ኢዜማ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ‘አገሪቱ ያለችበትን ችግር እያወሳሰበ ይገኛል’ አለ

ኢዜማ ሎጎ

የፎቶው ባለመብት, ECSJ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እየገባ እንደ አገር ያለንበትን ችግር ውስብስብ እያደረገው ይገኛል አለ።

ፓርቲው ዛሬ ሐሙስ የካቲት 02/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በክልሉ ሰላምና ደኅንነትን ማስከበር ያልቻለው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ እና በተግባር ወገንተኝነት እያሳየ ነው ብሏል።

አክሎም ፈጽሞ የፀጥታ ስጋት ባልሆኑ ምእመናን ላይ የኃይል እርምጃ ወስዶ የዜጎች ሕይወት እንዲቀጠፍ እና አካል እንዲጎድል ምክንያት ሆኗል ብሏል።

ፓርቲው ይህን ያለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ በአንዳንድ አካባቢዎች በግጭቶች ምክንያት ሰዎች ላይ ጉዳት እየደረስ ስለመሆኑ ሪፖርቶች እየወጡ ባሉበት ወቅት ነው።

ፓርቲው ይህን ይበል እንጂ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስተዳደራቸው በክልሉ የደኅንነት ችግርን ከመቅረፍ በላይ የሚፈልገው ነገር እንደሌላ ተናግረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ከክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ከቀናት በፊት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ ውስጥ ስላጋጠመው ችግር በቀጥታ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች እና ሲቪል አስተዳደሪዎች መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው ብለዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ እውቅና እውጪ የጵጵስና ሹመት መሰጠቱ እና አዲስ ሲኖዶስ የማቋቋም እንቅስቃሴ እንዳለ መገለጹ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ ሹመቱን ሕገ-ወጥ ነው በማለት ሿሚዎቹን እና ተሿሚዎቹን ካወገዘች በኋላ በጉዳዩ መንግሥት ጣልቃ እየገባ እና “ለሕገ-ወጥ ቡድኑ” አድልዎ እያሳየ ነው በሚል መንግሥትን ኮንናለች።

ቤተ-ክርስቲያኗ የመንግሥት ኃይሎች በእምነት ተቋማት እና በእምነቱ ተከታዮች ላይ ወረራዎች፣ እስሮች፣ ማዋከቦች እና ግድያዎች ተፈጽመዋል ስትል ቆይታለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከክልሉ መንግሥት በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱም “ዐይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት በገሀድ እያሳየ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰዱ ዋነኛው ተጠያቂ ያደርገዋል” ብሏል።

ፓርቲው መንግሥት የሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ እጁን መክተቱ መዘዙ ከፍተኛ መሆኑን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ ያለ ሲሆን፤ የተፈጠረው ችግር መፈታት ያለበት በተቋሙ ሕግ እና አሠራር መሠረት መሆን እንደሌለበት መክሯል።

“ውስጣዊ አሠራር አልፈው ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ካሉ ያለምንም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በሕጋዊ መንገድ ብቻ መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል።”

ኢዜማ የእምነቱ ተከታዮች የቤተክርስቲያን ጥሪ ተከትሎ ጥቁር በመልበሳቸው ደብደባ፣ መዋከብ፣ እስር እና ማስፈራራት ሲደርስባቸው እና መንግሥታዊ የአገልግሎት መስጪያ ተቋማት ጭምር በደል ሲደርስባቸው ተመልክቻለሁ ብሏል።

ኢዜማ ይህ የዜጎችን ነፃነት መጋፋት ስለሆነ በምንም መንገድ ተቀባይነት የለውም ያለ ሲሆን የእምነቱ ተከታዮች ላይ እና የሃይማኖት አባቶች ላይ የሚደረጉ ማዋከቦች፣ እስሮች እና ግድያዎች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል ሲል በመግለጫው አትቷል።

ፓርቲው ጨምሮም ችግሩ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰተ መሆኑን ጠቅሶ መስፋፋቱ አሳሳቢ እንደሆነ በዛሬው ዕለት ቀውስ ተከስቶባቸዋል ያላቸውን በአዲስ አበባ ዳርቻዎች ያሉ ስፍራዎችን ጠቅሷል።

በዚህም መሠረት መግለጫ ችግሩ “በወሊሶ መስመር በወለቴ፣ በአለምገና እና በሰበታ አካባቢዎች ተባብሶ ቀጥሏል” ብሏል።

በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ ወደ አየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አዲስ አስተዳዳሪዎች እየመጡ ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ የቤተ ክርስቲያኗ ደወል በመሰማቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪ ተሰብስቦ እንደነበነበር ገልጿል።

ነገር ግን የፀጥታ ኃይሎች ከስፍራው ድርሰው “የቤተ ክርስቲያኗ ደወል ከመደወሉ በስተቀር የተፈጠረ አዲስ ነገር እንደሌለ በማረጋገጥ አካባቢውን እና ኅብረተሰቡን የማረጋጋት ስራ እየተሰራ” መሆኑን አመልክቷል።

ጨምሮም በተከታታይ ቀናት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተከሰቱ “ሕገ ወጥ ተግባራትን የፀጥታ ኃይሉ በትዕግስት ማለፉን” የአዲስ አበባ ፖሊስ በመግለጫው ጠቅሶ፤ “ሕብረተሰቡ ወደ ግጭት እንዲገባ ቅስቀሳ እና ግፊት የሚያደርጉ ግለሰቦችን እንደማይታገስ እና አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ” እንደሚወስድ አሳስቧል።