ኔታኒያሁ ችላ ያሏቸው በተለያዩ አገራት የሚገኙ ሐማስ ሚሊዮኖችን የሚያንቀሳቅስባቸው የገንዘብ ምንጮች

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመፈፀሙ ከዓመታት በፊት የገንዘብ ፍሰቱን ለማስቆም የነበራቸውን ዕድል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ አልተጠቀሙበትም ሲል አንድ የቀድሞ የእስራኤል ከፍተኛ የስለላ መኮንን ተናገረ።
ቤንያሚን ኔታንያሁ የሐማስ ገንዘብ ፍሰት ላይ እንዲያነጣጥሩ ሐሳብ መሰንዘሩን ኡዲ ሌቪ ለቢቢሲ ፓኖራማ ተናግሯል።
የስለላ መኮንኑ በወቅቱ እርምጃ ቢወሰድ ኖሮ ለቡድኑ ወታደራዊ ዝግጅት እንቅፋት ይሆን ነበር ብሎ ቢያምንም፣ የእስራኤል መንግሥት ግን መረጃው ላይ ተመሥርቶ እርምጃ አልወሰደም ብሏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለቀረበው ክስ ምላሽ አልሰጠም።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ታጣቂዎች ወደ ደቡባዊ እስራኤል ተሻግረው 1200 ያህል ሰዎችን ገድለው፣ ከ250 በላይ ሰዎችን አግተው ወስደዋል። አንድ መቶ ሰላሳ ታጋቾች አሁን ድረስ የደረሱበት አልታወቀም።
የእስራኤል ሠራዊት አስካሁን ድረስ እየወሰደው ባለው ወታደራዊ እርምጃ ከ30 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ተገድሏል ሲል በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቋል።
እአአ እስከ 2016 ድረስ የእስራኤል የስለላ ድርጅት በሆነው በሞሳድ ውስጥ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት ሌቪ፤ አገራቸው ጋዛን የሚቆጣጠረውን ሐማስን ለማስቆም “የፋይናንስ ቁጥጥር ማድረግ” እንደሚገባ በተደጋጋሚ ለኔታንያሁ ተናግረው እንደነበር ገልጸዋል።
ለኔታንያሁ የቀረበው ሃሳብ ምንም አይነት ምላሽ አላገኘም ሲሉ ሌቪ አክለዋል።
ኔታንያሁ በሐማስ ፋይናንስ ጉዳይ ለመነጋገር ፈቃደኛ ያለመሆናቸው እና መስከረም 26 በደረሰው ጥቃት መካከል ግንኙነት ስለመኖሩ የተጠየቁት ሌቪ በማያሻማ መልኩ መልሰዋል።

“በትክክል አዎ። ወደ ጋዛ የገባውን ብዙ ገንዘብ መከላከል እንችል ነበር። ሐማስ የገነባው አቅም እንዳሁኑ ላይሆን ይችል ነበር የሚል ትልቅ እምነት አለ” ብለዋል።
ሐማስ ከጋዛ መሬት ሥር የገነባቸውን በመቶ ኪሎ ሜትሮች የሚገመቱ ዋሻዎችን ለመሥራት እና 30 ሺህ ለሚገመተው ወታደራዊ ኃይሉ ምንዳ ለመክፈል “ቢሊዮኖች እንጂ ሚሊዮኖች” አይበቃውም ነበር ይላሉ የቀድሞው የስለላ ኃላፊ።
ሌቪ በ2014 (እአአ) ለኔታንያሁ ካነሱት የገንዘብ ምንጮች አንዱ መቀመጫውን ቱርክ ያደረገው እና በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን የሚያዘዋውረው እና ሞሳድ በሐማስ ሥር እንደሚገኙ ከሚገልጻቸው ኢንቨስትመንቶች አንዱን ነው።
ኔታንያሁ በመረጃው ላይ ተመሥረተው እርምጃ ላለመውሰድ መርጠዋል ብለዋል።
የእስራኤልን ህልውና የማይቀበለው እና አገሪቱን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው ሐማስ ከወታደራዊ ኃይልም በላይ ነው። ከጋዛ ባሻገር የተዘረጋ የገንዘብ ድጋፍ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው።
ሌቪ ከኔታንያሁ ጋር ስላደረጉት ውይይት “ዋና ዋና [የቡድኑ] ስፖንሰሮች ስለሆኑት ኳታር እና ኢራን ተነጋግረናል። ቱርክ በጣም ቁልፍ ናት። ምክንያቱም ለሐማስ የፋይናንስ መሠረተ ልማቶቹን ለማስተዳደር ወሳኝ ናት” ብለዋል።
ቢቢሲ ፓኖራማ የሐማስን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያሳያል የተባሉትን በ2020 የተገኙ ሰነዶች ሲመረምር ቆይቷል። የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሐማስ ገንዘቡን እንዴት እንደሚያገኝ ያሳያል ብሏል።
በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ያሉ 40 ኩባንያዎች በሐማስ ቁጥጥር ውስጥ እንደሚገኙ ይታመናል። ከእነዚህም መካከል ሳዑዲ አረቢያ፣ አልጄሪያ፣ ሱዳን፣ ግብፅ፣ የባሕረ ሰላጤው አገራት እና ቱርክን ያካትታል።
ቡድኑ ተሠማርቶባቸዋል ከተባሉት ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ከመንገድ ግንባታ፣ ከፋርማሲዩቲካል እና ህክምና መሳሪያዎች እስከ ቱሪዝም፣ ማዕድን ማውጣት፣ የወርቅ ፍለጋ እና የቅንጦት ሪል ስቴት ፕሮጀክቶችን ያጠቃልላል።
ከ2022 ጀምሮ በሰነዶቹ ውስጥ ከተዘረዘሩት ኩባንያዎች መካከል ስድስቱ በአሜሪካ ግምጃ ቤት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሐማስ ባለቤትነት ወይም ቁጥጥር ተደርጎባቸዋል ተብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ በመጣል የንግድ አቅማቸውን አዳክማለች።
ከተዘረዘሩት ኩባንያዎች ቀጥሎ ያለው እያንዳንዱ በሐማስ ቁጥጥር ስር ያለው ድርሻም ተገልጿል። ሐማስ ከአንዳንዶቹ ኩባንያዎች ያለው ድርሻም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ሲሆን፣ አጠቃላይ ዋጋው እስከ 422 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል።
ከዚህ ውስጥ አብዛኛው በሪል እስቴት ላይ የዋለ ነው ተብሏል።
በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ የፋይናንስ ወንጀሎች እና የደኅንነት ጥናቶች ማዕከል (ሲኤፍሲኤስ) መሥራች የሆኑት ቶም ኪቲንግ እንዳሉት ዋጋቸው የማይዋዥቅ እና የኪራይ ገቢ የማስግኘት አቅም ያላቸው የንብረት ኢንቨስትመንቶች እንደ ሐማስ ላሉ ድርጅት ለማስተዳደር “ፍጹም የተመቹ” ናቸው።

በአሜሪካ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ኩባንያዎች አንዱ ትሬንድ ጊዋይኦ የተባለው የቱርክ ሪል እስቴት ድርጅት ነው። እአአ በ2018 ሰነድ ውስጥ በቅድሞ ስሙ “አንዳ ቱርክ” ተብሎ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷ።
የመስከረም 26ቱ ጥቃት ወይም ሐማስ እንደሚለው “ዘመቻ አል-አቅሳ” መፈጸሙን ተከለትሎ የትሬንድ የቀድሞ ሊቀ መንበር ሃሚድ አብዱላህ አል-አህማር አሙግሰውታል። የቀድሞቀው ሊቀ መንበር በኋላም የትሬንድ ዋና ኩባንያ ኃላፊ ሆኖ ቀጥሏል።
እአአ ጥር 2024 በኢስታንቡል በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ሲያደርግም “ዘመቻ አላቅሳ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እያለ እና የተወዳጇ ፍልስጤም ወረራ ሳይቀለበስ ከማይቆመው ዘመቻ በኋላ እንገናኛለን” ሲል ተደምጧል።
በመቀጠልም “ጽዮናዊነትን እንደ ዘረኛ እና የአሸባሪነት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዲሠራ” ጉባኤውን ጠይቋል።
ፓኖራማ ለአል-አህማር ስለጉዳየ ጥያቄ ቢያቀርብም ምንም ምላሽ አላገኘም።
ትሬንድ ለቢቢሲ እንደገለጸው ከሆነ የአሜሪካ ግምጃ ቤት በኩባንያው እና በሐማስ መካከል ግንኙነት አለው ሲል ያቀረበውን ክስ “ፍትሃዊ ያልሆነ እና መሠረተ ቢስ ነው” ብሎታል።
የቱርክ ባለሥልጣናት ትሬንድ ላይ ምርመራ እንዳደረጉ እና “የአገራችንን የፋይናንስ ሥርዓት የጣሰ ነገር” እንዳላገኙ እና ቱርክ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሕጎችን ታከብራለች ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሐማስ ግን የተለያዩ እና የረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ የገንዘብ ምንጮች አሉት።
ዋና ከሚባሉት የቡድኑ የገንዘብ አሰባሰቢዎች አንዱ ያህያ ሲንዋር ሲሆን፣ አሁን በጋዛ የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ መሪ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ግለሰቡ በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ እያለ ነበር ለሐማስ ገንዘብ ማሰባሰብ የጀመረው። ሲንዋር እአአ በ1988 ለእስራኤል ይሰልላሉ ብሎ የጠረጠራቸውን ፍልስጤማውያንን በመግደሉ ነበር ለእስር የተዳረገው።
ሚካ ኩቢ ቀደም ሲል የእስራኤል የፀጥታ ባልደረባ ሆኖ አገልግሏል። ሲንዋርን ከ150 ሰዓታት በላይ እንደጠየቀው ይናገራል። ሲንዋር እስር ቤት ሆኖ ምሥጢራዊ መልዕክቶችን በመላክ ከኢራን ጋር ግንኙነት ፈጥሯል ብሏል።
እአአ በ2007 ሐማስ በምርጫ ሥልጣን ከያዘ ከአንድ ዓመት በኋላ እስራኤል እና ጎረቤቷ ግብፅ ለደኅንነታቸው ሲሉ ጋዛ ላይ የጣሉትን እገዳ አጠናክረዋል። የሲንዋር እና የኢራን ግንኙነት እገዳውን ለማሸነፍ እንደረዳው ኩቢ ተናግሯል።
“ግንኙነቱን ለመጀመር ወደ ኢራን መልዕክተኞችን ላከ። የጦር መሳሪያ እንዲልኩትም ጠየቃቸው። እናም [ሐማስን] በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ለመርዳት ተስማሙ” ብሏል።
“ያ የሁሉም ነገር መጀመሪያ ነበር።”
የሞሳድ የቀድሞ ኃላፊ ኡዲ ሌቪ እንደተናገሩት ለሐማስ የሚሆን ገንዘብ ከባሕረ ሰላጤዋ ኳታር በግልፅም ሆነ በስውር ይደርስ ጀመር።
ከገንዘቡ የተወሰነው ጥሬ ገንዘብ በሰጠችው ፈቃድ መተላለፉን እስራኤል አምናለች። ይህም በሐማስ መንግሥት ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናትን ደመወዝ ለመክፈል እና ለጋዛ ሕዝብ ሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት የተመደበ ነው።
“ኳታራውያን በየወሩ የሚመጣ ልዩ ልዑክ [አላቸው]። በግል ጄት ወደ ራፋህ ሻንጣ ይዞ ይመጣና ጋዛ ገብቶ ሻንጣውን ለሐማስ ባለሥልጣናት ሰጥቶ ሰላምታ አቅርቦ ይመለሳል” ሲሉ ሌቪ ተናግረዋል።
ለፓኖራማ እንደተናገሩትም “ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛው መጠን የሐማስን ወታደራዊ ክንፍን ለመደገፍ የሚውል ነው” ይላል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ በዌስት ባንክ የሚገኘው የፍልስጤም አስተዳደር እና በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ድጋፍ ተደርጓል። ሁሉም ለሰብአዊ ዓላማዎች የታሰቡ ናቸው።
የሮያል ኢኒስቲቲዩቱ ቶም ኪቲንግ ይህ ገንዘብ ለሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ድጎማ ውሎ ሊሆን ይችላል የሚለውን “ፍትሃዊ ግምገማ” ሲል ጠርቶታል። “[ሐማስ] ገንዘቡን እንደ ዋሻ መገንባት እና ጦሩን ማስታጠቅን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ሊያውለው ይችላል” ብሏል።
ሐማስ ከለጋሾች ገንዘብ ምን ያህሉን ለወታደራዊ አገልግሎት መጠቀሙን ማወቅ አልቻለም።
ቡድኑ ምንም ዓይነት የእርዳታ ገንዘብ ለሌላ ዓላማ እንደማያውል አስተባብሏል። ወታደራዊ ክንፉ የራሱ የገቢ ምንጭ እንዳለው ለፓኖራማ ተናግሯል።
እአአ በ2019 ኔታንያሁ ለገዥው ፓርቲ ሊኩድ ባልደረቦቻቸው “የፍልስጤምን መንግሥት ምሥረታ ለማደናቀፍ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሐማስን ማጠናከር እና ገንዘቡን ወደ ሐማስ ማስተላለፍን መደገፍ አለበት…በዌስት ባንክ ያሉ ፍልስጤማውያን ከጋዛ መነጠል የስትራቴጂያችን አካል ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ ኔታንያሁ ሐማስን መገንባት ይፈልጉ ነበር መባሉን አስተባብለው፣ የኳታር ገንዘብ ወደ ጋዛ እንዲገባ የፈቀዱት ሰብአዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ኔታንያሁ ሐማስን ለማጥፋት ቃል ገብተዋል። በጋዛ ሽብርተኝነትን የሚደግፍ ምንም ዓይነት አካል አይኖርም ብለዋል።
አብዛኛውን የጋዛን አካባቢ በማጥፋት እና በርካታ ፍልስጤማውያንን በመግደል እስራኤል ካሰበችው ተቃራኒው ውጤት ሊገጥማት ይችላል።
ኤልጊንዲ “ኢራን ሐማስን በማስታጠቅ እና በገንዘብ መደገፏን ልትቀጥል ትችላለች። ከዚህ በላይ ግን እንደ ሐማስ ያለ ቡድን እነዚያን መሳሪያዎች ለማግኘት የሚሞክርበት ምክንያት እስካለ ድረስ ያንን ያደርጋሉ” ብለዋል።
“ለምን ከተባለ ለእነሱ ምክንያት የሆኑት ነገሮች አሁንም አሉ” ብለዋል።












