል።
የዚህ መጥፎ ድርጊት ተዋናዮች ማረጋገጫ ለማግኘት ሾልከው የወጡ ማስረጃዎችን በመጠቀም ብዙም አገልግሎት ላይ ያልዋሉ የሊንክድን አካውንቶችን ይጠልፋሉ።
እውነተኛ መስለው ለመታየትም እውነተኛ የሆኑ ኢንጂነሮችን ዒላማ እንደሚያደርጉ የጠቀሱት ኃላፊው፣ ተቋማት አጠራጣሪ የሆኑ የሥራ ማመልከቻዎችን ሲመለከቱ ለባለሥልጣናት እንዲያሳውቁ አስጠንቅቀዋል።
ሽሚት ቀጣሪዎችም በሰሜን ኮሪያውያን የሥራ ማመልከቻዎች ላይ ትክክለኛ ያልሆነ የስልክ ቁጥር እና የማይዛመድ የትምህርት ሁኔታ ታሪክን ጨምሮ የማጭበርበር ምልክቶችን በደንብ እንዲመለከቱ አሳስበዋል።
ሰኔ ወር ላይ የአሜሪካ መንግሥት በመላ አገሪቱ በሰሜን ኮሪያውያን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሠራተኞች በሕገ ወጥ መንገድ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 29 በአንድ ሥርዓት ውስጥ የሚሰሩ ላፕቶፖች ወይም ላፕቶፕ ፋርሞች ማግኘቱን ገልጾ ነበር።
እነዚህ ባለሙያዎች ሰሜን ኮሪያውያን በአሜሪካ ሥራ እንዲያገኙ ለመርዳት የተሰረቁ እና ሐሰተኛ ማንነቶችን እንደተጠቀሙም የፍትሕ መሥሪያ ቤት ገልጿል።
ለሰሜን ኮሪያውያን ተቋማት ሥራ በመፈለግ ሲረዱ የነበሩ የአሜሪካ ደላሎችን መለየቱንም መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
ሐምሌ ወር ላይ የአሪዞና ነዋሪ የሆነች ሴት ሰሜን ኮሪያውያን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በአሜሪካ ከ300 በላይ በሚሆኑ ኩባንያዎች ውስጥ ከርቀት ሆነው የሚሰሩት ሥራ እንዲያገኙ የላፕቶፕ ፋርም በመመስረት ከስምንት ዓመት በላይ እስር ተፈርዶባታል።
የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ፕሮግራሙ ለግለሰቧ እና ለፒዮንግያንግ 17 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ማስገኘቱንም ገልጿል።















