የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የመላክ ሐሳብ የኔቶ አባላት ውድቅ አደረጉት

የዩክሬን ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዩክሬንን ለማገዝ ሁሉንም አማራጮች መጠቀም ልንጠቀም ይገባል በሚል ወታደሮችን የማሰማራት ዕቅድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ውድቅ አደረጉ።

አሜሪካ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ የኔቶ አባል አገራት ጦራቸውን ወደ ዩክሬን እንዳያሰማሩ ግልጽ አድርገዋል።

ማክሮን ምዕራባውያን ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ለመላክ የተደረሰ ስምምነት የለም ብለዋል።

ሆኖም ፕሬዚዳንት ማክሮን ሰኞ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ “ጦር የማሰማራቱን የሚያስገድድ የደህንነት ፍላጎት ሊኖር ስለሚችል ማስቀረት የለብንም” ብለዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው የኔቶ ወታደሮች በዩክሬን ከተሰማሩ ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ እንደሚገቡ አስጠንቅቀዋል።

የሩስያ ኃይሎች በቅርቡ በዩክሬን ከፍተኛ ስኬት ያገኙ ሲሆን ዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲደረግላት አስቸኳይ ጥሪ አቅርባለች።

የፈረንሳዩ መሪ ንግግሩን ያደረጉት ዩክሬንን የሚደግፍ ስብሰባ በምታስተናግደው ፓሪስ ሲሆን የአውሮፓ አገራት መሪዎች እንዲሁም አሜሪካ እና ካናዳ እየተሳተፉበት ነው።

በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተከፈተው የዩክሬን ወረራ ሦስተኛ ዓመቱን የጀመረ ሲሆን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ እየተካሄደ የሚገኘው ትልቁ ጦርነት በቅርቡ ስለማብቃቱ ምንም ምልክት አልታየበትም።

ማክሮን የሰጡት አስተያየት ከሌሎች የአውሮፓ እና የኔቶ አባል አገራት ምላሽ አሰጥቷል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "ለድል መንገድ የሚጠርግ" ወታደራዊ ዕርዳታ እየተሰጠ ነው ብለው ያምናሉ። "ስለዚህ የዩክሬን ወታደሮች ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስፈልጋቸው የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች አሏቸው" ሲል ዋይት ሃውስ በመግለጫው አስታውቋል።

"ፕሬዚዳንት ባይደን አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን እንደማትልክ በግልጽ ተናግረዋል" ሲል አክሏል።

የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ደግሞ የትኛውም የአውሮፓ ወይም የኔቶ አባል አገር ጦሩን ወደ ዩክሬን እንደማይልክ በተስማማው አቋም ላይ ምንም አይነት ለውጥ የለም ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የሪሺ ሱናክ ቃል አቀባይ በበኩላቸው የዩክሬን ሃይሎችን በማሰልጠን ላይ ካሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደራዊ ሃይሎች ባሻገር አገሪቱ ወደ ዩክሬን ጦሯን ለማሰማራት ዕቅድ የላትም ብለዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጽህፈት ቤት ደግሞ የአገሪቱ "ድጋፍ ከአውሮፓ ወይም ከኔቶ ግዛቶች ወታደሮችን በዩክሬን ግዛት ማሰማራትን አያካትትም" ብሏል።

ፔስኮቭ ክሬምሊንን ወክለው እንዳስታወቁት የማክሮንን ሀሳብ "በጣም አስፈላጊ የሆነ አዲስ ክስተት” በማለት ከመግለጽ ባለፈ፣ በፍጽም የኔቶ አባላትን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

"እንደዚያ ከሆነ ስለ አይቀሬ [ቀጥታ ግጭት] መነጋገር አለብን” ብለዋል።

የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ቀደም ብለው እንዳስታወቁት ወታደሮቹ ወደ ዩክሬን ይላካሉ የሚለውን ውድቅ አድርገው፣ የኔቶ አባል ያልሆነችውን ዩክሬንን መደገፉን እንደሚቀጥል ግን አስምረውበታል።

ይህ አቋም ስፔን፣ ፖላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክን ጨምሮ በበርካታ የኔቶ አባል አገራት ተስተጋብቷል።

ሩሲያ ከፍተኛ መሣሪያ እና ከዩክሬን እጅግ የላቀ ወታደራዊ ኃይል አላት። ኪዬቭ በበኩሏ ከምዕራባውያን አጋሮች በተለይም ከአሜሪካ በሚሰጡ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ላይ ጥገኛ ናት።

"ውጥረት የሞላበት" ስብሰባ

ባይደን በኦቫል ኦፊስ በተካሄደው ስብሰባ ለዩክሬን የሚሰጠውን የ60 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ጨምሮ የ 95 ቢሊዮን ዶላሩን የአሜሪካን የእርዳታ ዕቅድ የኮንግረሱ መሪዎች እንዲያጸድቁ አሳስበዋል።

ድጋፉ በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። ሪፐብሊካኑ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ማይክ ጆንሰን ከድጋፉ ስምምነት በፊት ተጨማሪ የድንበር ማሻሻያዎችን እንዲደረግ አጥብቀው ተናግረዋል።

በሜክሲኮ እና በአሜሪካ ድንበር ላይ ያለው ቀውስ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ጆንሰን ገልጸዋል። ባይደን ማሻሻያዎቹን በድጋፉ ውስጥ ለማካተት ቢያካትቱም ሪፐብሊካኖች ግን ጉዳዩን ይዘውታል።

የሴኔቱ ዲሞክራቲክ መሪ ቹክ ሹመር በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ሆኖ በማያውቅ መልኩ የኦቫል ኦፊስ ስብሰባ በውጥረት የተሞላ ነበር ብለዋል።

አሜሪካ ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ በመስጠት ትልቁን ድርሻ የምትይዝ ሲሆን እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 15 ድረስ 45 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች ሲል የኪየል ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።

በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ በ17.7 ቢሊዮን ዩሮ በመስጠት ጀርመን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 9.1 ቢሊዮን ዩሮ ወታደራዊ እርዳታ ሰጥታለች።

ሰኞ ዕለት በቪዲዮ በፓሪሱ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ “የሩሲያን ጥቃት ለመከላከል በጋራ የምናደርገው ነገር ሁሉ ለመጪዎቹ አሥርት ዓመታት በአገሮቻችን ላይ እውነተኛ ደህንነትን ይጨምራል” ብለዋል።