በዩናይትድ ኪንግደም የቀረበው ከመቅደላ የተዘረፈው ጋሻ ጨረታ ኢትዮጵያ ቅሬታ በማቅረቧ ተሰረዘ

ከመቅደላ የተዘረፈው ጋሻ

የፎቶው ባለመብት, Anderson & Garland

በዩናይትድ ኪንግደም በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፎ የሄደ ጋሻ ለጨረታ ከወጣ በኋላ ኢትዮጵያ ቅሬታ በማቅረቧ መሰረዙ ተገለጸ።

ቅርሱ በአውሮፓውያኑ 1868 በነበረው የመቅደላ ጦርነት ላይ በብሪታንያ ወታደሮች ተዘርፎ የተወሰደ ነው።

አንደርሰን ኤንድ ጋርላንድ የተባለው የጨረታ ኩባንያ ጋሻውን በጨረታ ለመሸጥ በሰሜን ምስራቅ ኒውካስትል ትናንት የካቲት 21/ 2016 ዓ.ም እቅድ ይዞ ነበር።

“ሁኔታውን በጥንቃቄ ከገመገምን በኋላ ጋሻውን ከትናንትናው ጨረታ ዝርዝር ለማውጣት ወስነናል። ጉዳዩንም እንደገና እንዲያዩት ወደ ሻጮቹ መልሰነዋል” ሲሉም የአንደርሰን ኤንድ ጋርላንድ ቃለ አቀባይ ለብሪታንያው ጋዜጣ ዘ ቮይስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የጋሻው ጨረታ መሰረዙን “ብልህ ውሳኔ ነው” በማለትም ቅርሶቹን ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደትም እንደሚመራ ተስፋ ማድረጉን ለሮይተርስ የዜና ወኪል በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሆኖም የጨረታ ኩባንያው ሽያጩን ለመሰረዝ ምክንያቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የተዘረፉ ቅርሶቹ እንዲመለሱለት እያቀረበ ካለው ጥያቄ ጋር ስለመያያዙ ያለው ነገር የለም።

ጋሻው በጨረታ ለሽያጭ መቅረቡ በተገለጸበት ወቅት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጨረታውን “ተገቢ ያልሆነ እና ሥነ ምግባር የጎደለው” ማለታቸው ተገልጿል።

አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በ1868 ዓ. ም. ከእንግሊዝ አገር ከመጡ 32 ሺ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ተከትሎ በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ ዘረፋ እንደተፈፀመ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።

የእንግሊዝ ጦር ቅርሶቹን ከመቅደላ ለመውሰድ 15 ዝሆኖችንና 200 በቅሎዎችን ለማጓጓዣነት ተጠቅመው እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ምንም እንኳን የእንግሊዝ ጦር አዛዦች አፄ ቴዎድሮስ ይዘዋቸው የነበሩ እስረኞችን ለማስፈታት ነው ቢሉም የንጉሡን ቁንዳላ ከመሸለት በተጨማሪ መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፤ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ዘርፈዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መጻሕፍት፣ የተለያዩ ከወርቅ የተሠሩ ቅርሶችን፣ መንፈሳዊ ሥዕሎችን፣ ታቦታት፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፤ ቅርሶች ተቃጥለዋል፤ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል።

በተጨማሪም በወቅቱ የሰባት ዓመት ልጅ የነበረውን ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን የወሰዱት ሲሆን ሕይወቱም በግዞት ማለፉ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በዊንድሶር ካስትል የተቀበረውን የልዑል አለማየሁ አጽም እንዲመለስላት ጥያቄ ብታቀርብም ከባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ተቀባይነት አላገኘም።

ኢትዮጵያ ከመቅደላ የተዘረፉና በሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ቅርሶቿ እንዲመለሱላት ለተለያዩ የእንግሊዝ ቅርስ ተቋማት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርባ ነበር።