በቅርቡ የተሾሙት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ ነው

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር

በቅርቡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ኪን ጋንግ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ሊያቀኑ ነው።

በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር የነበሩት ጋንግ ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር የአገሪቱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን ጉብኝት በማስመልከት የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ ኪን ጋንግ የፊታችን ረቡዕ ጥር 3/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት ጋር ተገናኝተው የሁለትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ኪን ጋንግ እና ሙሳ ፋኪ መሐመት በተገኙበት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ባለስልጣናት ስትራቴጂካዊ ውይይት ያደርጋሉ ብሏል ኅብረቱ የሚንስትሩን ጉብኝት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ።

የቀድሞው በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር እና የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ስለመገናኘታቸው የተባለ ነገር የለም።

ከጥቂት ቀናት በፊት የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ኪን ጋንግ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

ሚንስትሩ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር ጽኑ ፍላጎቷን ገልጸው፤ በኪን ጋንግ የስልጣን ዘመን የሁለቱ አገራት አጠቃላይ ስትራቴጂካዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር ጠንካራ የሚባል ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያላት ሲሆን፤በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ የሆነ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ዋና መስሪያ ቤት እየገነባች ትገኛለች።

ኅብረቱ በዚህ መግለጫው ቻይና 90 ሺህ ሜትር ስኩዌር የሚሸፍን ቦታ ላይ የሚያርፈውን ፕሮጀክት ከመገንባት ባለፈ በቁሳቁስ ታሟላለች ብሏል።

የሲዲሲ አፍሪካ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታው ሲጠናቀቅ የአስቸኳይ ጊዜ የኦፕሬሽን ማዕከል፣ የዳታ ማዕከል፣ ቤተ-ሙከራ፣ የስልጠና እና የኮንፍረንስ ማዕከላትን ጨምሮ መኖሪያ እና መስሪያ ቤቶች እንደሚኖረው ተገልጿል።

ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉሪቱ ለሚገኙ አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ከመስጠቷ በተጨማሪ በአገራቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ታከናውናለች።

ቤይጂንግ ከምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ በአፍሪካ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ወታደራዊ ፍላጎቶቿን ለማሳካት የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።

በምሥራቅ አፍሪካ ሰፊ የሆነ ወታደራዊ ፍላጎት ያላት ቤይጂንግ፣በጂቡቲ ግዙፍ የባሕር ኃይል ሰፈር ገንብታለች።

በቅርቡም በግጭት እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለተወጠረው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ልዩ መልዕክተኛ መሾሟ ይታወሳል።

አንጋፋው ዲፕሎማት ዡ ቢንግ የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸውን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጎ ነበር።

ቻይና በምስራቅ አፍሪካ ላላት ፖለቲካዊ እና ምጣሄ ሃብታዊ ፍላጎቶች በኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ያለው ግጭት እና አለመረጋጋት ፈተና የሆኑባት ጉዳዮች ናቸው።