በዓለም ዙሪያ ከ1 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ከመጠን ላለፈ ውፍረት መጋለጣቸውን ጥናት ጠቆመ

ወፍራም ህጻን

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

በመላው ዓለም ከአንድ ቢሊዮን የሚልቁ ሰዎች ከመጠን ላለፈ ውፍረት (ኦቤሲቲ) ተጋልጠዋል ተብሎ እንደሚገመት አንድ ጥናት አመልክቷል።

ከዚህ ውስጥ 880 ሚሊዮን የሚሆኑት አዋቂዎች ሲሆኑ 159 ሚሊዮኖቹ ደግሞ ህጻናት እና ታዳጊዎች መሆናቸውን በአውሮፓውያኑ 2022 የተሰበሰበው መረጃ ያሳያል።

ከልክ ያለፍ ውፍረት ያላቸው ሴቶች በከፍተኛ ቁጥር የሚገኙት ቶንጋ በተባለች ሀገር እና አሜሪካን ሳዎማ በተሰኘ የአሜሪካ ግዛት ሲሆን በወንዶች ደግሞ አሜሪካን ሳዎማ እና ናኡሩ በተባለች ሀገር ነው። በእነዚህ አካባቢዎች ከጠቅላላው ህዝብ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው አዋቂ ከመጠን ላለፈ ውፍረት የተጋለጠ ነው።

ዓለም አቀፍ የሳይንቲስት ቡድን ከልክ ያለለፈ ውፍረትን ለመቆጣጠር ጥረት የሚደረግበት መንገድ በአፋጣኝ ሊቀየር ይገባዋል ብለዋል።

ከመጠን ያለፈ ውፍረት የልብ ህመም፣ የስኳር በሽታ እና ካንሰርን ጨምሮ ለበርካታ አሳሳቢ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን በተመለከተ በዝቅተኛ እና ከፍተኛ በመክፈል የተደረገው ጥናት ካሳያቸው መካከል፡

  • አሜሪካ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸውን ወንዶች በመያዝ ከዓለም ከፍተኛ የ‘ኦቤሲቲ’ ዝርዝር 10ኛ ደረጃ ላይ ስትሆን በሴቶች ደግሞ 36ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
  • ህንድ ከልክ ያለፈ ውፍረት ያላቸውን ወንዶች በመያዝ ከዓለም ዝቅተኛ የ‘ኦቤሲቲ’ ዝርዝር 19ኛ ደረጃን ስትይዝ በሴቶች 21ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
  • ቻይና ከዓለም ዝቅተኛ የ‘ኦቤሲቲ’ ዝርዝር በሴቶች 11ኛ በወንዶች 52ኛ ደረጃ ላይ ተቀማጣለች

በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማጂድ ኢዛቲ ደሴታማ በሆኑ አብዛኞቹ ሀገራት ከጤና ምግቦች አንጻር ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች የመገኘት እድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ይናገራሉ።

“ጤናማ የሆኑ ምግቦች በማይገኙበት እና ዋጋቸው ውድ በሆነበት በአንዳንድ ሁኔታዎች ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች በተጋነነ ሁኔታ ይተዋወቃሉ” ሲሉም አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለዓመታት ከልክ ያለፉ ውፍረቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን የሚከታተሉት ፕሮፌሰሩ ጨምረው፣ መረጃው እያሳየ ያለው እውነታ እየተቀየረ ያለበት ፍጥነት እንዳስገረማቸው ገልጸዋል። ተጨማሪ በርካታ ሀገራት ከልክ ያለፈ ውፍረት ቀውስ እየሆነባቸው እንደሆነ ጠቅሰው በተቃራኒው በከፍተኛ ሁኔታ መክሳት ከ’ኦቤሲቲ’ በላይ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም “ አዲሱ ጥናት በአዋቂነት እድሜ መግቢያ ላይ በአመጋገብ፣ በአካላዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም በበቂ እንክብካቤ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመከላከል እና ለማስተካከል ሊሰራ እንደሚገባ ያመላከተ ነው” ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረውም ችግሩን ለማስተካከል የመንግሥታትን እና የህብረተሰብ ጥረት እንደሚጠይቅ ጠቅሰው “ምርቶችን ከጤና ሁኔታ ጋር ለመቃኘት ከምንም በላይ የግል ዘርፉን ተሳታፊዎች ትብብር ይጠይቃል” ሲሉ ገልጸዋል።

በማዳራስ የስኳር ህመም ምርምር ፋውንዴሽን ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶክትር ጉሃ ፕራዲፓ የዓለም የጤና መሰረታዊ ችግሮች ምንጭ የሆነው እና ከልክ በላይም ይሁን በታች ለሆነ ውፍረት የሚዳርገው ከስነ ምግብ ጋር የተያያዘ ችግር እንደሆነ አንስተዋል።

ተመራማሪዋ “እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመጣው ችግር እና የዩክሬን ጦርነት ድህነትን በመጨመር እና በስነ ምግብ የበለጸጉ ምግቦችን በማስወደድ ከልክ ያለፈውንም ሆነ ከልክ በታች ውፍረትን አባብሶታል” ብለዋል።

አክለውም በሀገራት ያለው የጤናማ ምግቦች እጥረት ሰዎች ጤናማ ወዳልሆኑት እንዲሄዱ አድርጓቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የሚሰሩ ከ1500 በላይ ተመራማሪዎች ይህንን ጥናት ለመስራት የ220 ሚሊዮን ሰዎችን የክብደት እና ቁመት ምጣኔንን ለክተዋል።

ተመራማሪዎቹ ይህ መለኪያ በሰውነት ውስጥ ያለን ስብ ለማወቅ እንከን አልባ ነው ለማለት ባይደፍሩም ዓለም አቀፍ ጥናቶችን ለመስራት ጥቅም ላይ የሚውል እንደሆነ ገልጸዋል።